የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ምርጫና ተቃውሞ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2005ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባልነት የሚካሄዱ ፉክክራቸው የተገደበ ምርጫዎች የመንግሥታቱ ድርጅት ለምክርቤቱ አባልነት ላስቀመጣቸው ደረጃዎች ትኩረት ያልሰጡ ናቸው ሲል ሂዩመን ራይትስ ዋች ወቀሰ ። አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩመን ራይትስ ዋች በምክርቤቱ የምርጫ ስርዓት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈፅሙ ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ የአፍሪቃ ሃገራት በአባልነት መመረጣቸውን በፅኑ ተቃውሟል ። የድርጅቱን የ ጂኒቫ ቢሮ ሃላፊ ያነጋገረችው ሂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች ።ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ክፍት መቀመጫዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት በተካሄደ ምርጫ ከአፍሪቃ ከእስያ ና ከላቲን አሜሪካ ቡድን በሰብአዊ መብት ጥሰት በሚከሰሱ አገራት ጭምር መያዛቸው እያነጋገረ ነው ። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች በአብዛኛዎቹ ክፍለ አለማት ቡድኖች አስቀደሞ የተወሰነና የተዘጋጀ የሚሉትን የምርጫ ስርዓት አውግዘዋል ። የሰብአዪዊ መብት ተሟጋቹ የሂዩመን ራይትስ ዋች ይህ አይነቱ አሰራር እንዲስተካከል አሳስቧል ። የጂኔቫ ቢሮ ሃላፊ ጁሊ ደ ሪቬሮ የነዚህ ቡድኖች የምርጫው ሂደት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤን መስፈርት ይፃረራል ይላሉ ። « የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለተመድ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባልነት ምርጥ የሚባለውን ተወዳዳሪ መምረጥ ይኖርበታል ። ምክር ቤቱ ሲመሰረት የአባላት መመዘኛ ምርጥ የምክር ቤት አባላት በሰብአዊ መብት ምክር ቤት ውስጥ እንዲወከሉ ማድረግ ነው ። ይሁንና እንዳለ መታደል ሆኖ በአፍሪቃ በላቲን አሜሪካ በምሥራቅ አውሮፓና በእስያ የተወዳዳሪዎቹና የክፍት ቦታዎቹ ቁጥር እኩል ነበር ። ያ ማለት እጩ ሆነው የቀረቡት ሃገራት እንደሚመረጡ እርግጠኛ ነበሩ ። በዚህ የተነሳም ፉክክር አልተካሄደም ምርጫም አልነበረም ።
በአፍሪቃው ቡድን በተካሄደ ምርጫ አይቮሪ ኮስት ኢትዮጵያ ጋቦን ኬናያና ሲራልዮን ያለተፎካካሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መቀመጫዎች አግኝተዋል ። ሂዩመን ራይትስ ዋች እንደሚለው በአፍሪቃው ቡድን በተካሄደው በልማዳዊው የዙር ሥርዓት ምርጫ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ድርጅቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሳቸው አገራት ለመመረጥ ያበቃቸው ፉክክር አለመኖሩ ነው ። ጁሊ ደሪቬሮ
« በርከት ያሉ ተወዳዳሪዎች መቅረብ አለባቸው ። ያ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብአዊ መብት በተሻለ ሁኔታ ሰብአዊ መብትን የሚያከብሩትን ለመምረጥ ይቻላል ። በአሁኑ ሁኔታ ግን ያ አልነበረም ። እንደ ኢትዮጳያ ያለች ሲቪል ማህበራቷን የምትጨቁን ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች በሰብአዊ መበቶች ላይ መሥራት በማይችሉበት ሃገር የሰብአዊ መብት ቢጨቆንም መቀመጫ ማግኘት ችላለች ። »
ለዚህ መፍትሄው ጁሊ ደ ሪቬሮ እንደሚሉት በርከት ያሉ ሃገራትን በተወዳዳዳሪነት ማቅረብ ነው ። ለምሳሌ ከምዕራባውያኑ ሃገራት ቡድን 5 ሃገራት ለ3 መቀመጫ ተወዳድረው በምርጫው ዩናይትድ ስቴትስ ጀርመንና አየርላንድ ሲያሸንፉ ግሪክና ስዊድን መቀመጫ አላገኙም ። በሰብአዊ መብት ጥሰት ስማቸው የሚነሳ ሃገራት በሰብአዊ መብት ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ የመያዛቸውን አጋጣሚ በመጠቀም የሃገራቸውን የሰብአዊ መብት ይዞታ እንዲያሻሽሉ ኢትዮጵያን በምሳሌነት በማጥቀስ ግፊት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
« ዋናው ቁም ነገር እዚህ ላይ አሁን መመረጣቸው የሰውን ልጅ መብት በከፍተኛ ደረጃ ያከብሩ ዘንድ የሚላኩበትን ሁኔታ ፈጥሯል ። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሃገር አሁን የምክር ቤት አባል ሆናለች ። ስለዚህ የሰብአዊ መብት ይዞታዋን ማሻሻል አለባት ። በምክር ቤቱ መቀመጫ መያዝ እንደሚገባት ማሳየት አለባት ። እኛም በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ የፀዳ እንዲሆን ክትትል ና ግፊት ማድረግ አለብን ። »
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ