1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃዮች መብዛት ያሳሰበው የሰሜን ሸዋ ዞን

ሐሙስ፣ የካቲት 23 2015

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላለክልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት «ተፈናቃዮችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ከአቅሜ በላይ ሆኗል» አለ። ተፈናቃዮች በበኩላቸው «የርዳታ እህል ባለመኖሩ አማራጫችሁን ፈልጉ ተብለናል» ይላሉ። የፌደራሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንንም በክልሉ ለሚገኙ ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እርዳታ እያቀረበ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4OApj
Äthiopien Binnenvertriebene aus Wollega fordern humanitäre Hilfe
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ተፈናቃዮች የበዙበት የሰሜን ሸዋ ዞን

በርካታ ተፈናቃዮችን ከሚያስተናግዱ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንዱ ነው። ቀደም ሲል 76,500 ያህል ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ይኖራሉ። በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን አኖ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት 2,921 ሰዎች ፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ 6,210 ሰዎች ተፈናቅለው ወደ ደብረ ብርሀን መምጣታቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አስታውቋል። ከወራት በፊት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በዚሁ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አዋሳኝ ወረዳዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭትም በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የዕለት ርዳታ እየወሰዱ እንደሆነም አመልክቷል።

የተፈናቃዩ ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ በመምጣቱና የአቅርቦት እጥረት በመኖሩ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ተፈናቃዮችን ለመቀበል ከአቅሙ በላይ መሆኑን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

በዞኑ ያለው የተፈናቃይ ቁጥር ከአቅሙ በላይ መሆኑን ጽ/ቤቱ ማሳወቁን ያረጋገጡልን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን በበኩላቸው፣ ከፌደራል መንግሥት የሚላከው ርዳታም ወቅቱን ያልጠበቀና በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
የቀረበውን የርዳታ አቅርቦት ችግር ስሞታ በተመለከተ ምላሽ የሰጡን የፌደራል መንግሥት አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ በክልሉ ለ2.4 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊዎች ርዳታ እንደሚቀርብ አመልክተው፣ የኮሚሽኑ የአሰራር ግንኑነት መርህ ከክልል ጋር በመሆኑ የዞንና የቀበሌ ጥያቄዎችን እንደማይመልሱ ተናግረዋል።

አስተያየት የሰጡ አንድ ደብረብርሀን የሚገኙ ተፈናቃይ የሚጠለሉበት፣ የሚመገቡትና የሚታከሙበት ቦታ እንደሌላቸው ገልጸው፤ ዞኑ ተፈናቃይ አንቀበልም፣ የራሳችሁን አማራጭ ውሰዱ በማለቱ ግራ  እንደተጋቡ አስረድተዋል። በአማራ ክልል በዋናነት ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከማንነት ጋር በተያዘ በነበሩ ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሲሆን በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ደግሞ ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች የተፈናቀሉ 70ሺህ ያህል ተፈናቃዮች በሰቆጣና አካባቢው ተጠልለው ይገኛሉ።
ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ