1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዋና ዋና ዜና

Tamirat Geletaቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2016

https://p.dw.com/p/4iFvh

 

በናይሮቢ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ተቆራርጦ የተጣሉ የሰዎች አስክሬኖች ከተገኑ በኋላ የፖሊስ እጅ ይኖርበት እንደሁ እያመረመረ መሆኑን  የኬንያ ፖሊስ ተከታታይ ቡድን አስታወቀ። 

የተከታታይ ቡድኑ ምርመራ የተሰማው የኬንያ ፖሊስ ትናንት አርብ በመዲናዋ ሙኩሩ በተባለ የከተማዋ  ደቡባዊ ክፍል ብርቱ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ የተገደሉ የስድስት ሴቶች አስክሬን በከረጢት ታስሮ በቆሻሻ ቦታ ካገኘ በኋላ ነው ።

ገለልተኛው የፖሊስ ተከታታዩ ቡድን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ አይ ፒ ኦ ኤ እንዳለው በጸረ መንግስት ተቃውሞ ወቅት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የተሰወሩ ሰዎችን ጉዳይ እየመረመርኩ ነው ብሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የዘጠኝ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ያስታወቀው የፖሊስ ስራ ተከታታይ ቡድኑ  አይ ፒ ኦ ኤ ሰባቱ ሴቶች መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል። ቡድኑ ማንነታቸውን በማጣራት ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል።

ባለፈው ወር በወጣቶች በተቀሰቀሱ ሰልፎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የኬንያ ፖሊስ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገበት ነው። የመብት ተሟጋቹ ቡድን  ፖሊስ  ከልክ ያለፈ ሃይል ተጠቅመዋል ሲል ይከሳል።

በሀገሪቱ በተቀጣጠለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ በርካቶች መሞታቸውን ተከትሎ ጠንካራ ትችት የተሰነዘረባቸው የፖሊስ አዛዥ ጃፌት ኮሜ ትናንት ዐርብ  የስንብት ደብዳቤ አስገብተዋል። ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶም የኮሜን የስንብት ደብዳቤ መቀበላቸው ተረጋግጧል

 

ሞቃዲሾ ውስጥ እስር ቤት ሰብረው ለማምለጥ የሞከሩ አምስት የአልሸባብ አባላት መገደላቸውን የማረሚያ ቤቱ ባለስልጣናት አስታወቁ ።

በሙከራው በነበረው የተኩስ ልውውጥ ሶስት የጥበቃ አባላትም ተገድለዋል። በተቀናጀ መንገድ የጦር መሳሪያ ማግኘት ችለው እንደነበር የተነገረላቸው እስረኞቹ ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች ጋር ተኩስ ከገጠሙ በኋላ መገደላቸውን የሶማሊያ የጥበቃ ኃላፊ መሐመድ ሀሰን ተናግረዋል ።

ከእስር የማምለጥ ሙከራው ሌሎች 21 የእስረኞቹ ተባባሪ ነበሩ የተባሉ ሰዎች  መቁሰላቸውን ኃላፊውን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በሙከራው ከእስር ቤቱ ማምለጥ የቻለ እስረኛ እንደሌለም የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል

በእስር ቤቱ ያለው ሁኔታ ወደ መረጋጋት መመለሱን የገለጹት ባለስልጣናት ከእስር የማምለጥ ሙከራው እየተመረመረ ነው ብለዋል። የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት በአሜሪካ የአየር ድጋፍ ከየአካባቢው የጎሳ ሚሊሻዎች ጋር በመተባበር ከአልሸባብ ጋር እየተዋጋ ይገኛል። እንደዚያም ሆኖ ግን በአንዳንድ አውደ ዉጊያዎች ድል እየተቀዳጀ መሆኑን የሚገልጸው አልሸባብ በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል በርካታ ቦታዎችን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን አስታውቋል።

አልሸባብ ከከደካማው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባ ከ17 ዓመታት በላይ ተቆጠረ።

 

እስራኤል የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥን ዒላማ ያደረገ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ካስታወቀች በኋላ ሐማስ ጥቃቱን ሐሰት ነው በማለት አስተባብሏል።

ሐማስ ማስተባበያውን ያወጣው የእስራኤል ባለስልጣናት የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መሐመድ ደኢፍ የአየር ጥቃት ዒላማ መደረጉን ዛሬ ካስታወቁ በኋላ ነው ።

 ሐማስ በዛሬው መግለጫው እንዳለው እስራኤል የወታደራዊ መሪዎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች መፈጸሟን ስትገልጽ የመጀመሪያዋ አይደለም ፤ ነገር ግን በወታደራዊ አዛዡ ላይ የደረሰ ጥቃት የለም ብሏል። የእስራኤል ባለስልጣናትም ቢሆኑ ሁለት ወታደራዊ አዛዦቹ  ኢላማ መደረጋቸውን ከመግለጽ ባለፈ ስለመገደላቸውም ሆነ ስላሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ያሉት ነገር የለም። እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ካን ዩኑስ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 71 ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን የፍልስጥኤማውያኑ የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በጥቃቱ በሌሎች 289 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።  

 

በሳህል ሃገራት ከአልቃኢዳ እና ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት ባላቸው አክራሪ ኃይላት የተስፋፋው ሽብርተኝነት እና የተደራጁ ወንጀሎች በቀጣናው ብርቱ ስጋት መደቀናቸው የተመድ አስታወቀ።

የሽብር ጥቃቶች እና የተደራጁ ወንጀሎቹ ወደ ተቀሩ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት እንዳይስፋፉ እንዳሰጋቸው በቀጣናው የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ ልዑክ አስጠንቅቀዋል። በቀጣናው በሽብርተኝነት ላይ እየደረገ ያለው ዘመቻ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ እንዳላመጣ የገለጹት ልዩ ልዑኩ ሊዎናርዶ ሲማኦ በሳህል ሃገራት የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውሩን ለመግታት ተጨማሪ የፖሊስ ስምሪት መጠየቁን አመልክተዋል።

ሽብርተኞቹ «መድሃኒት ፣ የጦር መሳሪያ ፣ ማዕድናት እና ሰዎችን »  በተደራጀ መንገድ  በማዘዋወር ላይ እንደሚገኙም ነው ልዑኩ የጠቆሙት ።

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ አዲስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በሳህል እና የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የጎርጎርሳዉያኑ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ በተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ከእነርሱ ውስጥ አብዛኞቹ ሲቪላውያን ናቸው ።

 

አሜሪካ የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎቿን ጀርመን የምትተክል ከሆነ በአጸፋው የአውሮጳ ዋና ዋና ከተሞችን ዒላማ ለማድረግ እገደዳለሁ ስትል ሩስያ አስጠነቀቀች።

ሩስያ ለአሜሪካ የምትሰጠውን የአጸፋ እርምጃ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ጋር አመሳስላዋለች።

የአሜሪካ በጀርመን ሚሳኤል መትከል አስመልከተው የክሬምሊን ቃል አቃባዩ ዲሜትሪ ፔስኮቭ  «አውሮጳ በእኛ ላይ ያነጣጠሩ ሚሳኤሎች ሲታጠቁ የእኛም ሚሳኤሎች በአውሮጳ ዋና ዋና ከተሞች ያነጣጥራሉ» ብለዋል። ቃል አቀባዩ በአንድ የሩስያ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በሰጡት አስተያየት ሚሳኤሎቹን ለመያዝ በቂ አቅም አለን ፤ ነገር ግን ተጎጂዎቹ የእነዚሁ ሃገራት ዋና ዋና ከተሞች ናቸው ፣ ብለዋል። አሜሪካ ባለፈው ረቡዕ በሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት ኔቶ ጉባኤ ላይ ይፋ እንዳደረገችው ከሆነ ከጎርጎርሳዉያኑ 2026 ጀምሮ ቶሃውቭክ የተሰኘውን የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ክሩዝ ሚሳኤልን ጨምሮ የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎቿን ጀርመን ውስጥ የመትከል ዕቅድ ይዛለች።

ሩስያ የአሜሪካንን እርምጃ በመተቸት ወደ ሌላ የቀዝቃዛው ጦርነት አንድ እርምጃ እየገፋችን ነው ብላለች። በዩክሬን ጦርነት ውስጥም በቀጥታ እየተሳተፈች ነው ስትል ከሳለች።

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።