1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 24፣2016 የዓለም ዜና

Negash Mohammedማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

-የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት አከራይና ተከራዮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያገለግላል ያለዉን አዲስ ሕግ አፀደቀ።ምክር ቤቱ «የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ» ያለዉ ሕግ በአከራይ፣ በተከራይና በመንግስት መካከል ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ይረዳል ተብሏል። -የእስራኤል ጦር ለጋዛ ሕዝብ ርዳታ የሚሰጡ ሠራተኞችን መግደሉን የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አመኑ።ጥቃቱን የተለያዩ መንግስታትና ድርጅቶች አዉግዘዉታል።በሌላ በኩል ደማስቆ-ሶሪያ የሚገኘዉ የቆንስላ ፅሕፈት ቤቷ ትናንት የጋየባት ኢራን እስራኤል ለመበቀል ዛተች።የዜናዉ መልዕክት የእስካሁኑ ነበር።

https://p.dw.com/p/4eMex

የመኖሪያ ቤት ክራይን የተመለከተ አዋጅ ፀደቀ

 

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት አከራይና ተከራዮችን ግንኙነትን በሕግ የሚገዛ  አዋጅ ዛሬ አፀደቀ። «የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ» የተባለዉ ደንብ አከራይ ተከራዮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያገለግላል ተብሏል።የኢትዮጵያ መንግስት አዋጁን ያረቀቀዉ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው፣ የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት በማሰብ እንደሆነ አስታዉቋል።በአዋጁ መሠረት ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ተከራይ እስከ ሁለት ዓመት የመከራየት መብት አለዉ።የመኖሪያ ቤት አከራዮችም ይቋቋማሉ በተባሉ "ተቆጣጣሪ አካላት" በአመት አንድ ጊዜ በሚሰጡት የኪራይ ተመን ዋጋው የሚመራ እና የዘፈቀደ የኪራይ ጭማሪን የሚያስቀር ነው ተብሏል።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ እንደዘገበዉ አዋጁ በ3 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።ከዛሬ ጀምሮ የፀና ነዉ።

 

ዳካር-የአዲሱ ፕሬዝደንት በዓለ ሲመት

ባለፈዉ መጋቢት 15 ሴኔጋል ዉስጥ በተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ባሲሮ ድዮማዬ ፋይ ዛሬ ቃለ መሐላ ፈፅመዉ የሐገሪቱን የመሪነት ሥልጣን ተረከቡ። ፋይ፣ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት መሪዎች፣ የዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ተወካዮች በተገኙበት ድግስ ላይ ለፈጣሪና ለሴኔጋል ሕዝብ በታማኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

«በፈጣሪና በሴኔጋል ሕዝብ ፊት የሴኔጋል ሪፐብሊክ ፕሬዝደንትነት ኃላፊነቴን በተገቢዉ መንገድ ለማከናወን ቃል እገባለሁ።

ብዙም የማይታወቁት ፋይ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ታዋቂነት ያላቸዉን የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኦስማን ሶኖኮን ሙሉ ድጋፍ በማግኘታቸዉ የመንግስት ድጋፍ ያላቸዉንና ሌሎች አንጋፋ ፖለቲከኞችን በልጠዉ ለመመረጥ ችለዋል።ፋይ ሙስናን ለማስወገድና ነባሩን የፖለቲካ ሥርዓት ለመቀየር የገቡት ቃልም የመራጮችን ቀልብ ስቧል።የፋይ ዋና ደጋፊ ሶኖኮ በስም ማጥፋት ወንጀል የ6 ወራት እስራት በገደብ ስለተፈረደባቸዉ መወዳደር አልቻሉም። ሳንኮም፣ ፋይም ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ማኬይ ሳል ባደረጉላቸዉ ምሕርት ከእስር የተለቀቁት ምርጫዉ ሊደረግ ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ሲቀረዉ ነዉ።የ44 ዓመቱ የቀድሞ ግብር ሰብሳቢ በሴኔጋል ታሪክ የመጀመሪያዉ ወጣት ፕሬዝደንት ናቸዉ።

 

ካይሮ-አል ሲሲ ቃለ መሐላ ፈፀሙ

ባለፈዉ ታሕሳስ ግብፅ ዉስጥ በተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ያለብዙ ተቀናቃኝ ተወዳድረዉ ያሸነፉት አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ ዛሬ ቃላ መሐላ ፈፅሙ። የቀድሞዉ ፊልድ ማርሻል በሕዝብ የተመረጡትን ዶክተር መሐመድ ሙርሲን በመፈንቅለ መንግስት አስወግደዉ የመሪነቱን ሥልጣን የያዙት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ኃምሌ 2013 ነበር። ከዚያ በኋላ ሁለቴ በተደረጉ ምርጫዎች ብቻቸዉን ወይም ብዙም ከማይታወቁ ተፊካካሪዎች ጋር ተወዳድረዉ አሸንፈዋል። ባለፈዉ ታሕሳስ በተደረገዉ ምርጫ 89 ከመቶ ድምፅ ማግኘታቸዉ ተነግሯል።አል ሲሲ ዛሬ ቃለ መሐላ የፈፀሙት ከካይሮ አጠገብ አዲስ በተሰራችዉ ርዕሰ ከተማ በተሰየመዉ ምክር ቤት ጉባኤ ፊት ነዉ።

 

 

እየሩሳሌም፟-የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ጦራቸዉ የርዳታ ሠራተኞችን መግደሉን አመኑ

የእስራኤል ጦር ለጋዛ ሕዝብ ርዳታ የሚያቀብል ድርጅት ሠራተኞችን መግደሉን የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አመኑ። እዉቁ የወጥቤት ባለሙያ ሆሴ አንድሬ የመሠረተዉ የዓለም ማዕከል ማዕድ ቤት የተባለዉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከቅርብ ሳምንታት ጀርምሮ ለጋዛ ሕዝብ በብዙ መቶ ቶን የሚለካ ሰብአዊ ርዳታ አቅርቧል። ትናንት ሰባት ሠራተኞቹ ከተገደሉበት በኋላ ግን ድርጅቱ በቆጵሮስ በኩል ለጋዛ የሚልከዉን ርዳታ አቋርጧል።ከብዙ ማቅማማት በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያም ኔታንያሁ ዛሬ ቀትር ላይ ለጥቃቱ ይቅርታ ጠይቀዋል።

«እንዳለመታደል ሆኖ ባለፈዉ ቀን የኛ ኃይሎች ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ በየዋሕ ሰዎች ላይ ያልታሰበ አሳዛኝ ጥቃት አድርሰዋል። ይሕ በጦርነት ያጋጥማል። ይሕንን በጥልቅ እንመረምራለን። ከመንግስታት ጋር እየተገናኘን ነዉ። ሁለተኛ እንዳይደገም አስፈላጊዉን ሁሉ እናደርጋለን።»

የእስራኤል ጦር ከገደላቸዉ የርዳታ ድርጅት ሠራተኞች መካከል የአዉስትሬሊያ፣ የፖላንድ፣ የብሪታንያ፣ የአሜሪካ እና የካናዳ ጥምር ዜግነት ያላቸዉ ይገኙባቸዋል። ሠራተኞቹ የተገደሉት ዴር አል ባላሕ በተባለዉ ከተማ ርዳታ አራግፈዉ ሲወጡ ነዉ። የዓለም ማዕከል ማዕድ ቤት እንዳለዉ ሠራተኞቹ ሥለጉዟቸዉ ለእስራኤል መከላከያ ጦር አሳዉቀዉ ነበር። ግን ከመገደል አላመለጡም።የእስራኤልን ርምጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ የአረብና ዜጎቻቸዉ የተገደሉባቸዉ መንግስታት አዉግዘዉታል።

 

ቴሕራን-ኢራን ስራኤል ለመበቀል ዛተች፣ ሩሲያ ጥቃቱን አወገዘ

ኢራን የአብዮታዊ ዘብ ባልደረቦችን ገድላለች ያለቻትን የረጅም ዘመን ጠላትዋን እስራኤልን ለመበቀል ዛተች።  ሶሪያ ርዕሰ ከተማ ደማስቆ የሚገኘዉ የኢራን ቆንስላ ፅሕፈት ቤት ትናንት በከባድ ፈንጂ ተመትቶ ወድሟል። በፍንዳታዉ ሕንፃዉ ዉስጥ የነበሩ 7 የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባልደረቦችና ሌሎች 5 ሰዎች መገዳለቸዉን የኢራን መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ ያደረጉት የኢራን ባለስልጣናት እስራኤልን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት እየዛቱ ነዉ።የኢራን የበላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻምኒ «እስራኤል በጀግኖቻችን እጅ ትቀጣለች» ብለዋል። እስራኤል ሥለ ጥቃቱ ያለችዉ ነገር የለም። ይሁንና የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላን «በየአቅጣጫዉ ጦርነት ላይ ነን» ማለታቸዉ ተጠቅሷል። ሩሲያ ጥቃቱን አዉግዛለች።የፕሬዝደንት ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት ወገን ግን የለም።«ባሁኑ ወቅት ጥቃቱን ሥላደረሰዉ ወገን ማንነት ድምዳሜ ለመስጠት አንጣደፍም። ይሁንና እንዲሕ ዓይነቱ ጥቃት ዓለም አቀፍ መሠረታዊ ሕግጋትን የሚጥስና የወረራ እርምጃ ነዉ።»

ቱርክና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽም ጥቃቱን አዉግዘዋል።የድርጅቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሥለጥቃቱ ማምሻዉን ይወያያል።ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገር የጠየቀችዉ ሩሲያ ናት። በጥቃቱ ከተገደሉት ሁለቱ ጄኔራሎች እንደነበሩ የኢራን መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።

 

ጁባ-ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ወጣቶች በከፈቱት ጥቃት 12 ሰዎች ገደሉ፣ 15 ጠፉ

ደቡብ ሱዳን ምሥራቃዊ ግዛት የሚገኙ መንደሮችን የወረሩ ታጣቂ ወጣቶች 12 ሰዎች ገደሉ፤ ሌሎች 10 አቆሰሉ። ጥቃቱ የተፈፀመበት የታላቁ ፒቦር ግዛት  የማስታወቂያ ሚንስቴር እንዳለዉ ታጣቂዎቹ ከገደሉና ካቆሰሏቸዉ በተጨማሪ 15 ልጆች የደረሱበት አልታወቀም።ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ከብትና ልጆችን ለመዝረፍ በተቀናቃኝ ጎሳ ታጣቂዎች መካከል በየጊዜዉ በሚደረግ ግጭት የብዙ ሰዉ ሕይወት ይጠፋል፤ ልጅ፣ ሐብት ንብረት ይዘረፋልም። እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ ለ6 ዓመታት የተደረገዉ የርስበርስ ጦርነት ጋብ ካለ ወዲሕ ደግሞ መገዳደልና መዘራረፉ ተባብሷል። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ከተገነጠለች እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2011 ወዲሕ የመጀመሪያዉን ምርጫ ዘንድሮ ሚያዚያ ታደርጋለች ተብላ ትጠበቃለች።

 

 

ኢስታንቡል-የእሳት ቃጠሎ 25 ገደለ

ኢስታንቡል ቱርክ ዉስጥ በጥገና ላይ የነበረ አንድ የምሽት ክለብ ሕንፃ በመጋየቱ በትንሽ ግምት 25 ሰዎች ሞቱ። የቱርክ ዜና አገልግሎት የኢስታንቡልን ከተማ ባለስልጣናት ጠቅሶ እንደዘገበዉ ቃጠሎዉ የተነሳዉ ዛሬ ቀጥር ላይ ነዉ። 16 ፎቆች ካሉት ሕንፃ ከምድር ቤት የተነሳዉ እሳት ባጭር ጊዜ አካባቢዉን አዳርሶታል። በቃጠሎዉ ከሞቱት ሌላ የቆሰሉ ሥለመኖር አለመኖራቸዉ የተባለ ነገር የለም። አምስት ሰዎች ግን በጥርጣሬ ታስረዋል። የቱርክ ትልቅ የንግድ፣ የመዝናኛና ጥንቃዊት ከተማ ኢስታንቡል ሰሞኑን በከንቲባ ምርጫ ስትባትል ነበር።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።