1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኢትዮጵያ ምጣኔሐብት ምን ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ዓርብ፣ ጥር 2 2017

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ፈቃድ አግኝቶ ለሁለት ዓመታት ያህል የመሠረት ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል። ይህን የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ አስጀምረውታል።

https://p.dw.com/p/4p27k
 የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኢትዮጵያ ምጣኔ - ሐብት ውስጥ መቼ ፣ ምን ዐይነት ተጨባጭ ለውጥ ይዞ ይመጣ ይሆን
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዛሬ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።ምስል Ethiopia Securities Exchange (ESX)

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኢትዮጵያ ምጣኔሐብት ምን ለውጥ ያመጣ ይሆን?

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዛሬ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደወል ደውልናል" ሲሉ ሰዎች በዚህ መስክ ሐብታቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የግል የሥራ መሥክ ክፍት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ይህንን መሠል ሥራ "በዘፈቀደ" ሲመራ ነበር ያሉ አንድ የዘርፉ ባለሙያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ምዝገባ በዘርፉ ተዋናዮች መካከል መተማመንን እና ግልጸኝነትን በመፍጠር ገበያው በሕግ እና ተጠያቂነት ሥርዐት እንዲመራ ያግዛል ብለዋል።ለመሆኑ ይህ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኢትዮጵያ ምጣኔ - ሐብት ውስጥ መቼ ፣ ምን ዐይነት ተጨባጭ ለውጥ ይዞ ይመጣ ይሆን?

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዛሬ ጥር 2 ቀን በይፋ ሥራ ጀምሯል ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የካፒታል ገበያን የሚመራ ሕግም ሆነ ዘርፉን በበላይነት የሚያስተዳድር አካል  አልነበረም።

የግል ዘርፉ የገበያ እንቅስቃሴ ክፍት ሲሆን ደግሞላለፉት 30 ግድም ዓመታት ማለት ነው - በዋናነት የባንክ እና  የኢንሹራንስ የሥራ መስኮች ላይ የአክስዮን ገበያ እንቅስቅልሴ ተጀምሮ ሲሰራበት ቆይቷል።  ባለፉት አራት ዓመታት ግን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተቋቁሞ የአክስዮን ወይም የብድር ሰነዶች የሚሸጡበትና የሚገዙበት አንድ የተማከለ የግብይት ተቋም ማለትም የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ፈቃድ አግኝቶ ለሁለት ዓመታት ያህል የመሠረት ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል። ይህን የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ አስጀምረውታል። 


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን አስመልክቶ "ለኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ምህዳራችን የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደወል ደውልናል" ሲሉ ጽፈዋል። 

ሥራ ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሐብት ምን ያስገኛል?


ይህ የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በምን ያህል ጊዜ እና ኹኔታ ዐወንታዊ አስተዋጽዖ ያበረክት ይሆን? የሚለውን የጠየቅናቸው የፕራግማ ካፒታል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ አማካሪ የሆኑት አቶ መርዕድ ብሥራት ፍቅረ ዮሃንስ "ሥራው ተጀምሯል" ካሉ በኋላ፣ ውጤትም እያመጣ መሆኑን በመጥቀስ ለአብነት ባንኮች የአጭር ጊዜ የገንዘብ ገበያ እንደተፈጠረላቸው፣ በዚህም ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እስከ 1.1 ቢሊዮን ብር መገበያየታቸውን ተናግረዋል።


"የገበያው ሐብት የሚያዝበት በአክስዮን እንኳን ብትመለከተው ወደ አንድ ትሪሊየን፣ ወደ ሁለት ትሪሊየን በጊዜ ሂደት ውስጥ መሄዱ አይቀርም። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በየቀኑ በቢሊዮን ብር ሐብት የሚንቀሳቀስበት ገበያ ነው የሚሆነው።"

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዛሬ ጥር 2 ቀን 2017  በይፋ ሥራውን ጀምሯል
አዲስ አበባ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና መስሪያ ቤት ምስል Solomon Muchie/DW

የሥራው በይፋ መጀመር ይዞት የሚመጣው ነገር 

ነባር የሆኑ የአክሲዮን ድርጅቶች በዚህ ገበያ ውስጥ በይፋ መቀላቀል አለባቸው የሚሉት አቶ መርዕድ ብሥራት ፍቅረ ዮሃንስ አንድ አክስዮን ማህበር ከ50 በላይ ባለ አክስዮኖችን የያዘ ከሆነ እና ማስታወቅያ በማስነገር ከ 100 ሚሊዮን ብር በላይ ከሕዝብ ሐብት የሰበሰበ ይህንን ሰንዶ ማቅረብና ተቆጣጣሪ ባለሥልጣንም መሰል ድርጅቶች እነማን ናቸው የሚለውን ማወቅ ይጀምራል ብለዋል። ይህም ድርጅቶቹን እና ሀብታቸውን ፈሰስ ያደረጉትን ሰዎች መንግሥት በሕግ ከለላ ውስጥ ያውቃቸዋል ማለት ነው በማለት የሚታመን ግልጽ የንግድ ሥራ እንዲስፋፋ ይረዳል ብለዋል። 


"ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ተዐማኒ የሆነ ካፒታል የሚገለባበጥበት ሰው በመተማመን ሐብት ፈሰስ የሚያደርግበትን ገበያ ይፈጥራል።" ብለዋል።

ሥራው መጭበርበርን እና እንግልትንም ያስቀራል - ባለሙያ

በኢትዮጵያ በሕግና በተቋም የሚመራ የአክሲዮን ግብይት ባለመኖሩ ለዚሁ ሥራ የዜጎችን ሀብት በማስታወቂያ  የሚሰበስቡ ተቋማት እምነት አጉድለው ሲጠፉ ተስተውሏል። ምንም እንኳን ሥራው በባንክ እና ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሻለ በጎ ልምድ ያለው ቢሆንም። የፕራግማ ካፒታል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ አማካሪ የሆኑት አቶ መርዕድ ብሥራት ፍቅረ ዮሃንስ "እዚህ ገበያ ውስጥ ትልቁ የሚገዛው፣ የሚሸጠው አመኔታ ነው" ሲሉ ለዚህ ሥራው እንዴት የሕዝብን መጭበርበር እና እንግልት እንደሚያስቀር ገልፀዋል። አክለውም "ነባርና 
አዲስ ካፒታል መሰብሰብ የሚፈልጉት ተማምነው ገበያ ውስጥ በተሟላለት መስፈርት መሠረት ካፒታላቸውን እንዲሰበስቡ ያስችላል" ሲሉ አብራርተዋል።


እንዲህ ያለው አዲስ የሥራ መስክ የአክስዮን ማህበራት የተቋማት ቦርድን ሲያዋቅሩ በትውውቅና በመወዳጀት የሚደርጉትን ሂደት ያስቆማል፣ በዚህ ግብይት ውስጥ የሚሳተፉ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ አማካሪዎች፣ የሕግ ባለሙያ እና ጠበቆች ፣ የሒሳብ ዐዋቂ ባለሙያዎች ላይም  ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ እንዲከናወን ያስችላል ሲሉ ባለሙያው ገልፀዋል።


የካፒታል ገበያ የቁጥጥር መሣሪያዎች ከሚባሉት አሠራሮች አንዱ የሆነው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ባለ ድርሻዌችን ከለላ በመስጠት፣ የግብይት ሥራን ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ ያደርጋል የሚል እምነት የሚጣልበት ነው። ከዚህም አልፎ የግል ዘርፉን ያሳድጋል፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሀብት እድገትን ያመጣል፣ ተጨማሪ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበትን ዕድል ይፈጥራል፣ ቁጠባንም ያሳድጋል የሚል ትንተና ይሰጥበታል።

ባለሙያው ይህ የሥራ ዘርፍ በቀጣይ "በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በየ ቀኑ በቢሊዮን፣ በየ ዓመቱ ደግሞ በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ገበያን ይፈጥራል" ሲሉም ባለሙያው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሶሎሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ