የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ኮሮና ያሳደረዉ ተጽእኖ
ዓርብ፣ መጋቢት 25 2012ማስታወቂያ
የኮሮና ተህዋሲ ሥርጭትን ለመከላከል የተጣሉ የአውሮፕላን በረራ እገዳዎች ከምሥራቅ አፍሪቃ የበረሃ አንበጣ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) አሳሰበ። ድርጅቱ እንዳለው በበረራ እገዳ እና ክልከላዎች ምክንያት የሚረጩ መድኃኒቶች አቅርቦት ዘግይቷል። በአሁኑ ጊዜ የበረሃ አንበጣን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በመድሐኒት እጥረት ምክንያት ከተደናቀፈ፣ ከ4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ቤተሰቡን መመገብ አይችልም። ኬንያ መጋዘን ዉስጥ የተቀመጠው መድኃኒት ከቀናት በኋላ ያልቃል። አንበጣ በዚህ ዓመት የመን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያን ክፉኛ ጎድቷል። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መንግሥታት ድንበሮቻቸውን ከመዝጋታቸውም በላይ የእቃ ጫኝ አውሮፕላኖች በረራዎችንም ቀንሰዋል። ይህም የበረሃ አንበጣን ለማጥፋት የሚረጨውን መድኃኒት ዓለም አቀፍ አቅርቦት ያናጋ ሲሆን በአውሮጳ እና በእስያም የመድኃኒቱ ምርት እንዲቀንስ አድርጓል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ