1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ግንቦት 18 2015

«ምክረው ምክረው እንቢ ካለ መከራ ይመክረው የሚለው አባባል ሲገባቸው ተመልሰው ተስማምተዋል ከዚህ ጥፋት መማር አለባቸው» «እነሱስ አይደለም 1.5 ትሪሊዬን ፣ 1ብር ከሀምሳ ሳንቲም የጠፋባቸውም አይመስሉም» «ሀገሪቱንና ህዝቡን ለዚህ ችግር የዳረጉት ተጠያቂ መሆን አላባቸው ።»

https://p.dw.com/p/4RsPQ
Fürst Alemayehu Tewodro
ምስል Äthiopisches Außenministerium

የግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የ9 ወር ዘገባ በዚህ ሳምንትም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።የኤርትራ 30ኛ ዓመት የነጻነት በዓል እንዲሁም የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል ዓለማየሁ አጽም ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ የሚቀርበውን ጥያቄ የበኪንግሀም ቤተመንግሥት ውድቅ ማድረጉም ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ናቸው።  
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ሀገሪቱ 28 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት በአሁኑ የውጭ ምንዛሪ 1.5 ትሪሊዮን ብር ኪሳራ ማድረሱን አስታውቀዋል። በሪፖርቱ ጦርነቱ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ለከፋ ድኅነት እንደተዳረጉም ተጠቁሟል። 
ከማል ዑመ« ጉዳቱ ከዚህ ቢበልጥ እንጂ አያንስም ። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ሊማር ይገባል ሲሉ በፌስቡክ አሳስበዋል። «ይኸው ኣሻፈረን ብለን መከራ መከረን» ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት አባተ ፉላስ ቀለቻ «ከዚህ ተምረን ከአሁን በኋላ ልዩነትን በምክክር እና ውይይት ብቻ እንድንፈታ ፈጣሪ ቅን ልቡና ይስጠን !» ብለዋል። ወንድይፍራው ይስማውም «ምክረው ምክረው እንቢ ካለ መከራ ይመክረው የሚለው አባባል ሲገባቸው ተመልሰው ተስማምተዋል ከዚህ ጥፋት መማር አለባቸው» ሲሉ በላይ ዘለቀ ደግሞ «እነሱስ አይደለም 1.5 ትሪሊዬን ፣ 1ብር ከሀምሳ ሳንቲም የጠፋባቸውም አይመስሉም!! በማለት ትዝብታቸውን አጋርተዋል። በለጠ ካሳ ኃይለ ማርያም በፌስቡክ  ሀገሪቱንና ህዝቡን ለዚህ ችግር የዳረጉት ተጠያቂ መሆን አላባቸው የሚል መልዕክት በፌስቡክ አስፍረዋል ።
«የሀገሪቱን ሕዝብ ወደ ከፋ ድህነት የከተቱት የፌደራልና የክልሎቹ የፓለቲካ ሀላፊዎች በሕግ መጠየቅ ነበረባቸው ለሌላም ግጭት ጦር ባይሰብቁ ጥሩ ነበር።» ካሉ በኋላ «ከዚህም ሌላ ለስልጣን ያላቸዉን ፍቅር ወደጎን በመተው፣ ለሀገሪቱ ሰላምና ልማት ሲባል ሁሉን ያሳተፈ ብሔራዊ እርቅና እዉነተኛ የዲሞክራሲ ግንባታን የሚያፋጥኑ ገለልተኛ ተቋማት ለመመስረት ይጥሩ ነበር።በማለት ሰላማዊ መፍትሄ ሊሆን ይገባ ነበር ያሉትን አቅርበዋል። 
መዓዚ የድንግል በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ ከሁሉም ይለያል። «ዝም ብለን የፈጣሪን ቀን ነው ኢትየጵያዊያን እየጠበቅን ያለነው እንጂ ምንም አስተያየት አንሰጥም»የሚል ነው።
«የገንዘብ ሚንስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ የስው ልማት ሚንስትር ቢኖር በጦርነቱ የምን ያህል ዜጋ ህይወት እንደጠፋ አርድተውን ቢሆን ጦርነቱን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እርም ባልን ነበር። ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት የያሬድ ማኅበረሰብ ድምጽ ደግሞ ጦርነት ሲያበቃ እንጂ ሲጀመር የፍየል ወጠጤ እየተዘመረ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ቀላል ስላልሆነ ምን ያህል የስው ህይወት እንደሚያጠፋ ፣ የሀገር ሃብት እና ንብረት እንደሚያወድም በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ግምት ውስጥ አይገባም  ከጦርነት ጀርባ ልማት ያለ የሚመስለን ጥቂቶች አይደለንም።» በማለት ስለጦርነት የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው ላሏቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 
አህመድ በላይነህ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ ያለፈው ብቻ ሳይሆን አሁን ይደርሳል ያሉት ጥፋትም ለምን አይታሰብበትም ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል « ባለፈው መጸጸት ብቻ በቂ አይደለም ሲሉ ሃሳባቸውን የጀመሩት አህመድ «አሁንም በቤት ፈረሳ እና በየአካባቢው ጠርነቱን ለማቆም ለምን ማሰብ አቃታቹህ? የሚል ። ቴዲ ገብረ እግዚአብሔር እባካችሁ ያለፈውን እርሱና እንዴት ወደፊት እንደምንራመድ አመልክቱን ብለዋል።
ብሩክ ታደሰ ደግሞ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የሚካሄደው ጦርነትስ ሲሉ ጠይቀዋል። 
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ነፃነትዋን  ያወጀችበት 30ኛ ዓመት በዓል እንዲሁም የቀድሞዉ የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አዉጪ ግንባር (EPLF) ወይም ሻብዕያ የኢትዮጵያ መንግስት ጦርን ድል አድርጎ ዋና ከተማዋን አስመራን የተቆጣጠረበት 32 ተኛ ዓመት  ከትናንት በስተያ ተከብሯል። በዓሉ በኤርትራና ኤርትራውያን በሚገኙባቸው የተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል። በእለቱ ለነጻነት በተካሄደው ውጊያ የሞቱ ወገኖች ታስበዋል። የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች፣ የፖለቲካ አቀንቃኞችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ኤርትራን ከነፃነት ጊዜ ጀምሮ የሚገዙት የቀድሞዉ የአማፂ ቡድን መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ሐገሪቱን ለድሕነት፤ሕዝቡን ለመከራና ስደት ዳርገዉታል። ስዊድናዊ-ኤርትራዊቱ የመብት ተሟጋች ሜሮን እስጢፋኖስ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በሰጠችው አስተያየት በነፃነቱ ዉጊያ ሕይወታቸዉን የሰዉት «አራት አጎቶቼ ይህንን ቢያዩ ኖሮ ምን ይሉ ነበር?» በማለት ትጠይቃለች።»ሕይወታቸዉን የሰዉት ለዚሕ አልነበረም» ብላለች ሜሮን። ውልጫፎ ገብሬ በፌስቡክ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። ለነጻነት የተዋጉት እንደዚህ አይነት ውጤት እንደሚሆን ቢያውቁ እንዴት በቆጫቸው።ሆኖም የሚጨቁናቸው የራሳቸው ወገን ስለሆነ እንደ ስጦታ መቀበል ነው። ሲሉ ኢሳያስ አዳለ ለውልጫፎ ኤርትራውያን «በነጻነት የሚኖሩ የከበሩ ስላም ወጥተው ሰላም የሚገቡ ህዝብ ናቸው በማለት መልስ ሰጥተዋል። ተስፋዬ እሸቱ ድንቄም ነፃነት !? በማለት የኢሳያስን አባባል አጣጥለዋል።  መልሰዋል። ራስ ገቢሳ ቀነአ በፌስቡክ ያም ሆነ ይህ መሬቱ ነፃ ወጥቷል ብለዋል። ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ኤርትራ ምርጫ የማይደረግባት፣ሕገ-መንግስት የማይታወቅባት፣የፕሬስ ነፃነትና የሰብአዊ መብቶች የማይከበሩባት ሐገር ናት። አለም አረጋዊ ኤርትራ ሃገር ናት ግን መንግስት ግን የላትም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። 
አዲሱ አዳነ ግን።«እንኳን ለ30ኛ አመት የነፃነት በዐል አደረሳችሁ።» በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። 
19ኛው ክፍለ ዘመን በሰባት ዓመቱ ብሪታንያ ተወስዶ ሲሞት እዚያው የተቀበረው የኢትዮጵያዊው የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አጽም እንዲመለስ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበል ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አስታውቋል። የልዑሉ ቤተሰብ፣ ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ እና መንግሥት የልዑሉ አጽም ካረፈበት ከዊንድሶር ቤተ መንግስት ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ደጋግመው ቢጠይቁም ልዑል አለማየሁ በተቀበረበት ስፍራ“አርፈው የሚገኙት ሳይረበሹ፣ አጽሙን ማውጣት የሚቻል አይደለም። ስለዚህ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት እንደማንችል እናሳውቃለን” ሲል መልስ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል።ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩት ውስጥ ይህ የዊንድሶር ቤተ መንግሥት ይህን የሰሙ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን ተጠቃሚዎች መልሱን የሚደግፉ የሚቃወሙና የተለያዩ የስላቅ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። 
መሳፍንት ከጉመራ ማዶ በፌስቡክ «አለም ሁሉ አመፀብን ተው መልሡልን» ሲል ይማጸናል። ልዑል ኤም ኬ ደግሞ ያሳዝናል ብሏል። «ምነው በሀገሩ በሞተ ነበር ሞት የትም አትቀር» ልቤ በእግዚአብሔር ፀና በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ነው። ምስጋናው ለገሰ የግፍ ግፍ መስራት ካልፈለጉ መመለሱ የተሻለ የይቅርታ መንገድ ይከፍታል ብለዋል።ዳንኤል አበራ የልዑል አለማየሁ አጽም ከእኛ በቁም ካለነው የተሻለ አገራችንን እያስተዋወቀ ነው። በተቀበረበት የእንግሊዝ ነገሥታት መቃብር ቦታ በዓመት ሺዎች ይጎበኙታል። ኢትዮጵያዊው ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የሚለው ስሙ ከአንድ አምባሳደር በላይ እያስተዋወቀን ነው ።ለመሆኑ አምጥታችሁ ምን ልታደርጉት ነው ? በክብር ያረፈውን ልዑል ክብር ልታሳጡት ካልሆነ ብለዋል። 
ቢንከ ቢንከ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ ሃሳብ የልዑል አለማየሁ አጽም ባለበት መቆየቱን ይደግፋል  «በሰላም ይረፍ። በሕይወት ያሉትም መቼ ወደሀገር ገቡ? የሚል አስተያየት ሰፍሯል። ክብሮም ዎንድዮም « አረ በሰላም ይረፍ እኛም መሄጃ አጥተናል» ፉአድ ሁሴን አሊ ደግሞ «ኧረ በፈጠራችሁ አፅሙ እንኳን በሰላም እዛው ይረፍ በሱ ስም ሌላ ነገር ፍለጋ ካልሆነ በቀር» ብለዋል።ጆከር ዜሮ ዜሮ አጽም እንጀራ ይሆናል እንዴ የሚበጀውን ስንዴ አምጡልን
 «ኧረ ምን በወጣው እዚያው ይቀመጥ! ደሞ ሞቶም አይረፍ እንዴ? በዚች ሃገር ላይ የቆመውን መድረሻ እያሳጡ የሞተውን መቀስቀስ ምን የሚሉት ቂልነት ነው ? ብርሃኑ ግሩም ናቸe በፌስቡክ ይህን ያሉት ሀጎስ በርሄም እረ እዛው በሰላም ይረፍ ኢትዮጵያ ራስዋን ፈልጋ እስክታገኝ  ብለዋል, ከበር ቻቻ «አፅም ምን ልፈይድልህ? አሁን እየተጨፈጨፈ ያለውን ህዝብ በአግባቡ በያዛችሁ የሞተውማ በቃ አፈር ነው አፈር ሆኗልኮ። ሲሉ ምህረት ፓሪስ ደግሞ መጀመሪያ በሕይወት ላሉት ክብር ቢኖረን የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ጽላት አስናቀ ምንም እንኳን ጉዳዩ ቢዘገይም ትክክል አይደለም ህዝቡ አጽሙ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ከፈለገ መስማማት አለበት ይህን ጉዳይ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ጋር አታዛምዱት።» ሲሉ የበኩላቸውን ምክር አካፍለዋል ። 
በሰባት ዓመቱ ወደ ብሪታንያ የተወሰደው ልዑል አለማየሁ እጎአ በ1879 ፣ በ18 ዓመቱ በመተንፈሻ አካላት ሕመም አርፎ በዊንድሶር ካስል ተቀብሯል።የዊንድሶር ቤተ መንግስት የብሪታንያ ንጉሳውያን ቤተሰብ የመቃብር ቦታ ነው። 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 
 

Äthiopien Kulturministerin Dr. Hirut
ምስል Äthiopisches Außenministerium
Isaias Afwerki
ምስል Khalil Senosi/AP Photo/picture alliance
Äthiopien  | Bürgerkrieg
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance