1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመረጃ ፍለጋን ያቀለለው ቻትጂፒቲ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2015

ቻትጂፒቲ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት የሚመራ እና መረጃን በቀላሉ ለማግኜት የሚያገለግል ዲጅታል መድረክ ነው።ይህ ቴክኖሎጅ በተወሳሰቡ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች ላይ ሁለገብ መረጃን በቀላሉ በማቀበል የመረጃ ፍለጋን በእጅጉ አሻሽሏል። በአንፃሩ የፈጠራ ስራዎችን አቀጨጨ በሚል ይተቻል።

https://p.dw.com/p/4QGbr
ChatGPT And Internet Companies Photo Illustrations
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

ቻትጂፒቲ የፈጠራ ስራዎችን አቀጨጨ በሚል ይተቻል

 የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት «ቻትጂፒቲ» በተባለው የሰው ሰራሽ አስተውሎ ቴክኖሎጅ አጠቃቀም ፣ምንነት እንዲሁም ጥቅም እና ጉዳት ላይ ያተኩራል። 
ቻትጂፒቲ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት የሚመራ እና መረጃን በቀላሉ ለማግኜት የሚያገለግል ዲጅታል መድረክ ነው።በዚህ ቴክኖሎጅ ልክ ከሰዎች ጋር እንደሚደረግ ውይይት ፤ በኮምፒዩተር፣በተንቀሳቃሽ ስልኮች ወይም በታብሌት አማካኝነት ቻትቦት ከሚባሉት ሰው ሰራሽ የመግባቢያ ችሎታ እንዲያዳብሩ ተደርገው ከተሰሩ የኮምፒዩተር ፕራግራሞች ጋር ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላል።በዚህ መሰሉ ውይይትም፤ ቻትቦቶች የሰው ልጅ የሚናገረውን ቋንቋ ተጠቅመው በፅሁፍ ወይም በንግግር የሰው ልጆች ከዲጂታል ቁሶች ጋር እንዲግባቡ ያደርጋሉ። ይህም ጥያቄዎችን ለመመለስ  እንዲሁም በኢሜል እና በድርሰት ጽሁፎች ላይም ሊያግዙ ይችላሉ።ከታሪክ እስከ ፍልስፍና፣ከሙዚቃ ድርሰት እስከ የኮምፒዩተር ኮዲንግ ድረስ በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መልስ ለመስጠት ያገለግላል።በዚህ መንገድ ቻትጂፒቲ /ChatGPT/ በተወሳሰቡ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች ላይ ሁለገብ መረጃን በቀላሉ በማቀበል ከዚህ ቀደም ጎግል ላይ የምንጠቀምበትን የመረጃ ፍለጋ በእጅጉ አሻሽሏል።በዚህ የተነሳ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለተለያዩ ጉዳዮች ይጠቀሙበታል።

Symbolbild KI | Künstliche Intelligenz
ምስል CHRISTIAN BEUTLER/KEYSTONE/picture alliance

በዚያው አኳያ ደግሞ የፈጠራ ስራዎችን አቀጨጨ በሚል ይተቻል።በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ሥነ ምግባር ፕሮፌሰር የሆኑት ዮዲት ሲሞን ከሚተቹት ውስጥ አንዷ ናቸው።
«በእውነቱ በጣም ትንሽ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠቀም ወይም አንዳንድ ጥያቄዎችን ወደ በይነገጽ በማስገባት የጥበብ ሥዕሎችን ምናልባትም ቪዲዮዎችን ማዘጋጀት ይችላሉ። ስለዚህ፣ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ላይ እየወደቁ ነው።ለምሳሌ ስለአዉቶማቲክ ማባዛት መናገር እችላለሁ።»
መቀመጫውን አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ባደረገው ኦፕንኤይ/OpnenAI/ በተባለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኩባንያ የተሰራው ይህ ቴክኖሎጅ በጎርጎሪያኑ ህዳር 2022 ዓ/ም ለአገልግሎት የበቃ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ተቀባይነትን አግኝቷል።

Künstliche Intelligenz Symbolbild
ምስል Taidgh Barron/ZUMAPRESS.com/picture alliance

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ሴም አልትማን እንደገለጹት ይህ ቴክኖሎጅ ይፋ በሆነ  በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ነበሩት። ጎግል እና ማይክሮሶፍትን የመሳሰሉ ኩባንያዎችም ቴክኖሎጅውን በመጠቀም አገልግሎታቸውን ለማሳደግ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማፍሰስ መርሃግብሮች ነድፈው ይሰራሉ። ነገር ግን ቻትጂፒቲን ጨምሮ ሌሎች በሰው ሰራሽ አስተውት ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጅዎች ሰዎችን ተክተው በመስራት የስራ አጥ ቁጥርን በመጨመር ሌላው የሚተቹበት ውሱኑነት ነው። በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር ዮዲት የሰውሰራሽ አስተዉሎት የትኛውንም ሙያ ሊነካ ይችላል።የሚል ስጋት አላቸው።
 «የትኛውም ሙያ በእውነት አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አይደለም። ታውቃላችሁ በቅጽበት መባዛት የሚችሉት የስራዎቻችን ገፅታዎች እና  ክፍሎች በቀላሉ በማሽኖች ሊባዙ ይችላሉ።ቴክኖሎጂ በአጠቃላይ ሁልጊዜ ራሱን የሚሸጠው ስራን በመቀነስ እና ሰዎችን ለሌሎች ጉዳዮች ከስራ ነፃ ለማድረግ ቃል በመግባት ነው።ነገር ግን በጭራሽ ያ አልተከሰተም።

Symbolbild KI | Künstliche Intelligenz
ምስል MARCO BERTORELLO/AFP/Getty Images

ቻትጂፒቲ በአብዛኛው አገለግሎቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ  ሲሆን፤ በዚህ ዲጅታል መድረክ ለመጠቀም ከኩባንያው ድረ ገፅ  በነፃ በማውረድ የሚቻል ሲሆን፤ ለተሻለ አጠቃቀም የላቀ ውሂብ ያላቸው በግዥ መልክ የሚቀርቡም አሉ።ተጠቃሚው የሚፈልገውን ጥያቄ በመጠየቅ በአጭር ጊዜ የተደራጀ መልስ ማግኘቱ የዚህ ቴክኖሎጅ አንዱ ጥቅም ቢሆንም፤ የቃላትን እማሪያዊና ፍካሪያዊ ፍቺ እንዲሁም የምፀት እና የስላቅ እንዲሁም ውስብስብ ፅሁፎችን በተመለከተ ውጤታማ አለመሆኑም ይጠቀሳል። ከግማሽ ትሪሊዮን በላይ የተከማቹ ቃላት እንዳሉት የሚነገርለት ይህ ቴክኖሎጅ አንዳንድ ጊዜም ከተወሰኑ ቃላት በላይ በመቁረጥ የተሳሳሳቱ መረጃዎችን ሊሰጥ ይችላል። ይህም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ከሄልሲኒኪ ዩንቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ቲሙ ሩስ  ያስረዳሉ።  
«ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎች በበይነመረብ ስለመኖራቸው ይነገራል።ይህም በአሁኑ ጊዜ በዋናነት የሚታይ ነው።  ታውቃላችሁ ማህበራዊ ትስስሮች  ውስጥ, የተሳሳተ መረጃ የሚፈበርኩ እና በበይነመረብ ዉይይቶች፣ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ጣልቃ የሚገቡ ብዙ ሰዎችም አሉ።.ይህ ሊሆን ከቻለ  እና ይህም በፍጥነት እና በስፋት የሚባዛ ከሆነ ፤በእርግጥ ይህ አይነቱ ጉዳይ አዲስ የአሳሳቢነት ደረጃ ነው።»
በሌላ በኩል የቻትጂፒ የሰውሰራሽ አስተውሎት በመመሪያና በህግ ያልታሰረ በመሆኑ እንደ አውሮፓ ህብረት ባሉ ድርጅቶችም ክርክር አስነስቷል። የተለያዩ የኅብረቱ አባል ሀገሮች የተወሰኑ ቻትቦቶችን ማገድ ወይም አገልግሎታቸውን መወሰን  ላይ እየመከሩ ነው።
ያለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ጣሊያን መረጃቸውን ለተጠቃሚዎቹ የበለጠ ግልፅ እንዲያደርግ ሶፍትዌሩን የበለጠ እንዲያዳብር እና በልጆች አጠቃቀም ከወላጆች ፈቃድ እንዲጠይቅ የሚሉ ቅደመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ቻትጂፒቲን በጊዚያዊነት አግዳለች።ስፔን እና ፈረንሳይም በዚህ ቴክኖሎጅ ጥርጣሬ እንደገባቸው እየገለፁ ነው። የሕግ አውጪዎችም ኅብረቱ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት ላይ በተመሰረቱ ዲጅታል መድረኮች ላይ ግልጽ የሆነ ደንብ ሊኖረው ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ።

KI im Tourismus l Open AI logo - ChatGPT
ምስል Avishek Das/SOPA Images via ZUMA Press Wire/picture alliance

ያምሆኖ የአውሮፓ ኮሚሽን እና ፓርላማ በተጠቃሚዎች ጥበቃ ደንብ እና በኢኮኖሚ እና በነጻ የምርምር  ልማት መካከል ሚዛን ለመጠበቅ እየሞከሩ ነው።የአውሮፓ ህብረት የውስጥ ገበያ ኮሚሽነር ቲዬሪ ብሬተን እንደገለፁት የሰውሰራሽ ልህቀት በዲጂታል ማህበረሰብ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ አቅም አቅራቢ ነው። ከሁለት አመት በፊት የህብረቱ ህግ በቀረበበት ወቅትም አልሚዎችን ማራቅ ሳይሆን ማሳመን እንደሚፈልግ  አመልክቷል።ፕሮፌሰር ዮዲት ሲሞን ግን ሁሉም ነገር ለቴክኖሎጅ ኩባንያዎች መተው የለበትም ባይ ናቸው።
 «የተወሰነ ሚና አለ። ፖለቲካ እና የሕግ አውጪዎች የሚጫወቱት የተወሰነ ሚና እና ኃላፊነት አለ።ህጎችን ለማውጣት እና  ሀላፊነት ያለው የአጠቃቀም፣ መሰራት ያለበትን እና የሌለበትን ድንበሮችን ለማበጀት። እንዲሁም  የፈለጉትን እንዲያደርጉ ሁሉን ነገር ለኩባንያዎች መተው የለበትም።»
ከሄልሲኒኪ ዩንቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ቲሙ ሩስ በበኩላቸው ነባር ህጎች መከለስ አለባቸው ይላሉ።
«ማህበረሰቡ የሚንቀሳቀሰው በራሱ ህጎች እና ነገሮችን ለማከናወን በጋራ በተስማማባቸው  መንገዶች ነው። እንደማስበው ወደዚያ  የገባን ይመስለኛል። እንደዚህ ያሉትን ህጎች መከለስ አለብን።»
በብራዚል የሪዮዲጄኒሪዮ የቴክኖሎጂ እና ማህበረሰብ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሰሊና ቡቲና  ደግሞ በቴክኖሎጅ መመሪያ ዝግጅት የተለያዩ አካላት ሊሳተፉ ይገባል በማለት ያስረዳሉ።
«በእውነቱ የምንፈልገው ነገር መመሪያ እንዲኖረን ፣ሀላፊነት እንዲሰማን እንዲሁም ሰውሰራሽ አስተውሎትን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን ነው።የቴክኖሎጂን ደንብ በተመለከተ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በሚሰሩ ሰዎች መዘጋጄት አለበት። የቴክኖሎጅ አልሚዎችን ጨምሮ፣ከኢንዱስትሪ፣ከትምህርት ዘርፍ ሰዎችን ማካተት።የህግ አውጭዎች ብቻ ሳይሆን የእነሱ ስራም ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል ።»

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ