1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታህሳስ 27 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27 2016

https://p.dw.com/p/4avlH

የሱዳን ብሔራዊ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ከፈጥኖ ደራሽ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ አር ኤስ ኤፍ ጋር «እርቅ እንደማይኖር » አስታወቁ።

የሱዳን ብሔራዊ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ከፈጥኖ ደራሽ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ አር ኤስ ኤፍ ጋር «እርቅ እንደማይኖር » አስታወቁ። አልቡርሃን ትናንት አርብ ለሰራዊታቸው ባደረጉት ንግግር ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ተፈጻሚ አይሆኑም ፤ ዉጊያውም ይቀጥላል ። አልቡርሃን በንግግራቸው «አማጽያኑ በምዕራብ ዳርፉር እና በተቀረው ሱዳን የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል መፈጸማቸውን የተቀረው ዓለም ስለሚያውቅ » ከእነርሱ ጋር የሚደረግ እርቅ አይኖርም ብለዋል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ዳግሎ ሰሞኑን ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ በርካታ የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተዋል። ዩጋንዳ፣ኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ ጀቡቲና ደቡብ አፍሪቃን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ከብሄራዊ ጦሩ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን የሱዳን መንግስት ኬንያ ዳጋሎን ተቀብላ በማስተናገዷ አምባሳደሯን ወደ ሀገር ቤት ጠርታለች። የአሁኑ የአልቡርሃን የእርቅ አይኖርም ንግግር ሲታከልበት ደግሞ የምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት ኢጋድ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ለማሸማገል በያዘው ውጥን ላይ ሳያጠላ እንደማይቀር ተገልጿል። ዳጋሎ የሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔራዊ ጦሩ እጅ የነበሩ በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምርጫ ባለስጣናት በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ በመራጮች ላይ ደረሰ ባለው ማስፈራራት እና ማጭበርበር የሶስት ሚንስትሮችን እና የአራት ክልል አስተዳዳሪዎችን የምርጫ ውጤት ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምርጫ ባለስጣናት በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ በመራጮች ላይ ደረሰ ባለው ማስፈራራት እና ማጭበርበር የሶስት ሚንስትሮችን እና የአራት ክልል አስተዳዳሪዎችን የምርጫ ውጤት ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ።  የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ በመላው ሀገሪቱ መጭበርበር ተፈጽሞባቸዋል ባላቸው የ82 ዕጩዎችን የምርጫ ውጤት ሰርዟል። ኮንጎ ባለፈው ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ/ም የሃገራዊ እና የክልል ምክር ቤቶች የህግ አውጪዎች እና የአካባቢ ምክር ቤት አባላት ምርጫ አከናውናለች። ነገር ግን በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች መዘግየት መከሰቱን ተከትሎ እስከ ቀጣዩ ቀን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንዲራዘም መደረጉ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።የምርጫ ውጤቱ ይፋ ሲደረግ ግን የኮንጎ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ውድቅ አድርገውታል። የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽንም የተቃዋሚዎችን አቤቱታ ተከትሎ አደረኩ ባለው ማጣራት በበርካታ አካባቢዎች ህገ ወጥ የምርጫ ቁሳቁሶች መጠቀምን ጨምሮ በማጭበር ፣ ድምጽ መሰወር እና በመራጮች ላይ ተፈጽሟል ላለው ማስፈራራት እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ገልጿል። የምርጫ ውጤቱ ከተሰረዘባቸው ባለስልጣናት መካከል የመዲናዋ ኪንሻሳ ገዢ ይገኙበታል ።  የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ፕሬዚደንት ፊልኪስ ቲሲሽኬዲ 73 ከመቶ ድምጽ በማግኘት በድጋሚ መመረጣቸው ይታወሳል።

አሜሪካ ለፍልስጥኤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የፋይናንስ ምንጭ ናቸው ያለቻቸው የአምስት ግለሰቦች የፋይናንስ መረጃ   ለጠቆማት የ10 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ ማቅረቧን አስታወቀች

አሜሪካ ለፍልስጥኤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የፋይናንስ ምንጭ ናቸው ያለቻቸው የአምስት ግለሰቦች የፋይናንስ መረጃ   ለጠቆማት የ10 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ ማቅረቧን አስታወቀች። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአምስቱ ግለሰቦች የፋይናንስ መረጃ አልያም ወደ መረጃው የሚያመራ ጥቆማ ላቀበለ ወሮታ ይከፈለዋል። በአሜሪካ የፋይናንስ መረጃቸው በጥብቅ የሚፈለጉት አምስቱ ግለሰቦች አብዱልባሲጥ ሃምዛ ኤልሃሰን ፣ አሜር ካማል ሻሪፍ ፣ አህመድ ሳዱ ጃህሌብ ፣ ዋሊድ መሐመድ ሙስጠፋ እና ሙሃመድ አህመድ አብደ አል ዳይም ሲሆኑ ቀደም ሲል በዩናትድስቴትስ ዓለቀፍ  የሽብር ወንጀል ተፈላጊ የነበሩ ናቸው ። ተጠርጣሪዎቹ መቀመጫቸውን በሱዳን ፣ ቱርክ ፣ ቃጣር እና ኢራን ያደረጉ በርከት ያሉ የንግድ ተቋማትን ሲመሩ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ለታጣቂው ቡድን ሃማስ ማስተላለፋቸው እንደተደረሰበት የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።  የአሁኑ የአሜሪካ እርምጃ በታጣቂ ቡድኑ ላይ የወሰደችው አራተኛው ዙር የፋይናንስ ማዕቀብ አካል መሆኑን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።

የዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን ለጋዛው ቀውስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመሻት ወደ ቱርክ አቀኑ

የዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን ለጋዛው ቀውስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመሻት ወደ ቱርክ አቀኑ ። ብሊንከን ለአንድ ሳምንት ይቆያል በተባለ የዲፕሎማሲ ጉዞ ዛሬ ኢስታንቡል ውስጥ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ታይፕ ኤርዶኻን ጋር ተነጋግረዋል። ቱርክ ፤ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት የፕሬዚዳንት ኤርዶኻን መንግስት አውግዞታል። ብሊንከን ከኤርዶሃን ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድመው ከቱርኩ አቻቸው ሃካን ፊዳን ጋር በጋዛ ስላለው የሰብአዊ ሁኔታ እና ቱርክ የስዊዲን የሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ትብብር ኔቶን እንድትቀላቀል ለማጽደቅ ቱርክ እያደረገች ባለው ጥረት ላይ ተነጋግረዋል። ብሊንከን ዛሬ ከቱርክ ባለስልጣናት በተጨማሪ  ከግሪክ አቻቸው ጋር ለመነጋገር ወደ ቀርጤስ ደሴት ተጉዘዋል። ዩናይትድስቴትስ ለግሪክ የኤፍ 35 የጦር አውሮፕላኖች ሽያጭ በኮንግረንሱ በሚጸድቅበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ብሊንከን በቀጣዩ ሳምንት እስራኤል እና የዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻን ጨምሮ የተለያዩ የአረብ ሃራትን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያ ድንበር ላይ ወደ ምትገኝ ደሴት ከ60 በላይ ሚሳኤሎች አስወነጨፈች

ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያ ድንበር ላይ ወደ ምትገኝ ደሴት ከ60 በላይ ሚሳኤሎች አስወነጨፈች ። የዛሬው የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ናዳ ትናንት አርብ ከተፈጸመ ተመሳሳይ የሚሳኤል እሩምታ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል። ሰሜን ኮሪያ ትናንት አርብ በተመሳሳይ 200 ሚሳኤሎች በደሴቲቱ አቅራቢያ  አስወንጭፋለች ። በጥቃቱ በሲቪሊያውያንም ይሁን በጦር ኃይሉ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አቃባይ አስታውቋል። የሰሜን ኮሪያ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃትን ተከትሎ በሁለት ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል። የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር የደሴቶቹን ነዋሪዎችን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ ለሰሜን ኮሪያ ሚሳይል አዘፋ ለመስጠት አልያም ሌላ የተባለ ነገር የለም ። ነገር ግን ድርጊቱ ከጎርጎርሳውያኑ 2010 ወዲህ በሁለቱ ሃገራት መካከል ውጥረት ማስከተሉን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያን ተደጋጋሚ የሚሳኤል ማስወንጨፍ በኮሪያ ባህረገብ ምድር የለየለት ጠብ አጫሪነት ነው ስትል ትከሳለች። ለአጸፋው ሰራዊቷ ተመጣጣን እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቃለች።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።