1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት ተቺ ጋዜጠኞች እስር መቀጠሉ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2015

ኢንተርኔትን መሠረት አድርገው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚሠሩ እና የመረጃ ትንተና የሚሰጡ ሦስት ሴቶችን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ሰሞኑን እየታሠሩ ይገኛሉ ። መምህርት እና «ኢትዮ ንቃት» የተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ መሥራች መስከረም አበራ ትናንት ምሽት የፌዴራል ፖሊስ መለዮ በለበሱ ሰዎች ለሦስተኛ ጊዜ መታሰሯን ባለቤቷ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4Ps7I
Illustration | Mikrofon in Ketten
ምስል Sorapop/Panthermedia/imago images

ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዙም ቀጥሏል

ኢንተርኔትን መሠረት አድርገው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚሠሩ እና የመረጃ ትንተና የሚሰጡ ሦስት ሴቶችን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ሰሞኑን እየታሠሩ ይገኛሉ ። መምህርት እና «ኢትዮ ንቃት» የተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ መሥራች መስከረም አበራ ትናንት ምሽት የፌዴራል ፖሊስ መለዮ በለበሱ ሰዎች ለሦስተኛ ጊዜ መታሰሯን ባለቤቷ ተናግረዋል ።  

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ለእሥር ከተዳረጉት ውስጥ አብዛኛዎቹ የተያዙት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝመሆኑን ማረጋገጡን ገልጾ፣ ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ወቅትም ሆነ ከተያዙ በኋላ ሰብዓዊ መብታቸው በተጠበቀ መልኩ ሕግን ተከትሎ እንዲሠራ «በአገር ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳይችሉ የሚደረጉ ጫናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ» ጠይቋል ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም «ከመረጃ ነፃነት አዋጅ አተገባበር ጋር ተያይዞ ተቋሙ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ብዙ ጊዜ ሲቃወም መቆየቱን አስታውቋል። ሆኖም ግን በሥራቸው ምክንያት የደረሰባቸውን እንግልት ወይም ሌላ ችግር አቤት ለማለት ወደ ተቋሙ የሚሄዱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችም ሆነ ተቋማት እንደሌሉ ገልጿል ።

በቅርቡ «ኢትዮ ንቃት» የተባለ የበይነ መረብ የመገናኛ ዐውታር ከፍተው ሲሰሩ የቆዩት መምህርት መስከረም አበራ ትናንት ምሽት ለጥያቄ ይፈለጋሉ በሚል ለሦስተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባለቤታቸው ፍፁም ገብረ ሚካኤል ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 

መምህርት መስከረም አበራ በተለይ በማህበራዊ እና መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ ወቅታዊ እና ፖለቲካዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን በመናገር ይታወቃሉ። ከዚህ በፊት በመጀመርያ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ብሔር ከብሔር ለማጋጨት ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ሲያበቃ መፈታታቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መጋቢት 29 ቀን፣ 2015 ዓ.ም "መንግስት የመዘዋወርና የሚዲያ ነጻነት መብትን በአግባቡ ሊያስከብር ይገባል"  በሚል ባወጣው መግለጫ አንድ የመጽሔት እና ሦስት የዩቲዩብ መገናኛ ዐውታር ሠራተኞች መታሠራቸውን አስታውቃል ። የኢሰመጉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ "ሰው በነፃነት የመዘግብ አቅሙ እንዲጠበቅ የተገባ ነው" ብለዋል። 

ጋዜጠኞች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግባቸው ወከባና እስር ሊቆም እንደሚገባ ተጠይቋል
ጋዜጠኞች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግባቸው ወከባና እስር ሊቆም እንደሚገባ ተጠይቋልምስል fikmik/YAY Images/IMAGO

ኢሰመጉ፦ ፖሊስ «EMS» የተባለ የመገናኛ ዐውታር ባልደረባን «ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት በመሞከር ጠርጥሬዋለሁ" የሚል ምክንያት ማቅረቡን ገልጿል። በተመሳሳይ «የአበሻ ወግ» የተባለ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የዓይኔ አበባ ግዛው በፖሊስ ተይዛ በእስር ላይ በነበረችበት ወቅት ለ3ቀን ምግብ ማግኘት እንዳልቻለች እንዲሁም ድብደባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደተፈጸመባት ኢሰመጉ ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል። 

«የአማራ ሚዲያ ማዕከል» የተባለ መገናኛ ዐውታር ዋና አዘጋጅ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተይዞ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሚገኝ እና ከቤተሰብ ውጪ ሌላ ሰው መጠየቅም ሆነ ስንቅ ማቀበል እንደማይችል፣ «የኔታ» በሚል የሚታወቅ ዩቱዩብ ዘጋቢት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተይዛ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስራ የምትገኝ ሲሆን ጋዜጠኛዋ ስትያዝ የፍርድ ቤት የመያዣ ወረቀት አሳዩኝ በማለቷና የያዟትን ሰዎች ማንነት በመጠየቋ ብቻ ድብደባ እና እንግልት እንደደረሰባት ኢሰመጉ ማረጋገጡን ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ከመረጃ ነፃነት አዋጅ አተገባበር ጋር ተያይዞ ተቋሙ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነትን ብዙ ጊዜ ሲቃወም ቆይቷል ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ይህንን መሠል ሥራዎች ከዚህ በፊት ማድረጉን ገልፀዋል።

መንግሥት መሰል እሥር ሲፈጽም በራሱ የሚያቀርባቸው የእሥር ምክንያቶች ቢኖሩም ጋዜጠኞችም ይሁን የመገናኛ ብዙኋን ተቋማት ደረሰብን የሚሉትን ወከባ እና የመብት ጥሰት ወደ ተቋማቸው ይዞ ሄዶ አቤት የማለት ልማድ አለመኖሩን ዋና እንባ ጠባቂ ገልፀዋል። 

ፖሊሶችም ሆኑ ሌሎች የሕግ አካላት ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ወቅትም ሆነ ከተያዙ በኋላየሕግ ሥርዓትን በተከተለና የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት በጠበቀ መልኩ እንዲሰሩ ያሳሰበው ኢሰመጉ «በአገር ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መስራት እንዳይችሉ በፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች የሚደረጉ ጫናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ» ሲል ጥሪ አድርጓል ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ