የሶማሊያ እዉነትና የለንደን ጉባኤ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2005
ያኔም ግንቦት ነበር።ግን 1901 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የለንደን ቅኝ ገዢዎች የመሩና ያስተባበሩት እና የራሷ ብሪታንያ፣ የኢጣሊያና የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ሶማሊያ ያዘመቱት ጦር በሶማሊያ ፀረ-ቅኝ ገዢ ሐይላት ለሰወስተኛ ጊዜ ተሸነፈ።ያኔም ግንቦት ነበር።ግን 1936።የፋሽሥት ኢጣሊያ መሪ ቤኒቶ መሶሎኒ አዲስ የማረኳትን ኢትዮጵያን፣ከኤርትራና ከኢጣሊያ ሶማሊያ ጋር ቀይጠዉ «አፍሪካ ኦርየንታሌ ኢታሊያና» የሚባል ግዛት መመሥረታቸዉን አወጁ። ዘንድሮም ግንቦት ነዉ።2013።ጥንት ሶማሊያ ቅኝ እንድተገዛ የተወሰነባት ለንደን፣ የዛሬዋ ሶማሌያ እንዴትነትን፣ የወደፊት ጉዞዋ ወዴትነትን የሚበይኑ ሐይላትን ጉባኤ ታስተናግዳለች።ነገ። ጉባኤዉ መነሻ፣ የሶማሊያ እዉነት ማጣቃሻ፣ እድምታዉ መድረሻችን ነዉ፥-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
የብሪታንያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊልያም ሔግ ከአስር ቀን በፊት በሞቃዲሾ የብሪታንያ ኤምባሲ የተባለዉን ቅፅር ግቢ ሲከፍቱ እንዳሉት መንግሥታቸዉ የሶማሊያን የእስካሁንና ያሁን እዉነት ብቻ ሳይሆን የወደፊት ጉዞዋን እንዴትነትም ያዉቀዋል።
ሔግ ሥለ ሶማሊያ የወደፊት ጉዞ በጎነት የሰጡትን ተስፋ ገቢር ለማድረግ መንግሥታቸዉ ይሁን ተባባሪዎቹ በጀመሩት መቀጠል አለመቀጠላቸዉ በርግጥ ሲሆን ነዉ የሚታየዉ።ከአሥራ-ሥምንተኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ዓለምን የሚቆጣጠሩት የአዉሮጳና የአሜሪካ ሐያላን ሔግ እንዳሉት የተበታተነችዉን የጎስቋላ፣ ደካማይቱን ሶማሊያን ዓይደለም የድፍን ዓለምን ሁለንተናዊ ሒደት ባሻቸዉ ማሾሩ አይገዳቸዉም።
ከማንም እና ከምንም በላይ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድመዉ ሐያል ዓለም በየሥፍራዉ እንደሚያደርገዉ ሁሉ የሶማሊያን የወደፊት ጉዞ የሚቀይሰዉም ጉዞዋና መድረሻዋ የሶማሌዎችን ፍላጎት ሥለሚያረካ ሳይሆን የሐያላኑን ጥቅም ሥለሚጠብቅና በሚጠብቅበት መልኩ መሆኑ አያከራክርም።
ሶማሊያ በተለይ አዲስ ቋሚ መንግሥት ከመሠረተች ወዲሕ በተቆጠሩት መቶ ቀናት ዉስጥ የምዕራቡን ዓለም ከፍተኛ ትኩረት መሳቧ አላከረከራም።ትኩረቱ ግን ጀርመናዊቷ የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አኔተ ቬበር እንደሚሉት ለሶማሊያ ሕዝብ ቢያንስ እስካሁን የተከረዉ የለም።
«ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሶማሊያ በተለይም ሞቃዲሾ ዉስጥ በንቃት ሲንቀሳቀስ እናያለን።ቱርኮች ቤቶች ሲገነቡ፥ ሠብአዊ ርዳታ ሲያቀብሉ እናያለን።የጀርመንዋ አምባሳደር ሞቃዲሾ ዉስጥ የሹመት ደብዳቤያቸዉን ሲያቀርቡ እናያለን።ብሪታንያዎች፥አሜሪካኖችም ሞቃዲሾ ዉስጥና ወደ ሞቃዲሾ ሲመላለሱ እናያለን።በሌላ በኩል ግን ባለፉት መቶ ቀናት የታየዉ ሁሉ ለሶማሊያ ሕዝብ የጠቀመዉ የለም።»
ሔግ በቅርቡ የተናገሩትን ተስፋ እዉን ለማድረግ መንግሥታቸዉና ተባባሪዎቹ ከጣሩ የሚጥሩትም ለእነሱ እስከጠቀመና እስከፈለጉት ድረስ ብቻ ባይሆን ኖሩ የኤምባሲ ፅሕፈት ቤት ለመክፈት፣ ጉባኤ ለመጥራት፣ ሞቃዲሾ በድብቅም ቢሆን ለመመላለስ እና ገንዘብ ለማዋጣት ሃያ-ሁለት ዘመን ባልጠበቁ ነበር።
የዛሬዋ ሶማሊያ ለንደኖች ቅኝ ሊገዟት የዘመቱባት፣ ቅኝ የገዟትም አይነት አይደለችም።የዛሬዋ ሶማሊያ የለንደን መሪዎች በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የሮም ጠላቶቻቸዉን የመቱባት፣ ወይም በሺሕ ዘጠኝ መቶ ሥልሳዎቹ መጀመሪያ ነፃነቷን የፈቀዱላት አይደለችም።የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያም አይደለችም።የሔግ ቀዳሚዎች ኤምባሲያቸዉን የዘጉባት፣ አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ የሚገዛት አይነትም አይደለችምም።
የዛሬዋ ሶማሊያ ሔግ እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባደራጁት፣ ዴቪድ ካሜሩን እንደጠቅላይ ሚንስትር በሚመሩት በነገዉ ጉባኤ ሠነድ እንደተጠቀሰዉ፥ የጎሳ መሪዎች የወከሉት ምክር ቤት የተሰየመባት፣ አዲስ ሕገ-መንግሥት የፀደቀባት፥ ቋሚ መንግሥት የተመሠረተባት ናት።የሶማሊያ ጉዳይ አጥኚ ረሽድ አብዲም ይሕን ይመሰክራሉ።
«ባለፈዉ አንድ ዓመት በርካታ ገንቢ ለዉጦች ታይተዋል።መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎችን በማስፋፋቱ ረገድ ብዙ እመርታ ታይቷል።ያም ሆኖ በሶማሊያ ጦር ዉስጥ አሁንም የመዋቅርና የአደረጃጀት ችግር አለ።»
የፖለቲካ ተንታኙ እንዳሉት ሶማሊያ ከብዙ ችግሮቿም ጋር ቢሆን ዛሬ ከተሻለ ደረጃ መድረሷ እዉነት ነዉ።ከተሻለ ከሚባለዉ ደረጃ ለመድረሷ ከማንም፥ የዉጪ ሐያል ትልቁን እገዛ ያደረገዉ የአፍሪቃ ሕብረት ያዘመተዉ ጦር ነዉ።አሚሶም።የዩጋንዳ፥ የብሩንዲ፥የኢትዮጵያ በቅርቡ የኬንያ፥ የጅቡቲ እና የሌሎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ወታደሮች ዛሬም ደም ሕይወታቸዉን እየገበሩ ነዉ።
የአፍሪቃ ወታደሮች ባይኖሩ ኖሩ ባለፉት መቶ ቀናት ከዋሽንግተን-እስከ ብራስልስ ብዙ የተነገረለት፥ አድናቆት፥ እዉቅና ድጋፉ የተንቆረቆረለት የፕሬዝዳት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ መንግሥት ሳምንታት መቆየቱም ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ማርክ ፕላንክ ኢንስቲቱዩት የተሰኘዉ የጀርመን ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ማርኩስ ሆነ እንደሚሉት አዲሱ መንግሥት የርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾን ፀጥታ እንኳን ማስከበር አልቻለም።
«እዉነቱን መናገር ከተፈለገ የሞቃዲሾ (አንፃራዊ) ፀጥታ እንኳን የተፈጠረዉ በአሚሶም ድጋፍ ነዉ።መንግሥት የራሱን ርዕሠ-ከተማ ፀጥታ እንኳን ለማስከበር የዉጪ ሐይላት ጥገኛ ነዉ።ምክንያቱም የራሱ ፀጥታ አስከባሪዎች ብቁ አይደሉም።»
የለንደኑ ጉባኤ አዘጋጆች እንዳሉት የነገዉ ጉባኤ ከሚመክርና ከሚወስንባቸዉ ርዕሶች ዋናዉ ረሺድ «የመዋቅርና የአደረጃጀት ችግር አለበት» ያሉት የሶማሊያ መንግሥት የፀጥታ ሐይል ነዉ።የጉባኤዉ አዘጋጆች እንዳሉት የፕሬዝዳት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ መንግሥት ጦር ሐይሉን፥ ፖሊስ ሠራዊቱን፥ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚያደራጅ፥ የሚያጠናክርበትን፥ የገንዘብ ወጪዉን ቅጥ የሚያሲዝበትን ዕቅድ ያቀርባል።
ሐምሳ ሐገራትንና እና ድርጅቶችን የሚወክሉት ጉባኤተኞች ደግሞ እነዚሕን ዕቅዶች ገቢር ለማድረግ የሚረዱበትን ሥልት ይነድፋሉ።እና የሶማሊያን የጉዞ አቅጣጫ ይወስናሉ።አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አ-ሸባብ ትናንት ከሞቃዲሾ ያሥተላለፈዉ መልዕክት ግን ካሁኑ መላ ካልተበጀለት፥ የሶማሊያ የወደፊት ጉዞ እንደ እስካሁኑ ሁሉ ጨፍጋጋነቱን በግልፅ አመልካች ነዉ።የአሸባብ አጥፍቶ ጠፊዎች እንዳፈነዱት በታመነ-ቦምብ በትንሽ ግምት አስር ሰዉ ገድለዋል።
አሸባብ ከሁለት ሳምንት በፊት ሞቃዲሾ ላይ ባደረሰዉ ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃት ከሰላሳ በላይ ሰዎች ገድሎ ነበር።ከዓለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት አል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለዉ የሚባለዉን አሸባብን ማጥፋት የፖለቲካ አዋቂ አብዲ ረሺድ እንደሚሉት እንዲሕ ባጭር ጊዜ የሚሳካ አይነት አይደለም።
«አደጋ ለመጣል በጣም የቆረጡ እና በቅጡ የተደራጁ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊዎች አሉ።ሞቃዲሾ ዉስጥ ባለፈዉ የተፈፀመዉን ጥቃት፥ እንዳየነዉ በጣም አደገኛ ሁኔታ መኖሩን ጠቋሚ ነዉ።እና እኔ ከአሸባብ ጋር የሚደረገዉ ትግል ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ነዉ ብዬ እሰጋለሁ።»
የጠመንጃዉ ትግል ኢራቅና አፍቃኒስታን፥ ላይ ያመጣዉን ዉጤት አይተናል።እርግጥ ነዉ አሜሪካኖች የአልቃኢዳ ተባባሪ ይሏቸዉ ከነበሩት ከኢራቅ የሱኒ አማፃያን ጋር የተደራደሩት፥ የአፍቃኒስታኑ ፕሬዝዳት የሐሚድ ካርዛይ መንግሥት ከታሊባኖች ጋር እንዲደራደር ግፊት ማድረግ የጀመሩት የጠመንጃዉ ዉጊያ ከዕልቂት ዑደት ባለፍ የተከረዉ እንደሌለ በመረዳታቸዉ ነዉ።
የለንደኑ ጉባኤ የሶማሊያ መንግሥት ጦር ሐይሉን እንዲያደረጅ፥ እንዲያጠናክር ከማዘዝ ሌላ ከሶማሌዎች መሐል ከወጡት የሶማሊያ ሸማቂዎች ጋር እንዲደራደር በሐሳብ ደረጃ እንኳን አይጠቁምም። በጉባኤዉ ከተጋበዙ መሪዎች አንዱ ደግሞ አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሑሩ ኬንያታ ናቸዉ።
ኬንያታ በምዕራባዉያኑ ፍላጎትና ግፊት የተመሠረተዉ፥ የሚሠራዉና፥ የሚመማራዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በሰዉ ልጅ ላይ በተፈፀመ ወንጀል የከሰሳቸዉ ፖለቲከኛ ናቸዉ።ግን ብሪታንያዎች የሚሉትን ከፈፀሙ፥ ብሪታኒያዎች ባዘጋጁት ጉባኤ ላይ እንዲገኙ በብሪታንያዎች ከተጋበዙ በወንጀል መጠርጠር፥ በትልቁ ፍርድ ቤት መከሰሳቸዉ፥ ምናልባት እንደተጠረጠሩት ሕዝብ አጫርሰዉም ከሆነ-ሁሉም የሚወሳ ጉዳይ አይደለም።
የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በ1890ዎቹ ማብቂያ ወደ ዛሬዋ ሰሜን ሶማሊያ ብቅ ያሉት፥ ደቡብ ሶማሊያ ኢጣሊያኖች፥ ጀቡቲ ላይ ፈረንሳዮች መግባታቸዉን አይተዉ ቅኝ ግዛት ለመሻማት ነበር።ብሪታንያዎች ሰሜን ሶማሊያን ሙሉ ለሙሉ ለመያዝ ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ፥ ታዋቂዉ የሶማሊያ መሪ ሰይድ ኋላ ሙላሕ መሐመድ አብብደላሕ አል-ሐሰን በሚመሯቸዉ በሶማሊያ ፀረ-ቅኝ ገዢ ሐይላት በተደጋጋሚ ከሽፎባቸዋል።
የለንደን ገዢዎች ተደጋጋሚዉን ሽንፈት ለመበቀል ከተሻሚዎቻቸዉን ከኢጣሊያኖችን፥ ጋር ተወዳጅተዉ፥ ኢጣሊያኖችን አድዋ ድል የመቷቸዉን ኢትዮጵያዉያንን አባብለዉ የሙላሑን ሐይላት ዳግም ገጠሙ።ኮሎኔል ኢ.ጄ ስዋይን የመሩና ያስተባበሩት የብሪታንያ፥የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦር ግንቦት 1901 በሰይድ መሐመድ አብደላ ሐይላት ላይ በሰወስት አቅጣጫ ጥቃት ቢከፍትም በሶማሊያዎቹ ከመሸነፍ አላመለጠም።
ብሪታንያዎች ጥቅማቸዉን ለማስከበር ችግር ሲመጣባቸዉ፥ ከጠላታቸዉ ተወዳጅተዉ፥ ደም የተቃቡ ጠላቶችን አስተባብረዉ የሚፈልጉትን የማስፈፅም ችሎታቸዉን ግን ሶማሊያ ላይ በግልፅ ያስመሰከሩት ያኔ ነበር።ኋላም ለድል በቅተዋል።አሁንም በሶማሊያ ሰበብ የኢትዮጵያና የአሚሶም መሪዎች ግንኙነት ሻክሯል።የናይሮቢና የሞቃዲሾ መሪዎች ወዳጅነትም ወይዘሮ አኔተ ቬበር እንደሚሉት ወደ ግጭት እያመራ ነዉ።
«አዎ ሶማሊያ ዉስጥ ትልቅ ፖለቲካዊ ሥኬት አይታይም።በኬንያና በሞቃዲሾ መንግሥት መካካልም የመጋጨት አዝማሚያ ይታያል።»
ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ ሥለፈለጉ ግን የአዲስ አበባ፥ የአሚሶም መሪዎችም ልዩነት ዉዝግባቸዉን ትተዉ፥ የኬንያዉ ፕሬዝዳትም መከሰስ መጠርጠራቸዉ በይደርን አስቀርተዉ ነገ ከሞቃዲሾ መሪዎች ጋር ለንደን ላይ እኩል ይሰየማሉ።የጉባኤዉ ሒደትና ዉጤት አዘጋጆቹ እንዳሉት የሶማሊያን ችግር ለማቃለል መርዳት አለመርዳቱ በርግጥ ወደፊት የሚታይ ነዉ።
ሶማሊያ በርስ በርስ ጦርነት መዳከር ከጀመረች ወዲሕ ጅቡቲ፥ አዲስ አበባ፥ ካይሮ፥ ናይሮቢ እየተባለ አስራ-ዘጠኝ ጉባኤዎች ተደርገዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ቀዳሚዎቻቸዉ ያሸጉበትን የሶማሊያን «ዶሴ» አዋራ አራግፈዉ ባለፈዉ የካቲት ያዘጋጁት ጉባኤ አዉሮጳ ዉስጥ የተደረገ-የመጀመሪያዉ፥ ለሶማሊያና ለአፍሪቃዉያን ግን ሃያ አንደኛዉ ነበር።
ካሜሩን ሃያ-አንደኛዉን ጉባኤ የሶማሊያን ፋይል ከመዝገብ ቤት ያወጡት ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ከ2009 ጀምሮ ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት እና ሶማሊያ ለሠፈረዉ የአፍሪቃ ጦር፥ በብዙ ሚሊዮነ የሚቆጠር ዶላር ካፈሰሱ በሕዋላ ነዉ።አሸባሪዎችንና የባሕር ላይ ወንበዴዎችን የሚወጋ ጦር፥ አደን ባሕረ-ሠላጤና ጅቡቲ ላይ ካሠፈሩ በሕዋላ ነዉ።
ብሪታንያ ባዶም ቢሆን ኤምባሲ የከፈተችዉ፥ለሁለተኛ ጊዜ ለነገ-ጉባኤ የጠራችዉ ደግሞ የሶማሊያ ቅምጥ የተፈጥሮ ሐብት ከፍተኛነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነዉ።አረቦች፥ ኢራኖች፥ ቱርኮች ሞቃዲሾ ዉስጥ እግራቸዉን ከሰደዱ በሕዋላ ነዉ።የለንደኑ ወኪላችን ድል ነሳ ጌታነሕ ከዚሕ ቀደም እንዳለዉ ቻይኖችን አካባቢዉን በሚያማትሩበት ወቅት ነዉ።
ዓለምን ረስታ፥ በምዕራቡ ዓለም ተረስታ በርስ በርስ ጦርነት ስትወደም ከሃያ-ዓመት በላይ ያስቆጠረችዉ ሶማሊያ የሐያሉን ዓለም ትኩረት ማግኘቷ በርግጥ ጥሩ ነዉ።ጥሩዉ ትኩረት ለሶማሌዎች እንዲጠቅም የሶማሊያ ፖለቲከኞችና የልብ ደጋፊዎቻቸዉ ደቡብ ሶማሊያ፥ ሶማሊላንድ፥ ፑንትላንድ፥ ወዘተ እየተባለ አራት ቦታ የተሸራረፈችዉን ሐገር ማቀራረብ፥ የዉጪዉን ግፊት በዘዴ እያለፉ ከጠመንጃዉ ዉጊያ ጎን ለጎን ድርድርን እንደአማራጭ ለመከተል ቢዘይዱ የተሻለ ዉጤት ማምጣቱ አይገድም።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ