1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የመጀመሪዋ ጀርመናዊት ሴት ወደ ህዋ ልትመጥቅ ነው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016

ስፔስ ኤክስ የተባለው የግል የጠፈር ምርምር ኩባንያ ሰሞኑን እንዳስታወቀው የመጀመሪያዋ ጀርመናዊት ሴት ከሌሎች አራት ጠፈርተኞች ጋር በቅርቡ ወደ ህዋ ትጓዛለች።ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር ጉዞ የምታደርገው ጀርመናዊት ራቤያ ሮጌ ትባላለች።የሮቦቲክስ ተመራማሪ ነች። ለመሆኑ ሴቶች በጠፈር ምርምር ያላቸው አጠቃላይ ተሳትፎ ምን ያህል ነው?

https://p.dw.com/p/4k1Wr
የ28 ዓመቷ የሮቦቲክስ ተመራማሪ ራቢያ ሮጌ
የ28 ዓመቷ የሮቦቲክስ ተመራማሪ ራቢያ ሮጌ ትውልድ እና እድገቷ በጀርመኗ ዋና ከተማ በርሊን ሲሆን፣ በኤሌክትሪካል ምህንድስና እና በመረጃ ቴክኖሎጅ  የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪዋን ዙሪክ በሚገኘው የስዊዝ  ፌዴራል የቴክኖሎጂ ተቋም  ተከታትላለች። ለዶክትሬት ዲግሪዋ  ምርምርም አንድ ዓመት ያህል ስዊድን ስቶክሆልም  ቆይታለች። በኤሌክትሪካል ምህንድስና እና በመረጃ ቴክኖሎጅ  የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪዋን ዙሪክ በሚገኘው የስዊዝ  ፌዴራል የቴክኖሎጂ ተቋም  ተከታትላለች።ምስል Privat/dpa/picture alliance

የመጀመሪዋ ጀርመናዊት ሴት ወደ ህዋ ልትመጥቅ ነው

ጀርመን እንደ ኢምሊ ሾነንቫልድ እና ኒኮላ ዊንተር ያሉ ስመጥር ሴት የአስትሮኖሚ ባለሙያዎች ያሏት ሀገር ብትሆንም፤እስካሁን በህዋ በረራ ሴቶች የመሳተፍ ዕድል አለማግኘታቸውን የጀርመን የኤሮስፔስ ማዕከል (DLR) መረጃ ያሳያል።
በቅርቡ ግን ስፔስ ኢክስ /SpaceX/ የተባለው የግል የጠፈር ምርምር ኩባንያ የመጀመሪያዋ ጀርመናዊት ሴት ፤ራቤያ ሮጌ ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር በስፔስ ኤክስ ፋልኮን 9 / Falcon 9/  ሮኬት  ወደ ህዋ እንደምትመጥቅ ገልጿል።

የሮቦቲክስ ተመራማሪ ራቢያ ሮጌ ማነች?

የ28 ዓመቷ የሮቦቲክስ ተመራማሪ ራቢያ ሮጌ ትውልድ እና እድገቷ በጀርመኗ ዋና ከተማ በርሊን ሲሆን፣ በኤሌክትሪካል ምህንድስና እና በመረጃ ቴክኖሎጅ  የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪዋን ዙሪክ በሚገኘው የስዊዝ  ፌዴራል የቴክኖሎጂ ተቋም  ተከታትላለች። ለዶክትሬት ዲግሪዋ  ምርምርም አንድ ዓመት ያህል ስዊድን ስቶክሆልም  ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለ«ስፔስ ኤክስ»  በረራ ካሊፎርኒያ ውስጥ ስልጠና ላይ ትገኛለች።የካሊፎርኒያው ስልጠና ዋናው ትኩረቱ በ Falcon 9 ሮኬት ወደ ህዋ የሚተኮሰውን የ SpaceX "ድራጎን" የተሰኘ ካፕሱል በዝርዝር ማወቅ እና በጠፈር በረራ ወቅት ሰውነት ከፍተኛ ችግርን መቋቋም ይችል እንደሁ ለመፈተን ነው። «እዚህ በማንኛውም  አይነት ሁኔታ ውስጥ ሰው እንዴት ተለማምዶ መቆየት  እንደሚችል ይማራል» ብላለች ሮጌ።

ወጣቷ የሮቦቲክስ ተመራማሪ ለሦስት ወራት ያህልም መርከብ ላይ ሠርታለች።በዚህም  ለጠፈር  በረራ ሊረዳት የሚችል ልምድ አግኝታለች። ራቢያ ሮጌ፤ ከአሁኑ ተልዕኮ ጋር ምንም ግንኙነት ባይኖረውም ፤ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ  ውስጥ በስቫልባርድ ደሴት የጉዞ ስልጠና ላይ ነበረች።«በኔጌቲቭ 20 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ውስጥ እንዴት መኖር እንደምትችል እና ጣቶቻችን በብርድ ሳይቆረጡ መቆየት እንደሚቻል ተምሪያለሁ።  እስካሁን ተሳክቶልኛል»ብላለች።
ስፔስኤክስ ባለፉት አራት አመታት  ሰዎችን የያዙ  13 የጠፈር በረራ ተልዕኮዎችን አድርጓል። በዚህም የናሳ ጠፈርተኞችን ወደ አለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ /ISS/ ማጓጓዝን እና በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም  ለመጀመሪያ የተደረገውን የስፔስ ቱሪዝም ተልዕኮ ጨምሮ በርካታ የጠፈር በረራዎችን አከናውኗል።

በዚህ ተልዕኮ እነማን ይሳተፋሉ?

የአሁኑ ተልዕኮ ፍሬም2 /Fram 2 /ይባላል።በአሜሪካዊው ቢሊየነር ኤሎን ማስክ ባለቤትነት የተያዘው SpaceX  ኩባንያ እንደገለፀው፤ሮጌ የምትሳተፈው«የተልዕኮው ልዩ ባለሙያ» በመሆን ነው።የተልዕኮው ግብ ደግሞ ስለ አርክቲክ እና አንታርክቲክ የበለጠ ማወቅ ነው። ይህ በረራ በምድር ዋልታ ላይ የሚደረግ የመጀመሪያው የሰው ልጅ የጠፈር በረራ ሲሆን፤ የቡድኑ አባላት የመጀመሪያውን የሰው ልጅ የራጅ ምስሎች ከህዋ ላይ ሆነው ያዘጋጃሉ። በኩባንያው መሠረት በረራው  የጎርጎርያኑ  2024 ዓ/ም ከመገባደዱ  በፊት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል ።
በዚህ ተልዕኮ ከሮጌ በተጨማሪ ቻይናዊው  ቹን ዋንግ ፣ የኖርዌይ ፊልም ሰሪ ጃኒክ ሚከልሰን እና አውስትራሊያዊው የህዋ አሳሽ ኤሪክ ፊሊፕስ አብረው  ይጓዛሉ።
እንደ ስፔስ ኤክስ፣ይህ በረራ ለአራቱም የመጀመሪያ የጠፈር በረራ ይሆናል።ያም ሆኖ ሮጌ ለእነርሱ ብዙም አስቸጋሪ አለመሆኑን ገልፃለች።
«ሰዎች ከሁሉም የበለጥኩ መሆን አለብኝ ብለው እንዲያስቡ የማድረጉ ጉዳይ  በጣም አነስተኛ መሆን አለበት:: ድራጎን በራሱ እንዲሰራ ሆኖ የተቀነባበረ ቴክኒክ አለው። ስለሆነም በጠፈር ተመራማሪዎች ላይ ያለው ጥገኝነት  በጣም አነስተኛ ነው።»በማለት ገልፃለች።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስከ ጎርጎሪያኑ ግንቦት 2023 ዓ/ም ድረስ ወደ ጠፈር ከተጓዙ 634 ሰዎች ውስጥ 73ቱ ሴቶች ናቸው።ከነዚህም ውስጥ  አሜሪካ 56 ፣ ሶቬት ህብረት ስድስት፣ ካናዳ፣ቻይና እና ጃፓን ሁለት ሁለት ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ብሪታንያ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሴቶችን ወደ ጠፈር ልከዋል።
የስፔስ ሳይንስ ተመራማሪው እና የዓለም አቀፉ የስትሮኖሚ ህብረት  የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን በላይ እንደሚሉት  በዘርፉ የሴቶች ተሳትፎ እንዳይጎላ ያደረገው የተሳሳተ አመለካከት ነው።

ራቢያ ሮጌ እና የስፔስ ኤክስ የበረራ ቡድን
በዚህ ተልዕኮ ከሮጌ በተጨማሪ ቻይናዊው  ቹን ዋንግ ፣ የኖርዌይ ፊልም ሰሪ ጃኒክ ሚከልሰን እና አውስትራሊያዊው የህዋ አሳሽ ኤሪክ ፊሊፕስ አብረው  ይጓዛሉ።ምስል SpaceX/dpa/picture alliance

የሴቶች የጠፈር ጉዞ ታሪክ

የሴቶች የጠፈርጎዞ ታሪክ የተጀመረው በጎርጎሪያኑ 1963 ዓ.ም  የመጀመሪያዋ ሴት ሆና የፆታ እንቅፋትን በተሻገረችው የሶቪየቷ  ቫለንቲና ቴሬሽኮቫ ጉዞ  ነው። በቮስቶክ 6 ላይ የነበራት ታሪካዊ ተልዕኮ በሰው ልጆች የጠፈር በረራ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ብቻ ሳይሆን ሴቶች በጠፈር ምርምር ሙያ  እንዲገቡ ፈር ቀዳጅ ሆኗል።
ቴሬሽኮቫን በመከተል ዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያዋን አሜሪካዊት ሴት ሳሊ ራይድን በጎርጎሪያኑ 1983 ዓ/ም  ወደ ጠፈር በመላክ ታሪክ ሰርታለች።የዕውቋ የፊዚክስ ሊቅ  የራይድ የተሳካ የጠፈር ጎዞ ዘርፉ የፆታ ገደብ እንደሌለው በማሳየት ለሌሎች ሴት ጠፈርተኞች መንገድ ጠርጓል።
ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት ለዚህ በወቅቱ የነበረው የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም እና ዓለም አቀፍ የፖሊሲ ለውጥ እና የባህል አብዮት አስተዋፅኦ አድርጓል። 

የሴቶች የጠፈር ምርምር አስተዋጾ በናሳ

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ ፤ናሳ፣ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን በህዋ ምርምር በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ሆኖ ቆይቷል። አንጋፋዋ ጠፈርተኛ አይሊን ኮሊንስ በጎርጎሪያኑ 1995 የመጀመሪያዋ ሴት የጠፈር መንኮራኩር አብራሪ ስትሆን፤ በ1999ዓ/ም ደግሞ  ኮሊንስ የመጀመሪያዋ ሴት የጠፈር መንኮራኩር አዛዥ በመሆን ሌላ ታሪካዊ ስኬት አስመዝግባለች።
አሜሪካዊቷ የጠፈር ተመራማሪ ፔጊ ዊትሰንም ህዋ ላይ ረዥም ጊዜ በማሳለፍ ስሟ በክብር ይነሳል። ስኬቶቿ በጠፈር ውስጥ ያሉ ሴቶችን አቅም ከማሳየት ባለፈ ሳይንሳዊ እውቀትን ለማራመድ ያላቸውን ጽናት እና ትጋትም አጉልቷል።
 በህዋ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አሜሪካዊት ዶ/ር ሜይ ጀሚሰን ከአለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (ISS) ጋር በመሆን ህዋ ላይ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ ጥናት አካሄዳለች። በዚህም እጅግ አነስተኛ  በሆነ ስበት /ማይክሮግራቪቲ/ ውስጥ የህይወት ሳይንስን  እንድንረዳ አስተዋፅዖ አድርጋለች።
እንደ ዶክተር ሰለሞን በዚህ ሁኔታ እያደገ የመጣው የሴቶች ተሳትፎም ለዘርፉ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ ናሳ
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ ፤ናሳ፣ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን በህዋ ምርምር በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ሆኖ ቆይቷል።ምስል NASA Johnson

የሴቶች አስተዋፅኦ በህዋ ምርምር  

ሴቶች በጠፈር ምርምር ሚያበረክቱት አስተዋፅዖ የጠፈር መንኮራኩሮችን ከማብረር የዘለለ ነው። ድንቋ የሂሳብ እና የፊዚክስ ሊቅ ዶ/ር ካትሪን ጆንሰን በናሳ ቀደምት የጠፈር ተልዕኮዎች  የበረራ ቀመር በመስራት ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። ጆንሰን በጎርጎሪያኑ1969 በአፖሎ 11 ተልዕኮ ሮኬቱ የት እና መቼ እንደሚወነጨፍ የሂሳብ ቀመር በመስራት  የመጀመሪያዎቹን ሶስት ሰዎች ወደ ጨረቃ ልካለች። ከዚህ አንፃር የአለን ሼፓርድ ታሪካዊ የሜርኩሪ በረራ እና የጆን ግሌን የምህዋር ተልዕኮዎች ያለ ካትሪን  የሂሳብ ቀመር  ስኬታቸው የሚታሰብ አልነበረም።

በአሁኑ ወቅትም ሴቶች በተለያዩ ሕዋ ነክ መስኮች የላቀ ብቃታቸውን ቀጥለዋል። እንደ ጁሊ ፔይቴ ያሉ መሐንዲሶች እና እንደ ዶ/ር ሳራ ሲገር ያሉ ሳይንቲስቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማዳበር እና ከፀሀይ ስርአታችን በላይ ለመኖር ስለሚችሉ ዓለማት ያለንን እውቀት በማስፋት ግንባር ቀደም ናቸው።
ምንም እንኳ ቁጥራቸው ዝቅተኛ ቢሆንም  ሴቶች ስለ ህዋ ያለውን ግንዛቤ በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ እና ለውጥ የሚያመጣ ሚና ተጫውተዋል። ሴት ጠፈርተኞች፣ መሐንዲሶች እና ሳይንቲስቶች  በጠፈር ምርምር ታሪክ ላይ  አሻራ ጥለዋል።
በዚህ ሁኔታ ከቫለንቲና ቴሬሽኮቫ የመጀመሪያ እርምጃ ጀምሮ በተለያዩ ሚናዎች  የሴቶች አስተዋፅኦ እና ተጽዕኖ እንደቀጠለ ነው።
አሁን ተራው የጀርመናዊቷ የሮቦቲክስ ተመራማሪ የራቢያ ሮጌ ነው።
«ከዚህ ተልዕኮ በኋላ አንዲት ሴት ሄይ! እኔም  ወደ ጠፈር መብረር እችላለሁ። ፍላጎቴንም እንዲሁ መከተል እችላለሁ። ብላ እንድታስብ ያደርጋል። ይህ በእኔ አስተያየት ፍጹም ድል ሆኖነው ያገኘሁት።»ብላለች ወጣቷ ተመራማሪ ራቢአ ሮጌ።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ