1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ባንኮች ስራ መጀመር

ረቡዕ፣ የካቲት 1 2015

ከመቐለ ውጭ በበርካታ የትግራይ ከተሞች ከትላንት ጀምሮ ዛሬ ደግሞ በብዛት አገልግሎት አቆርጠው የነበሩ ባንኮች ወደ ስራ እየተመለሱ ነው። የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ለገንዘብ አዘዋዋሪዎች እስከ 50% በመክፈል ለቤተሰብ እና ወዳጅ ይልኩ ለነበሩ በውጭ ላሉ የክልሉ ነዋሪዎችም ቢሆን እፎይታ የፈጠረ ሆንዋል።

https://p.dw.com/p/4NF2R
Äthiopien | Wiederaufnahme Bankbetrieb in Mekelle
ምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ የባንኮች ሥራ መጀመር

በትግራይ የተለያዩ ከተሞች ያሉ የግልና መንግስት ባንኮች ወደ አገልግሎት በመመለሳቸው ተከትሎ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው መነቃቃቱ ተገለፀ። ላለፊት 19 ወራት ተዘግተው የቆዩ በትግራይ የሚገኙ ባንኮች ከትላንት ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው እየተመለሱ ሲሆን፣ የባንኮች ደንበኞች ደግሞ ለረዥም ግዜ ታግዶባቸው የነበረ ገንዘባቸው ከተቋማቱ በማውጣት ላይ ናቸው። በመቐለ አስተያየት የሰጡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በባንኮች  ያስቀመጡት ገንዘብ ማውጣት ተከልክለው ለረዥም ግዜ ችግር ላይ መቆየታቸው ገልፀዋል። 

የሰላም ስምምነቱ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ትግራይ ጥሬ ገንዘብ መላክ በመጀመሩ በመቐለ እና የተለያዩ የትግራይ ከተሞች የሚገኙ የግልና መንግስት ባንኮች በረዥም ግዜ በኃላ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በመቐለ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሌሎች የግል ባንክ ቅርንጫፎች ደጃፍ በርካታ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ የተሰለፉ ህዝብ የሚስተዋል ሲሆን፣ አንዳንድ ባንኮች ለደንበኞቻቸው እስከ 50 ሺህ ብር ወጪ እንዲያደርጉ መፍቀዳቸው ተነግሯል። ይህ በጦርነቱ ምክንያት ያስቀመጠው ገንዘብ ማግኘት ላልቻለ ህዝብ እንደ መልካም አጋጣሚ የተገለፀ ሲሆን ተቀዛቅዞ የነበረው ኢኮኖሚም ያነቃቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል። 

Äthiopien | Wiederaufnahme Bankbetrieb in Mekelle
ምስል Million Haileselassie/DW

በመቐለ በሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው ቅርንጫፍ ገንዘብ ሲያወጡ ያገኘናቸው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ መለሰ ለክፉ ቀን ብለው በባንክ ያስቀመጡት ገንዘብ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸው የሚገልፁ ሲሆን አሁን የተፈጠረው ዕድል ለመጠቀም ረዥም ተራ ተሰልፈው ገንዘባቸው ማውጣታቸው ይናገራሉ። 

ሌላው ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር በኃላ ገንዘባቸው ከባንክ ሲያወጡ ያገኘናቸው የመቐለ ነዋሪው አቶ ክብሮም ግደይ ባንኮች በመዘጋታቸው እሳቸውን ጨምሮ ሕብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ መቆየቱ ይናገራሉ።  "የባንክ አገልግሎት በመዘጋቱ የደረሰው ጉዳት ይህ ነው ተብሎ አይገልፅም። የጤና ዕክል አጋጥሞን ለችግር ተጋልጠናል። ከበሽታ ከሞት የሚወጣበት አጋጣሚ በገንዘብ እጦት በርካቶች አጥተናል" ያሉት አቶ ክብሮም  ይህ መጥፎ አጋጣሚ በታሪክ የሚታወስ ነው ብለውታል። አሁን ላይ የባንክ አገልግሎት መከፈቱ ግን ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።
ከመቐለ ውጭ በበርካታ የትግራይ ከተሞች ከትላንት ጀምሮ ዛሬ ደግሞ በብዛት አገልግሎት አቆርጠው የነበሩ ባንኮች ወደ ስራ እየተመለሱ ነው። የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ለገንዘብ አዘዋዋሪዎች እስከ 50% በመክፈል ለቤተሰብ እና ወዳጅ ይልኩ ለነበሩ በውጭ ላሉ የክልሉ ነዋሪዎችም  ቢሆን እፎይታ የፈጠረ ሆንዋል። በትግራይ ሁለት ሚልዮን ገደማ ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ መደበኛ የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ለዶቼቬለ ገልጿል። 
የባንኩ ኮርፖሬት ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሳን አሰፋ ያልተቋረጠ የባንክ አገልግሎት በትግራይ ላሉ  ለደንበኞች ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መገባቱ ገልፀዋል። ኮምኒኬሽን ዳይሬክተሩ "ዛሬ ጠዋት ላይ 31 ረፋድ ላይ ደግሞ 16 ተጨማሪ ቅርጫፎቻችን ስራ ጀምረዋል። ይሄ ሙሉ በሙሉ ትግራይን የሚያጠቃልል ነው። የሽሬ ዲስቲሪክትም ስራ እንዲጀምር ተደርጓል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ የነበረው አገልግሎት ሙሉበሙሉ ነው ያስጀመረው። ከዚህ በኃላም ቢሆን ምንም አይነት የካሽ እጥረት ይኖራል ብለን አንገምትም" ብለዋል። በቀጣይም የኤቲኤም እና ፖስት ሜሽን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ለመጀመር ይሰራል ብለዋል።
ሚልዮን ሃይለስላሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸት በቀለ

Äthiopien | Wiederaufnahme Bankbetrieb in Mekelle
ምስል Million Haileselassie/DW