1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተወላጆች ውይይት በድሬደዋ

ሰኞ፣ መስከረም 23 2015

በውይይቱ በጦርነቱ ተሳታፊ ሆኗል ያሉት «የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ነው ያሉትን ድርጊት በፅኑ በመቃወም መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ» ሲሉ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4Hh0E
Äthiopien Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

የትግራይ ተወላጆች ውይይት በድሬደዋ

የድሬደዋ አስተዳደር በከተማው ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር ዛሬም ድረስ መቋጫ ባላገኘው የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት "የግጭቱ ቀስቃሽ" ባለው ህወሀት እየተፈፀመ ባለው የጦርነት ድርጊት እና የህዝቡ እጣ ፈንታ ላይ የመምከር ዓላማ እንዳለው የገለጠውን ውይይት አድርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች "በክልሉ በከፋ ችግር ውስጥ ይገኛሉ" ያሏቸው ነዋሪዎች ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው አንስተዋል። "መንግስት ለህዝቡ ሲል መድሀኒትና ምግብ የሚቀርብበትን ሁኔታ እንዲያመቻች" ጠይቀዋል።

አንድ አስተያየት ሰጪ "ወያኔ ባጠፋው ጥፋት ህዝቡ እልቂት መጣበት ፤ ህፃናት እየሞቱ ነው በአጥንት ቀርተዋል ምነው ይህን ያህል ጭካኔ?" ሲሉ ቁጭታቸውን ገልፀዋል።ይህ የተከሰተው "አንደኛ እርዳታ በማጣቱ ፣ ሁለተኛ መድሀኒት በማጣቱ እና ሶስተኛ ገንዘብ በማጥስቱ ነው የትግራይ ህዝብ የተቸገረው" ብለዋል ።

መንግስት በውጭ ድርጅት አድርጎ ለእነዚህ ህዝቦች እርዳታ እንዲሰጥ ቢያደርግ ሲሉ ጠይቀዋል።

በውይይቱ በጦርነቱ ተሳታፊ ሆኗል ያሉት" የኤርትራ መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ነው ያሉትን ድርጊት በፅኑ በመቃወም መንግስት ለምን ዝምታን መረጠ" ሲሉ ጠይቀዋል።

በውይይቱ ከተሰጡ አስተያየቶች አብዛኞቹ "የኤርትራ መንግስት ወደ ትግራይ ገብቶ ጥቃት እየፈፀመ ነው ይሄ መቆም አለበት" የሚል ነው ።

Äthiopien Dire Dawa | Kedir Juhar
ምስል Messay Teklu/DW

"የትግራይ ህዝብን እና ወጣቱን ወደ ቁጣ ያሻገረው ሻዕቢያ ነው " ያሉ አድተያየት ሰጭ" ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነው ለምን ሻዕቢያ ይገባል ?" ሲሉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በድሬደዋ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርስ የከፋ ችግር አለመኖሩን ያነሱት ተሳታፊዎች በቀበሌ እና አንዳንድ ቦታዎች መገለል እንዳለ ጠቅሰው ይኸው መፍትሄ እንዲደረግለት ጠይቀዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በከተማው" ሽብርተኛ "ያሉትን ህወሀት አጀንዳ ለማስፈፀም ሲሰሩ በነበሩ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ከመደረጉ ውጭ በብሔር ማንነት የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ጠቅሰው አለአግባብ የተፈፀመ ችግር ካለ ባፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ተሳታፊዎቹ በአስተዳደሩ በሚከናወኑ ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

መሳይ ተክሉ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ