1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ ውይይት መደረጉ

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2016

በቅርቡ ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል የተባለውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የነፃ ማድረግ የሥራው ዋነኛ መርህ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4XuqK
ፎቶ ከማኅደር፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
በምክር ቤት ስለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ውይይት ተካሂዷል። ፎቶ ከማኅደር፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምስል Solomon Muche/DW

የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ

 

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አስፈላጊነት

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ አለመረጋጋቶች፣ ግጭቶችና የእርስ በርስ ጦርነት መቋጫ አለማግኘታቸው ዜጎችን ለሞት፣ ለመፈናቀል በማጋለጣቸው ፣ የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆናቸው የአጥፊዎችንና የተጎጅዎችን ቁጥር ማብዛቱ ነው የተገለጸው። የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማኅበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል በማለቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅን ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት አምኖበት ሥራው ከተጀመረ አሥር ወራቶች አልፈዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የታቀፉትና 14 አባላት ያሉት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አርቃቂ የባለሙያዎች ቡድን በቅርቡ ፖሊሲውን አርቅቆ እንደሚያጠናቅቅ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቀዋል።

ፍትሕ ሚኒስቴር በባለሙያዎች እያዘጋጀው ያለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስልቶች ክስ ፣ እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማድረግ፣ እርቅ ፣ ምህረት፣ ማካካሻ ይገኙበታል። የባለሙያዎች ቡድን «የፀጥታ ሥጋት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሥራችን እንቅፋት ሆነዋል» ሲል ከዚህ በፊት መግለፁ ይታወሳል። ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ እንደሚሉት የሽግግር ፍትሕ ተጠያቂነትን ያስቀራል ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። ማን እንዴት ተጠያቂ ይሆናል የሚለው በሂደት ተግባራዊ መሆን ሲጀምር በሕግ የሚመለስ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሽግግር ፍትሕ ከመቼ ጊዜ ጀምሮ ይጀምር ? የሚለውም ገና ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ ነው። 
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስትዳደር በሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄዎች እንዳሉት እና በፖሊሲ ዝግጅቱ ላይ መሳተፍ ሲገባው እንዳልተሳተፈ ገልጾ ቅሬታ ማቅረቡን በተመለከተ በጋዜጠኞች የተጠየቁት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ አሁንም ዕድል መኖሩን ገልፀዋል።

የገለልተኝነት ጥያቄዎችና የፍትሕ ሚኒስታር ምላሽ 

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ሲቪክ ድርጅት የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ረቂቅ ፓሊሲውን የሚያወጣው ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ክስ እና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን የሚጠበቀው የፌዴራል ፖሊስ መሆናቸውን በመጥቀስ እነዚህ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ሥራውን በትክክል ያስፈጽማሉ ብሎ እንደማያምን ጠቅሶ ከሳምንታት በፊት ጥያቄ አንስቶ ንበር። ለዚህ የጋዜጠኞች ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ጌድዮን «ጥያቄው ውኃ የማይቋጥር ነው» ብለዋል። 
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ሁኔታ ማለፏን የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭት፣ በጦርነት ወይም በሌላ ምክንያት ለተፈፀሙ ጥቃቶች ፣ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሔ መስጠት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ዋነኛ አላም መሆኑን እና ውጤቱ ዘላቂ ሰላም ፣ እርቅ፣ መረጋጋት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መፍጠር መሆኑንም አስታውቋል።

 ፎቶ ከማኅደር፤ የፍትህ ምልክት
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ፎቶ ከማኅደር፤ የፍትህ ምልክትምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ