1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ቀውስ፡ የዘር ማጥፋት አደጋዉ ጠንክሯል

ቅዳሜ፣ ሰኔ 1 2016

እየተባባሰ ባለዉ የሱዳን ቀዉስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተገድለዋል። በሃገሪቱ የሚገኙ ተዋጊ ቡድኖች ለሰላም ብዙም ፍላጎት ያላቸዉ አይመስልም። የተመድ እና ግብረሰናይ ድርጅቶች በጋር ይፋ ባደረጉት መግለጫ “በሱዳን ለሚኖሩ ጠኔ አፋፍ ላይ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጊዜው አሳሳቢ እና እያበቃ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4go0L
 ባለሙያዎች RSF ሰሜን ዳርፉር፤ ኤል ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠረ አገሪቱ ይከፋፈላል ይላሉ
ባለሙያዎች RSF ሰሜን ዳርፉር፤ ኤል ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠረ አገሪቱ ይከፋፈላል ይላሉምስል Ebrahim Hamid/AFP

የሱዳን ቀውስ፡ የዘር ማጥፋት አደጋ ፍራቻዉ ጠንክሯል

የሱዳን ቀውስ፡ የዘር ማጥፋት አደጋ ፍራቻዉ ጠንክሯል
እየተባባሰ ባለዉ የሱዳን ቀዉስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተገድለዋል።  ዛሬም በሃገሪቱ የሚገኙ ተዋጊ ቡድኖች ለሰላም ብዙም ፍላጎት ያላቸዉ አይመስልም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች በያዝነዉ ሳምንት በጋር ይፋ ባደረጉት መግለጫ “በሱዳን ለሚኖሩ ጠኔ አፋፍ ላይ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጊዜው አሳሳቢ እና እያበቃ ነዉ። ህዝብ ከፍተኛ እርዳታ ቢያስፈልግም ረድኤት ሰራተኞቹ ላይ በግጭቱ አካላት ሆነ ተብሎ በሚሰነዘርባቸዉ ስልታዊ እንቅፋት እና ክልከላዎችን እየተጋፈጡ በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከአንድ ዓመት በላይ በሆነዉ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ሀገሪትዋ ተከፋፍላ ትገኛለች።  

የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከያ ከፍተኛ ኮሚሽነር፤ አሊስ ንዴሪቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ደኅንነት ምክር ቤት ባቀረቡት መግለጫ፤ በዳርፉር ክልል በሚፈጸመው አመፅ "ሲቪሎች በቆዳቸው ቀለም እና በብሔራቸው ምክንያት ጥቃት ይይፈፀምባቸዋል፤ ይገደላሉም። ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ዘመቻ መጠን ሊኖረው ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።  

ድንበር የለሹ የሃኪሞች ድርጅት ተመሳሳይ አስተያየት እንዳለዉም አስታዉቋል። የድርጅቱ የፕሮግራም ዳይሬክተር ክሌር ኒኮሌት "ደም መፋሰስ እንዴት እየተፈጸመ እንደሆን በዓይናችን እያየን ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ድንበር የለሹ የሃኪሞች ድርጅት ከሆነ በኤል ፋሸር ከግንቦት ወር ወዲህ ብቻ ቢያንስ 145 ሰዎች ተገድለዋል፤  ከ700 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሱዳን ዳርፉር በሚታየዉ ከፍተኛ ዓመጽ ምክንያት የእርዳታ ድርጅቶች ስራቸዉን ሊሠሩ አልቻሉም። 


በኤል ፋሸር የሚታየዉ አስቸጋሪ ሁኔታ

በተለይ የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በኤል ፋሸር ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ትርፋማ ያልሆነዉ የጀርመኑ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን መድረክ ፕሬዚዳንት ማሪና ፔተር ተናግረዋል። በጦርነት ተፈናቅለዉ የመጡ ሱዳናዉያን የሚገኙባት ኤል ፈሽር ከተማ፤ በአሁኑ ወቅት በአብደል ፋታህ አል-ቡርኃን በሚመራዉ፤ በመደበኛው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች  (SAF) የተያዘ ነዉ።  በተመሳሳይ ከተማዋ በመሓመድ ሓምዳን ዳግሎ በሚመራዉ፤   የ(RSF) ተከባለች፤  በተደጋጋሚም ጥቃት ይሰነዘርባታል።

«በአሁኑ ወቅት የዳርፉር መዲና በኤል ፋሸር የሚደረገው ትግል፤ ትልቅ ችግር ሆኖብናል። የተዋጊ ቡድኖቹ የትግል ሁኔታ ይቀያየራል። እናም ትልቁ ፍርሃታችን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች  ኤል ፋሸርን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ በእርግጥም ከፍተኛ የስደተኞች ማዕበል ይከሰታል።  በከተማዋ ከገቡ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ወድያዉ ይጨምራል። ይህን ሌሎች ከተሞችን በተቆጣጠሩበት ወቅት ያየነዉ ነዉ። ትንሽ ገንዘብ ያላቸዉ ከተማዋን ለቀዉ ይወጣሉ። ገንዘብ የሌላቸውን ደግሞ ይጨፈጨፋሉ»  

በመሓመድ ሓምዳን ዳግሎ በሚመራዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል
በመሓመድ ሓምዳን ዳግሎ በሚመራዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልምስል Mohamed Babiker/Photoshot/picture alliance

ነዋሪዎች የ ሓምዳን ዳግሎ የሚመራዉን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች  እንዲከተሉ ለማሳመን የሚደረግ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እየተፈጸመ መሆኑን እንደሚያምኑ ማሪና ፔተር አክለዋል። ኤል ፋሸር በመሠረቱ የ RSF የመጨረሻ ኢላማ ነዉ ያሉት የሱዳንና ደቡብ ሱዳን መድረክ ፕሬዚዳንት ማሪና ፔተር ፤ ይህ ቢሳካላቸዉ ግን ከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀዉስ የሚከሰትበት እና ሱዳንን ለሁለት የሚከፍል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። 

አንድ ዓመት ያለፈዉ የሱዳኑ ጦርነት
ዓለም አቀፉ የቀዉስ አጥኚ ቡድን፤ ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ (ICG) ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት ሁለቱም ወገኖች ከአካባቢው ሚሊሽያዎች ጋር ኅብረት በመፍጠር ላይ ናቸው። የጭካኔ ድርጊታቸዉ ምናልባትም ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ከጊዜ ጋር ግፊት ዉስጥ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል። ጦርነቱ ረዘም ላለ ጊዜ በቆየ መጠን ቡድኖቹ ከሌሎች ሚሊሺያዎች ጋር የሚያደርጓቸዉ ጥምረቶች ሁሉ ዘላቂ ላይሆኑ ይችላሉ። ፤ እንደ ዓለም አቀፉ ቀዉስ አጥኚ ቡድን "የሱዳን ግጭት ሃገሪቷን በመፈራረስ አደገኛ እና አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ገብቷል"።
ከዚህም በላይ ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ከዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው ጋር ባላቸዉ ኅብረት እንዲተማመኑ እና የልብ ልብ እንዲሰማቸዉ ተጨማሪ ምክንያት ሆንዋቸዋል። ለምሳሌ የሱዳን ጦር አዛዥ አል-ቡርኃን በቅርቡ ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ከዚህ ዲፕሎማሲ ማንሰራራት ጀምሮ የሱዳን ጦር በተቃዋሚዎቹ ላይ የጦር አውሮፕላኖችን ጨምሮ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሯል። ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያም ቡርኃንን በግልፅ ይደግፋሉ። ስለዚህም ጀነራል አል ቡርኃን ሁኔታዉ ከባድ ቢሆንም እራሳቸዉን የሀገሪቱ ጠንካራ ሰው አድርገዉ ማቅረባቸዉን ቀጥለዋል።    

ለሱዳን ጦርነት ለምን መፍትሄ ታጣ
በሱዳን ስለላዉ ጦርነት በቅርቡ የትንታኔ ጽሑፍቸዉን ይፋ ያደረጉት በጀርመን ዓለም አቀፍ እና የአካባቢ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ሃግር አሊ፤ ግብፅና ሱዳን በፖለቲካ ብሎም በርዕዮተ ዓለም የተሳሰሩ ናቸው። «ግብፅና ሱዳን በፖለቲካ ይሁን በርዕዮተ ዓለም የተሳሰሩ ናቸው። የአል-ቡርኃን ፖሊሲዎች እና የግብፅ መንግስት ወግ አጥባቂ ባህሪ ተመሳሳይነት ያላቸዉ ናቸዉ። ከዚህም ሌላ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች  የመንግስት ተዋናዮች ባለሞሆናቸዉ ብቻ ግብፅ አብራቸዉ አትሰራም።» 

እንደ ፖለቲካ ተንታኝዋ ሃግር አሊ፤ ከዚህ አንፃር የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጀነራል መሐመድ ሓምዳን ዳጋሎ፤ ከጊዜ ወደጊዜ ራሳቸዉን የነፃነት ታጋይ እንደሆኑ አድርገዉ እያቀረቡ ነው። በዚህም ምክንያት ዳጋሎ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ድጋፍ አግኝቷል። ሩሲያም ብትሆን በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ከጎናቸው መሆንዋን የፖለቲካ ተንታኝዋ ተናግረዋል። 

«የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶችም ሆነ ሩስያ በአፍሪቃ ያላቸውን ተሰሚነት ለማስፋት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ሁለቱም ሀገሮች በሱዳን የወርቅ ክምችት ላይ አንድ አይነት ፍላጎት አላቸው። ይህን ፍላጎታቸዉን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ከሆኑ እንደ ሓምዳን ዳጋሎ አይነት ተዋናዮች ጋር በመተባበርና የባለስልጣናትን በሮች በተዋናዮች በመዝጋት ነዉ።»
እንደ አሶሽየትድ ፕሬስ የዜና አገልግሎት ዘገባ፤ ሩሲያ በፖርት ሱዳን የሎጂስቲክስ ማዕከል ለመገንባትና ማዕከሉን ወደ ባሕር ኃይል ለማስፋፋት እቅድ ይዛለች። ሩስያ ምንም እንኳ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች  ጋር የቀጥታ ግንኙነት ቢኖራትም፤ ባለፈዉ ሚያዝያ ወር መጨረሻ የሩሲያ መልእክተኞች ስለሩስያ እቅድ ለመወያየት ከሱዳን ጦር ዋና አዛዥ አል ቡርኃን ጋር ተገናኝተዋል። በዘገባዉ መሰረት ሩሲያ ለሱዳን የጦር መሣሪያና ወታደራዊ ቁሳቁስንም ትሰጣለች። በዚህም ይላሉ ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝዋ ሃግር አሊ፤ በዚህም ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ለሱዳን መፍትሄ እንዲገኝ ያላቸዉ ፍላጎት አነስተኛ ነዉ። 

በካርቱም አቅራቢያ የነበረው የኦምዱማን ገበያ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ መካከል ከተካሄደ ከባድ ውጊያ በኋላ ወድሟል
በካርቱም አቅራቢያ የነበረው የኦምዱማን ገበያ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ መካከል ከተካሄደ ከባድ ውጊያ በኋላ ወድሟልምስል ohamed Khidir/Xinhua/picture alliance

«በሱዳን ምንም አይነት ሥራን የሚያከናውኑ ተቋማት አለመኖራቸዉ ለሃገራቱ ተስማሚ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ይህ ደግሞ በቀላሉ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ለማቋቋም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ያለምንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በቀላሉ ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው ዳርጓል። በአሁኑ ወቅት በሱዳን እንደሚታየው፤ መደበኛ ባልሆነና በድብቅ በሚተላለፉ መንገዶች የጦር መሣሪያዎች ወደ ሱዳን ይገባሉ።  በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ያልተረጋጋችን ሃገር ከመቆጣጠር በቀር ለዘላቂ ሰላም እምብዛም ፍላጎት የላቸውም። ሱዳን ለሁሉም ሀገሮች የቀይ ባህር መዉጫ አልያም ከቀይ ባህር ወደ አፍሪቃ መግቢያ በርም ናት።» 


ክርስቲን ክኒፕ / አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ