1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዳፋ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 4 2015

ተመራማሪዎቹ ማህበራዊ መነጠል እና ብቸኝነት ፣ ድብርት ፣ ከፍ ያለ ጭንቀት እና ራስን የማጥፋት ሀሳቦችን እና ሌሎች ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጋር የተገናኙ ተፅዕኖዎችንም ጠቁመዋል ። ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ፣በራስ ስራ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በዲጅታሉ ዓለም ባልተጨበጡ ነገሮች መጠመድም ሌላው ችግር ነው።

https://p.dw.com/p/4PyG9
Social Media Apps auf Smartphone
ምስል picture alliance / empics

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሉታዊ ተፅዕኖ

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሰዎችን ተግባቦት እና ግንኙነት የቀየሩ ፈጣን ዲጅታል መድረኮች ናቸው። እነዚህ የአውታረ መረብ መድረኮች ለአጠቃቀም ቀላል እና አዝናኝ በመሆናቸው የልጆችን ትኩረትም በቀላሉ መሳብ ችለዋል።በ25 የአውሮፓ ሀገራት የተደረገ የማህበራዊ መድረኮች አጠቃቀም ጥናት እንደሚያሳየው ከ9-12 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ልጆች መካከል 38 በመቶ፤ ከ13-16 አመት እድሜ ክልል ከሚገኙት 77 በመቶ የእነዚህ መድረኮች ተጠቀሚዎች ናቸው። እነዚህ ልጆች ቢያንስ በአንድ የማህበራዊ ድህረ ገጽ ላይ የራሳቸው መገለጫ እንዳላቸው ይናገራሉ።የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ ፣ ለመማር፣ ለመግባባት እና ለመዝናናት ጥሩ መድረኮች ናቸው። የሥነ አእምሮ ባለሙያው ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራም በዚህ ይስማማሉ።
የማህበራዊ ትስስር መድረኮች በአሁኑ ወቅት የልጆችም ሆነ የአዋቂዎች ዋነኛ የህይወት አካል እና አዲስ የመግባቢያ መንገዶች ሆነዋል። በሰዎች ማህበራዊ ህይወት እና የህዝብ አስተያየት እንዲሁም በሰዎች የግዢ ውሳኔዎች እና ንግዶች ላይም ተፅዕኖ ያሳድራሉ።.
ያም ሆኖ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በልጆች ላይ የሚያመጡት አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አልሆነም። ምክንያቱም እንደ ፕሮፌሰር ሰለሞን እነዚህ መድረኮች ከልክ በላይ ጥቅም ላይ ከዋሉ  ለሳይበር ጉልበተኞች ጥቃት/cyberbulling/፣ ለጭንቀት ፣ለድብርት እና የእንቅልፍ መዛባትን ለመሳሰሉ  የጤና ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ። ልጆች ተፅዕኖውን የሚረዱበት የአዕምሮ ብስለት ደረጃ ላይ ባለመሆናቸው ደግሞ ችግሩ በእነሱ ላይ የበረታ ይሆናል ያላሉ።
የኒውዮርክ ፣የቨርጂኒያ፣የሳን ዲዬጎ ዩኒቨርሲቲዎች እና ደብሊው ብራድፎርድ ዊልኮክስ የቤተሰብ ጥናት ተቋም ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም ጋር በተገናኘ ባደረጉት ጥናትም  መድረኮቹ በልጆች የአእምሮ ጤና ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አመልክተዋል። ጉዳቱ በተለይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ባሉ ልጃገረዶች ከፍተኛ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል በበኩሉ በጎርጎሪያኑ  2021 ዓ/ም ባደረገው ጥናት የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ከሚያዘወትሩ 10 ታዳጊ ልጃገረዶች 6 ቱ ያለማቋረጥ የሀዘን ወይም የተስፋ ቢስነት ስሜት እንደሚሰማቸው ይፋ አድርጓል። ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ካሉ ሴት ተማሪዎች መካከል 30% የሚሆኑት ከፍተኛ የሆነ ራስን የመጥላት ስሜት እንደሚሰማቸው ገልጿል።ተመራማሪዎቹ ማህበራዊ መነጠል እና ብቸኝነት ፣ ድብርት ፣ ከፍ ያለ ጭንቀት እና ራስን የማጥፋት ሀሳቦችን እና ሌሎች  ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጋር የተገናኙ ተፅዕኖዎችንም ጠቁመዋል ። ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ፣በራስ ስራ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በዲጅታሉ ዓለም ባልተጨበጡ ነገሮች መጠመድም ሌላው ችግር  ነው።ፕሮፌሰር ሰለሞንም የሳይበር ጉልበተኝነት በወጣት ሴቶች የከፋ ነው ሲሉ በምሳሌ ያስረዳሉ።
ይህ ያሳሰባት የአሜሪካዋ ዩታህ ግዛትም በቅርቡ በአዳጊዎች የፌስቡክ፣ የቲክቶክ እና የኢነስታግራም እንዲሁም ሌሎች  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም ላይ ገደብ የሚጥል አዲስ ህግ አውጥታለች። በአዲሱ ህግ አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያዎች ለልጆች አገልግሎቱን ከማቅረባቸው በፊት የወላጆችን ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል ። እነዚህን መተግበሪያዎችም ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ አዳጊዎች ያለ ወላጅ ይሁንታ እንዳይከፍቱ ያደረጋል።ረቂቅ ህጉ ኩባንያዎቹ የአዳጊዎቹን የማኅበራዊ ትስስር አጠቃቀም፣ ታሪክ፣ የለጠፏቸውን እና በግል የተጻጻፏቸውን መልዕክቶች ሳይቀር ለወላጆች እንዲሰጡ የሚያስገድድም ነው። የሚጠቀሙበትን ስዓት፣በልጆቹ የማኅበራዊ መገናኛ ሰሌዳ ላይ የሚለቀቁ ማስታወቂያዎች ላይም ገደብ ይጥላል።
በልጆች መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማት እርምጃውን ይበል የሚያሰኝ ነው ብለውታል።የችግሩን አሳሳቢነት የተመለከቱ ሌሎች ግዛቶችም ተመሳሳይ ሕጎች እያረቀቁ ነው ተብሏል።
በመሆኑም ልጆች የተንቀሳቃሽ ስልኮችን እና  እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቱዩብን  የመሳሰሉ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን  እንዲጠቀሙ ወላጆች ከመፍቀዳቸው በፊት ተግባራቶቹን፣ የግላዊነት መመሪያዎችን እንዲሁም የእድሜ ገደቦችን ማወቅ አለባቸው። በአጠቃቀም ወቅትም የወላጆች  ቁጥጥር  ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
ልጆች መቼ ስልክ መያዝ አለባቸው? ለሚለው ቁርጥ ያለ መልስ ባይኖርም፤ ዕድሜያቸው 13 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ልጆች፡ ፌስቡክ /Facebook/፣ቲዩተር  /Twitter/፣ቲክ ቶክ/Tiktok/ እና ዩቱዩብ Youtube፣ዕድሜያቸው 16 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ደግሞ፡ ዋትስአፕ/WhatsApp/፣ ሊንክዴን/LinkedIn /እና ማይስፔስ /Myspace/ ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ወጣቶች ደግሞ  ሚት ሜ /MeetMe /እና ታግድ /Tagged/የመሳሰሉትን ዲጅታል መድረኮች መጠቀም እንደሚችሉ በየ ገጾቹ የሰፈሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ያም ሆኖ በልጅነት ዕድሜ ክልል የሚገኙት ክፉውን እና ደጉን ለመለየት ስለሚቸገሩ አንዳንድ ይዘቶች  ባህሪያቸው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላል።ለዚህም ወላጆች የልጆችን የስክሪን ጊዜ መገደብ ተግባራዊ መፍትሄ መሆኑ ይጠቀሳል።
በሌላ በኩል በፔው የምርምር ማእከል  ጥናት መሰረት 95% የሚሆኑ ወጣቶች ስማርት የተንቀሳቀሽ ስልኮችን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። 45 በመቶ የሚሆኑት ሁል ጊዜ በይነመረብ ላይ ናቸው። በዚህ የተነሳ አጠቃቀማቸውን መቆጣጠር ለወላጆች ፈታኝ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ወላጆች የልጆችን ዲጅታል መድረኮች አጠቃቀም ለመቆጣጠር ከመሞከራቸው በፊት አወንታዊ እና አሉታዊ ውጤቶቹን ማወቅ ፣ ከልጆች ጋር ጥብቅ ትስስር መፍጠር  እና አንዳንዴም አብሮ በመሳተፍ አቅጣጫ ማሳየት እና ማስተማር በባለሙያዎች የሚመከር ነው።
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ዩታህ ግዛት ፤በመንግስት በኩል የልጆችን አዕምሮ ከችግር የሚታደግ የዲጅታል አጠቃቀም መመሪያዎች እና ፖሊሲዎችን ማውጣት የመፍትሄ አካል መሆኑን ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ገልፀዋል።

Protest iranischer Frauen durch Tanz
ምስል DW
Symbolbild Soziale Netze
ምስል Axel Heimken/dpa/picture alliance
Symbolbild | Cyber Bullying
ምስል Antonio Guillen Fernández/PantherMedia/IMAGO
Symbolbild | Cyber Bullying
ምስል Antonio Guillen Fernández/PantherMedia/IMAGO

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ገለታ