1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 1 ቀን 2016ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaቅዳሜ፣ ሰኔ 1 2016

https://p.dw.com/p/4gp5N

 

በአማራ ክልል የሁለት ወረዳ አስተዳዳሪዎች በታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት ተገደሉ ።

ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ቀናት ደረሰ በተባለው ጥቃት የተገደሉት ባለስልጣናት  የኤፍራታ ግድም እና የቀዌት ወረዳ አስተዳዳሪዎች ናቸው ።

ጥቃቱን በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ቡድን ሳይሆን እንዳልቀረ ከአካባቢው ባለስልጣናት በተለያዩ ቀናት የተሰጡ መግለጫዎችን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ጥቃቱ ግንቦት 25 እና 28 2016 መፈጸሙንም ዘገባው አመልክቷል። ስለጥቃቱ ከፌዴራልም ሆነ ከክልል መንግስታት የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም። የፌዴራሉ መንግስት በአማራ ክልል እና አንደአስፈላጊነቱ በተቀረው የሀገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆነው እና ለ10 ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ ቢያበቃም መንግስት በይፋ ስለማብቃቱም ሆነ ስለመቀጠሉ ያለው ነገር የለም።

 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የታሰሩትን ከእስር መፍታትን ጨምሮ መንግስት ወደ መደበኛ የህግ ማስከበር » እንዲመለስ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በአማራ ክልል የልዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ መወሰኑን ተከትሎ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የፋኖ እና በመንግስት ኃይሎች መካከል የሚደረገው ዉጊያ አንድ ዓመት ገደማ ሲያስቆጥር መቋጫ ሳያገኝ በክልሉ በርቱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዳስከተለ ቀጥሏል።

 

አሜሪካ በሱዳን ከ100 በላይ ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት የፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ተጠያቂ አደረገች ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ በሰሜናዊ ካርቱም ባልታጠቁ ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጅምላ ግድያ « አሰቃቂ» ነው ብሏል። 35 ህጻናትን ጨምሮ ከ100 በላይ በላይ ሲቪላዊያን በተገደሉበት በዚሁ ጥቃት በርካቶች መቁሰላቸው ተሰምቷል። በጥቃቱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ተጠያቂ ያደረገችው አሜሪካ  « በመላው ሱዳን ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት በአስቸኳይ መቆም አለበት ብላለች።

 ጥቃቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቃባይ ማቲው ሚለር «በዚህ ሁኔታ ምንም አይነት ወታደራዊ ድል ሊገኝ አይችልም ፤ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ንግግር » መጀመር አለበት ብለዋል። 

ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ከሚመሩት የሱዳን ቤሔራዊ ጦር ጋር ከአንድ ዓመት በላይ እየተዋጋ የሚገኘው የጄኔራል አምዳን ዳጋሎው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ባለፈው ረቡዕ በአልጃዚራ ግዛት የምትገኘው የዋድ አል ኖራ መንደር በከባድ መሳሪያ ማጥቃታቸውን የሱዳን የማህበራዊ አንቂዎች ቡድን አስታውቋል። አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ተፋላሚ ኃይላቱን ለማደራደር ያደረጓቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል።

 

በምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በትንሹ አስር ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የአካባቢው ባለስልጣናት እና የሲቪል ማህበራት አስታወቁ ።

ታጣቂዎቹ ትናንት ምሽት በሰሜናዊ ኪቩ ግዛት የምትገኝ ማሳላ በተሰኘች መንደር ላይ ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።  ለጥቃቱ ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ጥቃት በማድረስ ለ16 ሰዎች ህልፈት ተጠያቂ የተደረገው የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥምረት የተሰኘው ጽንፈኛ ቡድን ኃላፊነት እንደሚወስድ ሮይተርስ ያነጋገራቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ነገር ግን ታጣቂ ቡድኑ በሁለት ሳምንት ውስጥ በተከታታይ ለደረሱ ጥቃቶች በይፋ ኃላፊነት አልወሰደም። መነሻውን ከዩጋንዳ እንዳደረገ የሚነገርለት የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥምረት (ADF) በምስራቃዊ ኮንጎ እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም የሚል ዓላማ አንግቦ በተደጋጋሚ በሚያደርሳቸው ጥቃቶች በርካቶችን ለህልፈት እና ለመፈናቀል ዳርጎ አካባቢው እንዳይረጋጋ አድርጓል።

 

የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ አራት እስራኤላውያን ታጋቾች ማስለቀቁን አስታወቀ።

ጦሩ በህይወት ያሉ ታጋቾች በኃይል ሲያስለቅቅ በጋዛ ሰርጥ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ጦሩ በጋዛ አል ኑሰሪያት በከፈተው ወታደራዊ ዘመቻ በህይወት ከታደጋቸው ታጋቾች በተጨማሪ የሟች ታጋቾችን አስክሬን ማግኘቱንም አስታውቋል። ጦሩ በኅይወት የታደጋቸው ታጋቾች ዕድሜያቸው የ21፣ 25 ፣27 እና 40 የሆኑ አንዲት ሴት እና ሶስት ወንዶች ናቸው። በመስከረም 27ቱ የሃማስ ጥቃት ከሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ እንደተወሰዱ የተነገረላቸው ታጋቾቹ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ህክምና የተወሰዱ ሲሆን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል። እስራኤል እንደምትለው ባለፈው መስከረም 27 ቀን ሃማስ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት 250 ሰዎች ታግተው ሳይወሰዱበት እንዳልቀረ አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ ከሃማስ ጋር በተደረጉ ድርድሮች 112 ሰዎች የተለቀቁ ሲሆን አሁንም ድረስ 80 ያህል ታጋቾች በታጣቂው ቡድን እጅ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል። እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ አጠናክራ በቀጠለችው ወታደራዊ ዘመቻ ሰላማዊ ሰዎችን ያልለየ ነው ሲሉ  ሁነኛ አጋሯ አሜሪካን ጨምሮ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ብርቱ ተቃዉሞ እና ውግዘት አስከትሎባታል። 

 

ምዕራባዉያን ማዕቀባቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉም ሩስያ የዓለም ንግድ ሁነኛ አጋር ሆና ቀጥላለች ሲሉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ ። 

ፕሬዚዳንቱ ሃገራቸው ባስተናገደችው የ27ኛው የሴንት ፒተርስበርግ ዓለማቀፍ የኤኮኖሚ ትብብር መድረክ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው የምዕራባውያን «ህገ ወጥ» ያሉት ማዕቀብ ቢጫንባትም በአቅርቦት እና ዓለማቀፍ ተደራሽነት ተጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል። ሩስያ ጀርመንን በመከተል ከዓለም ቀዳሚ የኤኮኖሚ መሪ ሃገራት ተርታ ተሰልፋለች ያሉት ፑቲን ወዳጅ ካሏቸው ሃገራት ጋር ከአራት ሶስት እጅ የወጭ ንግድ እየተሳለጠ ነው ብለዋል። የምዕራባዉያኑን የተጠናከረ ማዕቀብ ተከትሎም ከቻይና ጋር በተናጥል እንዲሁም ከህንድ አፍሪቃ እና ደቡባዊ አፍሪቃ ጋር ኤኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውn ማጠናከራቸውን አስረድተዋል።  በንግድ ግንኙነቱ ከአሜሪካ ነጻ የሆነ የክፍያ ስረዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። በሩስያ እና ዩክሬን መካከል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለት ዓመት በኋላም ሩስያ በንጽጽር ጠንካራ ኤኮኖሚ ይዛ መቀጠሏን የምዕራባዉያን ባለሞያዎች ትንታኔን ጠቅሶ የጀርመን ዜና ምንጭ ዘግቧል። ባለፈው ረቡዕ ተጀምሮ ዛሬ በተጠናቀቀው ጉባኤ ላይ የታደሙ ሩስያውያን ፖለቲከኞች የንግድ ስራ ፈጠራ ባለሞያዎች ሃገራቸው ለተራዘመ ጦርነት መዘጋጀት እንደሚገባት አሳስበውዋል።  

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።