1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ አድጋፍ አቅርቦት ፈተና በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 2015

በርካቶች በተፈናቀሉባት የአሙሩ ወረዳዋ አገምሳ ከተማ እና በምስራቅ ወለጋ በርካቶች በተፈናቀሉባት ኪረሙ ወረዳ በቂ የእርዳታ አቅርቦት የለም፡፡ መንገድን ጨምሮ የመሰረታዊ ማህበራዊ መገልገያ አውታሮችም በበቂ ሁኔታ አገልግሎት አለመስጠታቸው የእለት ተእልት ኑሮያቸውን ፈትኖ ለእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ማስገደዱን አክለው ያነሳሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4UU6Q
Äthiopien | Dürre
ምስል Claire Nevill/WFP/AP Photo/picture alliance

የፀጥታ ችግር ለርዳታ አቅርቦት ተጨማሪ እንቅፋት ነዉ

                                               
ኢትዮጵያ ዉስጥ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ከየቀያቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በዕርዳታ እጥረት መስተጓጎሉን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ ) አስታወቀ፡፡ድርጅቱ ትናንት ረቡዕ ባወጣው ዘገባ እንዳለዉ የሚገኘዉንም ርዳታ በተለይ ግጭት  በሚደረግባቸዉ እንደ ምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ አከባቢዎች  ለሰፈሩ ተፈናቃዮች ማድረስ እያዳገተ ነዉ።
የጎርጎሳውያኑ 2023 ከገባ ወዲህ በኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ተፈናቅለው የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር 4.5 ሚሊየን እንደሚገመቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ (UN-OCHA) ሰሞነኛ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ዕቅድ ከተያዘው የፈረንጆች ዓመት ማለትም ከጥር ወር ወዲህ በድርቅ፣ ጎርፍ እና የጸጥታ ችግር ምክኒያት በተጨማሪነት ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ መኖራቸውን ይጦቁማል፡፡
ተቋሙ በዚሁ አሁናዊ ሪፖርቱ በሰኔ ወር ብቻ በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች ከ24 ሺህ አባወራ በላይ ወደ መኖሪያ ቀዬያቸው መመለሳቸውን ግን በአዎንታዊ ጎኑ አንስቷል፡፡ 
ይሁንና በትግራይ ብቻ አንድ ሚሊየን ተፈናቃዮች መኖራቸውን ያመለከተው ተቋሙ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ያቆመው ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ 800 ሺኅ ገደማ ዜጎች ወደ ቄያቸው ቢመለሱም አሁን ላይ ያለው የእርዳታ አቅርቦት እጥረት ሂደቱን መግታቱን ነው ያሳወቀው፡፡ ወደ ቄየያቸው የተመለሱም ቢሆን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ሚያስፈልጋቸው ናቸው ብሏል ሪፖርቱ፡፡
580,0000 የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙበት አማራ ክልልም ከዚህ በፊት 360 ሺኅ ገደማ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ብቻልም፤ አሁን ያጋጠመው የምግብ፣ መጠለያ፣ ውሃ እና ንጽህና ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን ፈትኗል ተብሏል፡፡ 
እንደ ሪፖርቱ በአፋር እና ሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥሟል፡፡ በሌላ መልኩ በኦሮሚያ በተለይም ግጭት በሚስተዋልባቸው አራቱ የወለጋ ዞኖች (ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቄሌም ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ) እንደ ትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች ተስተጓጉሏል ያለው OCHA በነዚህ አከባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ የእርዳታ አቅርቦቱንም ማስተጓጎሉን አመልክቷል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ጎቡ ሳዮ እና ዋዩ ቱቃ ወረዳዎች ብቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት 13 ሺህ 800 ገደማ ዜጎች ለሁለተኛ ጊዜ ተፈናቅለው በመጠለያ እንደሚገኙ ሪፖርቱ በማሳያነት አንስቷል፡፡  
ዶይቼ ቬለ ከምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ ያነጋገራቸው ዜጎችም ከየገጠር አከባቢዎቹ ያፈናቀላቸው የፀጥታ ሁኔታ ለከፋ የድጋፍ ፍላጎት እንደዳረጋቸው ይገልጻሉ፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት በርካቶች በተፈናቀሉባት የአሙሩ ወረዳዋ አገምሳ ከተማ እና በምስራቅ ወለጋ በርካቶች በተፈናቀሉባት ኪረሙ ወረዳ በቂ የእርዳታ አቅርቦት የለም፡፡ መንገድን ጨምሮ የመሰረታዊ ማህበራዊ መገልገያ አውታሮችም በበቂ ሁኔታ አገልግሎት አለመስጠታቸው የእለት ተእልት ኑሮያቸውን ፈትኖ ለእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ማስገደዱን አክለው ያነሳሉ፡፡
ስለነዋሪዎቹ እሮሮ ምላሽ እንዲሰጡን ለክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ሃብታሙ ሲሳይ እና ለተቋሙ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በጽሁፍና ስልክ ጥሪ ጥያቄ ብናቀርብም ለዛሬ ምላሻቸውን ማግኘት ባለመቻላችን አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙ አቶ አታለል አቦሃይ እንደሚሉት ግን መንግስት ቅድሚ ድጋፍ የሚሻቸውን እየለየ ድጋፍ የማድረጉን ጥረት እያከናወነ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ 200 ገደማ ወረዳዎች ለጎርፍ ተጠቂ ናቸው፡፡ ይህ በራሱ 1.5 ሚሊየን ገደማ ህዝብን አጥቅቷል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ቅድም ተከተል አውጥተን እንደ ችግሩ አሳሳቢነት ደረጃ ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡”
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ሪፖርትም በኢትዮጵያ በክረምቱ የ1.5 ሚሊየን ዜጎች ህይወት በጎርፍ ስጋት ላይ ነው ይላል፡፡ 
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚዩኒኬሽን ተወካዩ አቶ አታለል እንደ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ያሉ ዓለማቀፍ የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ድጋፍ መግታታቸው ፈተናውን ማባባሱን ገልጸው፤ መንግስት ግን የሚፈጠረውን ክፍተት በተለያዩ መንገዶች ለመድፈን እየጣረ ነው ብለዋል፡፡ “4 ሚሊየን ገደማ ዜጎችን ለመርዳት የተለያዩ ድጋፎችን በዚህ ሳምንት እንኳ ማንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ ማቋረጥ ተጽእኖው ቀላል አይደለም፡፡ ይሁንና መንግስት ሌሎች አማራጮችንም እየተመለከተ ነው፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በቅርቡ የሰጡት የ5.5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ከዚህ አንጻር ተጠቃሽ ነው፡፡”
አቶ አታላይ ከዚህ በፊት የእርዳታ እህል ለስርቆት እንዲዳረግ ከፍተት ያሳዩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ በመንግስት የተዋቀረው ስራ የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑነንም ጠቁመዋል፡፡

Äthiopien Mekelle | WFP Nahrungsmittellager
ምስል Million H. Silasse/DW
Symbolbild Äthiopien Ankunft des Konvois mit Hilfslieferungen in Tigray
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ