1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመቐለ ሀምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ሥራ አቆመ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 28 2014

ከትግራይና ከአማራ ክልሎች እንዲሁም ከኤርትራ ለሚመጡ ሕመምተኞች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመቐለ ሀምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ሥራ ማቆሙን ኃላፊው ገለጹ። የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ባለሙያዎች እርጉዞችን ለማዋለድ የሚያስፈልጋቸውን የእጅ ጓንት አጥበው ድጋሚ ለመጠቀም መገደዳቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/45Dw2
Äthiopien Opfer des Luftangriffs in Tigrai
ምስል Million Haileselassie/DW

የመድሐኒቶች እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት በትግራይ የጤና ተቋማት ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ

ላለፉት 16 አመታት ከትግራይ እና ከአማራ ክልሎች እንዲሁም ከኤርትራ ለሚመጡ ሕመምተኞች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመቐለ ሀምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ሥራ ማቆሙን ኃላፊው ገለጹ። በመቐለ የሚገኘው እና በመድሐኒቶች እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት በርካታ አገልግሎቶቹን ለማቋረጥ የተገደደው የአይደር ሆስፒታል ባለሙያዎች እርጉዞችን ለማዋለድ የሚያስፈልጋቸውን የእጅ ጓንት አጥበው ድጋሚ ለመጠቀም መገደዳቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ለአንድ አመት የተካሔደው ጦርነት በጤና ተቋማት ላይ ካደረሰው ውድመት እና የባለሙያዎች ጉዳት በተጨማሪ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ትግራይ የሚያመሩ መንገዶች በመዘጋታቸው አሳሳቢ የመድሐኒቶች እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት መከሰቱ ተገልጿል። በዚህም ከሪፈራል ሆስፒታል እስከ መካከለኛ ደረጃ ያላቸው የመንግሥት እና የግል የጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን እያቋረጡ እየተዘጉ ነው። 

የመቐለ ሀምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መላኩ አብርሃ "ላለፉት ስድስት ወራት የሕክምና መሣሪያ፤ የሰራተኛ ደሞዝ እና የተለያዩ የለት ተዕለት ወጪዎች ምንም ልናገኝ ስላልቻልን አሁን ልናስቀጥለው ከማንችልበት ደረጃ ደርሷል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ተቋሙ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ ምክንያት ፊስቱላ "በቁጥርም በአይነትም በከፋ መንገድ እየመጣ ነው" የሚሉት ዶክተር መላኩ "የሕክምና ቦታውም ቢኖር ባለሙያ አይኖርም። ባለሙያ ሲኖር ደግሞ መገልገያ ዕቃዎቹ በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም" በማለት አስረድተዋል። ኃላፊው "ፊስቱላ ድንበር የለሽ ነው። እኛ ከኤርትራም [ሕሙማን] መጥተው አክመናል። ይኸ ሥራ ለሚያውቀው ሰው ድንበር የለውም፤ ሐይማኖት የለውም። ዘር የምትለይበት በሽታ አይደለም" በማለት ተናግረዋል። 

Eingang des Mekele Fistula Center in Äthiopien
ምስል Fistula e.V.

የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ገብረስላሴ "በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት ምንም ነገር እንዳይወጣ እና እንዳይገባ ከተደረገ በኋላ ሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ እና እየዘጋ ነው የመጣው" ሲሉ ተቋማቸው የሚገኝበትን ደረጃ አስረድተዋል።

"ሆስፒታላችን አሉ ከሚባሉ ትልልቅ ሆስፒታሎች አንዱ ነው የነበረው። አሁን ግን አንድ ጤና ጣቢያ ከሚሰጠው አገልግሎት በላይ እየሰጠን አይደለም ያለንው። ይኸ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ደግሞ መድሐኒቶች እንዳይገቡ ክልከላ ስለተደረገ ነው" ያሉት ዶክተር ክብሮም በጀት ባለመኖሩ እንዲሁም ባንኮች በመዘጋታቸው ተቋሙ የሚያስፈልገውን መግዛት እንዳልቻለ ገልጸዋል። 
"የእርዳታ ድርጅቶች ገዝተው ሊያመጡልን የነበረ መድሐኒትም ከአፋር እንዳያልፍ ተከልክሏል። በዚህ ደግሞ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ ታካሚዎች፤ የስኳር መድሐኒት ሲያገኙ የነበሩ ታካሚዎች እየመለስናቸው ነው ያለንው" ብለዋል። 

ከትግራይ ጤና ተቋማት 80 በመቶ የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት መውደማቸው የሚገልፀው የትግራይ ጤና ቢሮ የተፈጠረው የመድሃኒት እና ሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ደግሞ ከውድመት የተረፉት ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጭ እያደረጋቸው እንደሚገኝ አስታውቋል። 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ