የሶርያ ውዝግብ እና መፍትሔ ፍለጋው
ረቡዕ፣ ሐምሌ 4 2004
አናን ባለፈው ሰኞ በደማስቆ ከሶርያ ፕሬዚደንት በሺር አል አሳድ ጋ ከተወያዩ በኋላ ውዝግቡን ማብቃት በሚቻልበት አካሄድ ላይ ከአሳድ ጋ ስምምነት መድረሳቸውንና በዚሁ ዕቅድም ላይ የጦር መሣሪያ ከታጠቁ የተቃዋሚ ቡድኖች መሪዎች ጋ እንደሚወያዩ ያስታወቁበት ድርጊት ተስፋ መፈጠቁ ይታወሳል።
« ሁከቱን ማብቃት እንደሚያስፈልግ እና እንዴት ማስወገድ እንደሚቻልም ተወያይተናል። ውዝግቡን ማብቃት በሚቻልበት አንድ አካሄድ ላይ የተስማማን ሲሆን፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ የጦር መሣሪያ ከታጠቀው የተቃዋሚ ወገንም ጋ እንወያይበታለን። የፖለቲካ ውይይቱን ማራመድ አስፈላጊ መሆኑንም በአፅንዖት አሳስቤአለሁ። ፕሬዚደንቱም ተስማምተዋል። »
የሶርያ መንግሥት አናን ያዘጋጁትን ባለስድስት ነጥብ የሰላም ዕቅድን እንደሚያከብርና ዓለም አቀፉ ድርጅትም ዕቅዱን እስካሁን ከታየው በተሻለ ሁኔታ በትክክል ስራ ላይ እንዲያውል መጠየቁን ኣናን አስረድተዋል። የሶርያ ተቃዋሚ ወገን ግን የአናን የደማስቆን ጉብኝት በመንቀፍ የሰላሙ ዕቅዳቸው መክሸፉን አመልክቶ፡ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሶርያ መንግሥት አንፃር ውሳኔ እንዲያሳልፍና አሳድ ሥልጣናቸውን በሚለቁበት ጉዳይ ላይ ድርድር እንዲጀመር ነው የጠየቀው። ይሁንና፡ አናን፡ ትናንት በተቃዋሚው ቡድን አስተያየት ተስፋ ሳይቆርጡ ከሩስያ ቀጥላ ዋነኛዋ የሶርያ ወዳጅ ወደሆነችው ኢራን በመሄድ ለሰላሙ ዕቅዳቸው የመንግሥቱን ድጋፍ ፍለጋ በቴህራን ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ አክባር ሳሌሂ ጋ ሀሳብ ተለዋውጠዋል፤ ውይይቱ የተሳካ እንደነበርም አመልክተዋል።
« በሶርያ ልዩ ልዑክ ሥልጣኔ ከሚንስትሩ እና ከመንግሥታቸው አበረታቺ መልስ እና ትብብር እንዳገኘሁ መግለጽ እፈልጋለሁ። ለሶርያ ውዝግብ መፍትሔ ለማስገኘት አብረን መስራታችንን እንድንቀጥል ፍላጎቴ ነው። »
አናን ከቴህራን ቀጥለው ወደ ኢራቅ መዲና ባግዳድ በመጓዝ የፕሬዚደንት አሳድ ደጋፊ ከሚባሉት ከኢራቅ ጠቅላይ ሚንስትር ማሊኪ ጋ ሀሳብ ተለዋውጠዋል። የኢራቅ መንግሥት ቃል አቀባይ አናን ባግዳድ ከመግባታቸው በፊትእንዳስታወቀው፡ ሀገራቸው መፍትሔ በማፈላለጉ ጥረት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አላት። ሩስያም ብትሆን አሁን በሶርያ መንግሥት እና በተቃዋሚዎቹ ላይ ግፊት በማሳረፍ፡ ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ድርድር እንዲጀምሩ ማስገደድ እንደሚያስፈልግ የሩስያ ፕሬዚደንት ፑቲን አስታውቀዋል። ሩስያ አሳድን መደገፏን እንድታቆም ለማግባባት ዛሬ ወደ ሩስያ የሄዱት የሶርያ ተቃዋሚ ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር አብደል ባሴት ሳይዳ ጥረታቸው ሳይሳካ መቅረቱ ተሰምቷል። ይህ በዚህ እንዳለ፡ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሶርያ ጉዳይ ላይ ለመምከር ዛሬ ስብሰባ ያካሂዳል። በሶርያ የተሰማራውና ተልዕኮ በሚቀጥለው ሣምንት የሚያበቃው 300 አባላት ያሉት የታዛቢ ቡድን ዕጣ በፀጥታ ምክር ቤቱ እጅ መሆኑን የቡድኑኃላፊ ጀነራል ሙድ አስታውቀዋል።
« ከሀምሌ ሀያ በኋላ የሚሆነውን የሚወስነው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ነው። ግን የተመድ የሶርያ ሕዝብ የወደፊት ዕጣ አስተማማኝ ለማድረግ ያሳየው ፍላጎት ከሀምሌ ሀያም በኋላ ጠንካራ ሆኖ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። »
የንስ ቪኒንግ/አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሠ