የማሊ ቀውስ እና ኤኮዋስ
ረቡዕ፣ ኅዳር 5 2005
የተመ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የአፍሪቃ ህብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ወደማሊ የጦር ተልዕኮ የሚላክበትን ዕቅድ እአአ እስከ ህዳር ሀያ ሰባት እንዲያቀርብ ጊዜ ሰጥቶዋል። ለማሊ ውዝግብ ከጦሩ ርምጃ በፊት፡ በድርድር መፍትሔ የማስገኘቱ ጥረት እንዲቀድም የማሊን ቀውስ ለማብቃት የተነደፈው የሰላም ማፈላለጊያው ዕቅድ በግልጽ አስቀምጦዋል።
የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፡ ኤኮዋስ ጦሩን ወደ ማሊ ለመላክ ዝግጅት ቢጀምርም፡ ውዝግቡ በውይይት ሰላማዊ መፍትሔ ሊገኝለት ይችላል የሚል እምነት ስላለው፡ በወቅቱ ከፅንፈኞቹ አንዱ የሆነው የአንሳር ዲን የልዑካን ቡድን የሽምግልናውን ሚና ከያዙት የኤኮዋስ ተደራዳሪ የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ ጋ እየተደራደረ ነው።
የማሊ ውዝግብ በርግጥ በድርድር መፍትሔ ማግኘት አለማግኘቱ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፡ እንደ ለንደኑ የቻታም ሀውስ የፖለቲካ ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አሌክስ ቫይንስ አስተያየት፡ ኤኮዋስ፡ የአፍሪቃ ህብረትም ሆኑ የተመድ ጦርነትን እንደመጨረሻ አማራጭ ነው የሚያመለከቱት።
« ይህ የሰላም ማፈላለጊያው ዕቅድ አካል ነው። ማለትም ድርድሩን በመቀጠል በማሊ የጦር ርምጃ ማስወገድ የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ነው። ይህ የአፍሪቃ ህብረት ባለፈው ጥቅምት ወር የደረሰው የስልታዊው መመሪያ እና የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ አንቀጽ 2071 አካል ነው። ስለዚህ የወቅቱ ዕቅድ ድርድሩን ከመቀጠሉ ጎን፡ የጦሩን ርምጃ ካስፈለገ በሚቀጥለው ዓመት መጀመር የሚቻልበትን ዝግጅት ማካሄድ ነው። »
ኤኮዋስ ግን የማሊን የግዛት ሉዓላዊነትን ከሚያከብሩ ጋ ብቻ ድርድሩን እንደሚያካሂድ በወቅቱ ቅድመ ግዴታ አስቀምጦዋል። ይህ አንዳንድ ወገኖችን የሚያገል ሊሆን እንደሚችል ነው አሌክስ ቫይን የሚገምቱት።
« በኔ አስተያየት ድርድሩ በጠቅላላ የተሳካ ውጤት ያስገኛሉ ብዬ አላስብም። ሰላማዊ መፍትሔ መድረስ የማይፈልጉ ቡድኖች ይኖራሉ። ስለዚህ በሚቀጥለው አውሮጳዊ ዓመት የጦር ርምጃ የምናይበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። »
ኤኮዋስ በወቅቱ ይፋ ባይሆንም ብዙ የአፍሪቃ መሪዎች የተሳተፉበት የሽምግልና ጥረት መጀመሩ አዎንታዊ ነው፤ ግን በማሊ ሰላማዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ወይም የጦሩን ርምጃ የመጀመሩ ማንኛውም ውሳኔ ከኤኮዋስ ባሻገር ሌሎች ሀገራትንም የሚመለከት በመሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያሻው አሌክስ ቫይን ገልጸዋል።
« የማሊ ውዝግብ የኤኮዋስ አባል ያልሆኑ ሌሎች፡ በተለይ አልጀሪያ እና ሞሪታንያንንም ይመለከታል። ስለዚህ በዚሁ ረገድ የሚደረስ ማንኛውንም ስምምነት ወይም ዕቅድ በሚገባ ማስተባበር ያስፈልጋል፤ በተለይ ዕቅዱን ሞሪታንያ እና አልጀሪያ አባል ከሆኑበት ከአፍሪቃ ህብረት ጋ ማቀነባበሩ ተገቢ ይሆናል። የአፍሪቃ ህብረት የጦሩን ተልዕኮ በማስተባበሩ ረገድ ሚና መጫወቱ ባይቀርም፡ የተልዕኮውን አመራር የሚይዘው ኤኮዋስ ይሆናል። ኤኮዋስ ወደ ማሊ ስድስት ወር የሚቆይ ጦር ለመላክ ማቀዱን ባለፈው የሣምንት መጨረሻ ያስታወቀበት መግለጫም ይህንን የሚጠቁም ነው። »
ግን ኤኮዋስ ካለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ብቻውን ሰሜናዊ ማሊን የተቆጣጠሩትን ኃይላት መደምሰስ መቻሉን የፖለቲካ ተንታኞች አጠያይቀዋል።
« ኤኮዋስ በማሊ ጉዳይ ላይ ለሚወሰደው ርምጃ ሰፋ ያለ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንደሚያገኝ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ ተረጋግጦለታል። ስለዚህ የሚያስፈልገው ቴክኒካዊ ርዳታ ይቀርብለታል። የማሊን ቀውስ ለማስወገድ በተነደፈው ዕቅድ የማሊን ጦር ማሠልጠን ትልቅ ሚና ይይዛል። የአውሮጳ ህብረትም በሥልጠናው ተልዕኮ፡ ፈረንሣይን የመሳሰሉ ሀገራት ደግሞ በጋራው ግንኙነት ረገድ የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸው አይቀርም። »
ፈረንሣይ ምናልባት ወደ ማሊ ሊላክ ይችል ይሆናል የሚባለውን የኤኮዋስ ጦር በአየር ጥቃት እንደማትረዳ በትናንቱ ዕለት ግልጽ አድርጋለች። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ማሊ ለሚባለው ጦር ስምሪት የስንቅና የትጥቅ ርዳታ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጾዋል።
አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ