1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተወላጆች ጦርነት ይቁምልን ድምጽ በአዲስ አበባ

ማክሰኞ፣ መስከረም 24 2015

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኙ በእንግሊዝ እና የአሜሪካ ኤምባሲዎች እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተገኝተው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲቆም ድምጻቸውን አሰምተዋል። በቁጥር ውስን የሆኑት ሰልፈኞቹ ሰላም እንዲሰፍን ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

https://p.dw.com/p/4HjYU
Äthiopien Addis Abeba | Menschen aus der Region Tigraya demonstrieren vor der US-Botschaft
ምስል Seyum Getu/DW

የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ

የትግራይ ተወላጆች ጦርነት ይቁምልን ድምጽ በአዲስ አበባ 

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኙ በእንግሊዝ እና የአሜሪካ ኤምባሲዎች እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተገኝተው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲቆም ድምጻቸውን አሰምተዋል። 

በቁጥር ውስን የሆኑት ሰልፈኞቹ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ አሳስበው፤ በጦርነት ውስጥ ተጎጂ የሆነው የትግራይ ህዝብ ሰላም እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡

በሰልፉ በጦርነቱ የጎላ ሚና አለው ያሉትን ህወሓትን እንደሚቃወሙ የተናገሩት ሰልፈኞቹ ከሕወሓት  በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሌሎችም በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ኃይላት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ጦርነት የሚቆምበትን መንገድ እንዲፈልጉም አሳስበዋል፡፡

የትግራይ ተወላጆች ሰልፍ
አዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ትግራይ ክልል የሚደረገዉ ጦርነት እንዲቆም በሰልፍ ጠየቁምስል Seyum Getu/DW

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በእንግሊዝ ኤምባሲ እና በአፍሪካ ህብረት ፊትለፊት ተገኝተው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደና የበርካቶችን ደም እያፋሰሰ ያለውን ጦርነት የተቃወሙት ሰልፈኞች፤ በተለይም የጦርነቱ አንዱ ተዋናይ የሆነውን ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ከሰልፈኞቹ አግኝቼ ያነጋገርኳቸው መድህን አሰፋ የተባሉ እናት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት እሳቸው በዚህ ሰልፍ ላይ የተገኙት በሁሉም ወገን በጦርነቱ የተሳተፉትን በመቃወም ለሰላምም እንዲሰራ ለማሳሰብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

“በዚያ በጦርነቱ እያለቀ ያለው ጭቁን ህዝብ እጣፈንታው ያሳስበናል” ያሉን እኚህ እናት፤ በጦርነቱ የሚፋለሙ አካላት በሙሉ ሰላም እንዲያወርዱ ጠይቀዋል፡፡

የዚህ ሰልፍ አስተባባሪ የሆኑት ሰለሞን ገብረ እግዚኣብሔር ስለ ሰልፉ ዓላማ እና ግብ ለዶይቼ ቬለ ሲገልጹ፤ “አንደኛ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጋር አንድ ነው መባሉን መቃወም ነው” ይላሉ፡፡ አቶ ሰለሞን አክለውም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የሚያሳድሩት ተጽእኖ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቢቻ  የሚወሰን ሳይሆን ጦርነቱን ቀስቅሷል ያሉት ህወሓት ላይ እንዲጠነክር መጠየቅ ሌላው የሰልፉ ዓለማ ነው ብለዋል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba | Menschen aus der Region Tigraya demonstrieren vor der US-Botschaft
ምስል Seyum Getu/DW

ወይዘሮ ኢሌኒ ሌላኛዋ የዛሬው ሰልፍ ተሳታፊ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ ለተጽእኖ ፈጣሪ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በሰልፉ ማስተላለፍ የፈለጉት መልእክት ወደ ትግራይ የሚላኩ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይዘርፋል ያሉት ህወሓት ከዲርጊቱ እንዲቆጠብ ነው፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ እንግልት የዳረገው ጦርነት እንዲቆም ጥሪውን ያቀረበው ሌላው የሰልፉ ታዳሚ ወጣት ዳዊት በርሄ ደግሞ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ሶስተኛ ዙር የያዘው ጦርነት ህዝቡን የሚያስከፍለው ዋጋ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ፤ በዚያም ድምጻቸው ታፍኗን ላላቸው ድምጽ መሆን የሰልፉ ዓለማ ነው ይላል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የኢትዮጵያ መንግስት ለ5 ወራት የዘለቀውን የተናጥል የተኩስ አቁም ጥሪ በማቅረብ በአፍሪካ ህብረት መርህ ከህወሓት ኃሎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ሰባት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ኮሚቴንም አዋቅሮ ነበር፡፡ ህወሓት በበኩሉ ለዚህ ቀናውን ምላሽ ለመስጠት ዘግይቷል በሚል በኢትዮጵያ መንግስት ቢወቀስም በዘንድሮው የኢትዮጵያ አዲስ አመት መቀበያ እለት መስከረም 01 ባስተላለፈው ጥሪ ያለ ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር መዘጋጀቱን አሳውቆ ነበር፡፡

ይሁንና የሁለቱም ተፋላሚ ኃይላት የሰላም ጥሪው አንዱ ሌላኛው ላይ ባሳደረው ጥርጥሬ ወደ ገቢራዊነት የመጣ አይመስልም፡፡ የዛሬውን ሰልፍ ካስተባበሩት አንደኛው አቶ ሰለሞን ገብረእግዚአብሔርም የቅርብ ጊዜውን የህወሓት የሰላም ጥሪ ያመኑ አይመስልም፡፡

“ህወሓት ወደ ሰላም ከመጣ እሰዮ ነው፡፡ ለዚያ ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩን ብንጓጓም” ይላሉ አስተያየት ሰጪው፡፡

በዛሬው ሰልፍ ላይ ታድመው አስተያየታቸውን ያጋሩን ታዳሚያኑ ለጦርነቱ ህወሓትን ብቻ ተጠያቂ የሚያደርጉ እና መፍትሄውም በዚያ ብቻ የሚመጣ ብለው እንደማያምኑ በአስተያየታቸው ያረጋግጣሉ፡፡ የሰሜን ኢትጵያው ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ በሁሉም ተፋላሚ ሃይላት ቁርጠኝነት የሚመጣ እንደመሆኑ ሁሉም አካላት ለሰላም እንዲሰሩም ያሳስባሉ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ቢሊየን ንብረቶችን አውድሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወትን መቅጠፉን ቀጥሏል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ተቀስቅሶ አውዳሚነቱን የቀጠለው ጦርነት ከዓለማቀፍ ማህበረሰብም ዘንድ በተደጋጋሚ የሚተችና ተፋላሚ ሃይላትን በጦርነት ቀስቃሽነት ሲያወዛግም መቆየቱም ይታወቃል፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ