1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Shewaye Legesseሐሙስ፣ ሐምሌ 25 2016

በአዲስ አበባ ከተማና ኦሮሚያ ክልል የብር አቅም መዳከምን ተከትሎ በሸቀጦች ላይ ዋጋ ጭማሪ ያደረጉ በርካታ የንግድ ድርጅቶች መዘጋታቸው ተገለጸ። በጸጥታ ችግር ምክንያት ለፈተና በሄዱበት ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ሳምንታት ያህል መቆየት የተገደዱት ከ400 በላይ ተማሪዎች ትናንት ማምሻውን ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ተሰማ። የናይጀሪያ ፖሊስ በሀገሪቱ የተባባሰውን የዋጋ ንረትና የአስተዳደር ችግር በመቃወም አደባባይ ከወጡ ሰልፈኞች ጋር ፍጥጫ ገጥሟል። ትናንት ለተገደሉት የሃማሱ መሪ በኢራን ብሔራዊ የአስክሬን ሽኝት ሥረዓት ተከናወነ። አዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት መንግሥታቸው ለሃማስ የሚያደርገው ድጋፍ ይጨምራል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4j15N

አዲስ አበባ፤ ባለሥልጣናት የብር የመግዛት አቅም በመቀነሱ ዋጋ በጨመሩ ላይ እምርጃ መውሰዳቸው

በአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል የብር አቅም መዳከምን ተከትሎ በሸቀጦች ላይ ዋጋ ጭማሪ ያደረጉ በርካታ የንግድ ድርጅቶች መዘጋታቸው ተገለጸ። ሮይተርስ እንደዘገበው የንግድ ድርጅቶቹ የተዘጉት ብሔራዊ ባንክ የውጭ ገንዘብ የምንዛሪ ተመንን ከመለወጡ አስቀድሞ ባከማቿቸው የምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ነው። የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ ቃል አቀባይ ሰውነት አየለ ለሮይተርስ እንደገለጹት በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ ላይ ብቻ 71 ድርጅቶች ተዘግተዋል። በተመሳሳይ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ 19 የንግድ ድርጅቶች መዘጋታቸውን እና ሦስት ሰዎችም መታሠራቸውን የኦሮሚያ የንግድ ቢሮ ሀላፊ መሠረት አሰፋ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል። እንደ ዘገባው ዋጋ ከተጨመረባቸው መካከል ዘይት እና ሩዝ ቀዳሚዎቹ ናቸው። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ ገበያ መር የምንዛሪ ተመንን ተግባራዊ ካደረገ ወዲህ የሀገሪቱ ሸርፍ የሆነው ብር ከዶላር አንጻር 28 በመቶ መዳከሙን ነው ሮይተርስ ያመለከተው። ይህ ውሳኔም የሀገሪቱ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ብድር መርሃ ግብር አዲስ ብድር ለማግኘት እንዲሁም የዕዳ መመለሻ ጊዜንም ለማስተካከል ያለመ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ይህ የመንግሥት ውሳኔ እና እርምጃ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው ሕዝብ ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።  

 

ሰላሌ፤ ለፈተና ከሄዱበት መመለስ ያልቻሉት ተማሪዎች ወደቤተሰባቸው መመለስ

በጸጥታ ችግር ምክንያት ለፈተና በሄዱበት ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ሳምንታት ያህል መቆየት የተገደዱት ተማሪዎች ትናንት ማምሻውን ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ተሰማ። ከ400 በላይ እንደሚሆኑ የተነገረው የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ግጭት ከሚካሄድበት የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ነበር ወደ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የተጓዙት።

ተማሪዎቹ ከሁለት ሳምንታት በፊት የ12ኛ ክፍል ፈተናቸውን ፊቼ ከተማ በሚገኘው በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ካጠናቀቁ በኋላ በፀጥታው ይዞታ ስጋት መመለሻ በማጣታቸው በዩኒቨርሲቲው ለመቆየት ተገደው ነበር። የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶ/ር የሺእመቤት ቦጋለ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ ወደ መጡበት እንዲመሰለሱ የተደረገው ለፈተናው ባመጧቸው አካላት አማካኝነት ነው።

ዳይሬክተሯ አክለውም በትናንትናው ዕለት ተማሪዎቹ ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ሙሉ በሙሉ ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተወስደው በሰላም ወደ ወላጆቻቸው መድረሳቸውን አረጋግጠናል ብለዋል። በሰላሌ ዩኒቨርሲቲም የቀረ አንድም የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ እንደሌለም አመልክተዋል። ለሁለት ሳምንት እና ከዚያ በላይ በዩኒቨርሲቲው ለመቆየት የተደገዱት ከደራ ወረዳ ሦስት ትምህርት ቤቶች የመጡ የማኅበራዊና ተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መሆናቸውን መግለጻቸውንም ከአዲስ አበባ ሥዩም ጌቱ በላከው ዜና ጠቅሷል።

 

አቡጃ፤ የኑሮ ውድነት ያቀጣጠለው ተቃውሞ በናይጀሪያ

የናይጀሪያ ፖሊስ በሀገሪቱ የተባባሰውን የዋጋ ንረትና የአስተዳደር ችግር በመቃወም አደባባይ ከወጡ ሰልፈኞች ጋር ፍጥጫ ገጥሟል። አቡጃ ላይ ሰልፈኞቹን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ተገልጿል። የተቃውሞ ሰልፉ በተለይ በዋና ከተማ አቡጃ፣ በንግድ ማዕከሏ ሌጎስና ሌሎችም የናይጀሪያ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን የፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ የኤኮኖሚ ማሻሻያ በሀገሪቱ የከፋ የዋጋ ግሽበትና በተራው የሀገሪቱ ዜጋ ኑሮ ላይ ጫና ማስከተሉ ዜጎችን አስቆጥቷል። ፕሬዝደንት ቲኒቡ ሀገሪቱ እንድትቀጥል ለውጥ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ዝተዋል። ባለሥልጣናት በየከተሞቹ ጥቃት እንዳይፈጸም የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎችን አሰማርተዋል። ሌጎስ ላይ የታጠቁ ፖሊሶች ሰልፈኞቹ ወደ መንግሥት ጽሕፈት ቤት እና ለሰላማዊ ሰልፍ ወደተፈቀደ ስፍራ ሲጓዙ ሲመለከቱ እንደነበር ተገልጿል። አቡጃ ላይ ወታደሩ ዋና መንገዶችን ዘግቷል። የናይጀሪያ መንግሥት ከተቃውሞው አስቀድሞ ለውይይት ክፍት መሆኑን ገልጾ ነበር። ፕሬዝደንቱም ሕዝቡ እሳቸው የጀመሩትን ማሻሻያ እንዲታገስ ጠይቀው ነበር። ሆኖም ሕዝቡ ፖለቲከኞቹ በቂ መስዋዕትነት አልከፈሉም በማለት ይተቻሉ።

 

ቴህራን፤ የሃማሱ መሪ አስከሬን ሽኝትና የሂዝቦላ የጦር አዛዥ መገደል

ኢራን ትናንት ሌሊት ለተገደሉት የሃማሱ መሪ እስማኤል ሃኒያ ብሔራዊ የአስክሬን ሽኝት ስነሥረዓት አከናወነች። አዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት ማሱድ ፔዜሽኪያን መንግሥታቸው ለሃማስ የሚያደርገው ድጋፍ ይበልጥ እንደሚጨምር ተናግረዋል። ከሃማስ የበላይ ሀላፊዎች ጋር በስልክ የተነጋገሩት ፕሬዝደንቱ፣ የእስማኤል ሃኒያን ግድያ «የሽብር ድርጊት» ነው ማለታቸውን የኢራን የዜና አውታር ኢርና ዘግቧል። ኢራን እና ሀማስ ለሃኒያ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል። እንዲያም ሆኖ እስራኤል በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር የለም።  በአስከሬን ሽኝቱ ላይ የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ሃሚኒ እና ፕሬዚዳንት ፕዜሽካንን ጨምሮ የሀገሪቱ ፖለቲካኞች እና ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም አንድ ከፍተኛ የሂዝቦላህ የጦር አዛዥ ከትናንት በስተያ መገደላቸው ተነግሯል። ከሂዝቦላህ መስራች አባላት አንዱ እንደነበሩ የተገለጸው ፉአድ ሹኩር፣ ቤይሩት ውስጥ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ነው የተገለጸው። የፉአድ ሽኩር ሞት ለሂዝቦላህ አመራር ከባድ ጉዳት እንደሆነ ሮይተርስ በዜናው ጠቅሷል። ዩናይትድ ስቴትስ ሽኩር ለ241 የአሜሪካ ወታደሮች መገደል ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ገልጻለች። እስራኤል በበኩሏ ለበርካታ እስራኤላውያን ሞት ተጠያቂ ናቸው ብላለች።

 

አንካራ፤ የሩሲያ እና ምዕራባዊ ሃገራት የእስረኞች ልውውጥ

በስድስት ምዕራባዊ ሃገራት እና በሩሲያ መካከል በዛሬው ዕለት አንካራ ቱርክየ ላይ የእስረኞች ልውውጥ ተደረገ። በውሉ መሠረትም ሁለት ልጆችን ጨምሮ 10 ሩሲያውያን እስረኞች ለቱርክየ ፕዝደንታዊ ቢሮ የተሰጡ ሲሆን፤ በለውጡ በሞስኮ እጅ የነበሩ 16 የምዕራብ ሃገራት ዜጎች መለቀቃቸው ከአንካራ ይፋ ሆኗል። በሩሲያ ተይዘው ከቆዩት መካከል የዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛ ኤቫን ገርሽኮቭስኪ አንዱ መሆኑ ተገልጿል። ጋዜጠኛው ከሳምንት በፊት በቀረበበት የስለላ ክስ በሩሲያ ፍርድ ቤት የ16 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር። እስረኞቹ ባጠቃላይ ከአሜሪካ፤ ከጀርመን፤ ከፖላንድ፤ ከስሎቬኒያ፣ ኖርዌይ፤ ቤላሩስ እና ሩሲያ ነው ወደ አንካራ የተወሰዱት። በሩሲያ ተይዘው ከተለቀቁት 13ቱ ወደ ጀርመን ሦስቱ ደግሞ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጓዛቸው ተገልጿል።

 

ፓሪስ፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች ይካሄዳሉ

33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን እያስተናገደ ነው። በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉባቸው የፍጻሜ እና የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ከእነዚህ መካከል ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ የሚካሄደው የወዶች የ10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ይጠበቃል። በዚህ ውድድር የቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊው ሰለሞን ባረጋ እንዲሁም አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊም ይሳተፋሉ።

በማጣሪያ ውድድሮች  ምሽት 1 ሰዓት ከ10 ላይ የሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ፣ 2 ሰዓት ከ45 ላይ ደግሞ የሴቶች የ800 ሜትር ውድድሮ ይደረጋሉ። በሴቶች 5 ሺህ ሜትር አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ ፣ መዲና ኢሳ እና እጅጋየሁ ታዬ ይካፈላሉ። በ800 ሜትር አትሌት ፅጌ ዱጉማ ፣ ሀብታም ዓለሙ እና ወርቅነሽ መለሰ ተሰላፊዎች ናቸው።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው የወንዶች የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር አትሌት ምስጋናው ዋኩማ በስድስተኝነት አጠናቋል። ያስመዘገበው ሰዓት ለኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ክብረ ወሰን መሆኑ ነው የተነገረው። ዛሬ ለፍጻሜም ሆነ ለማጣሪያ የሩጫ ውድድር ለመሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መልካም ዕድል እንመኛለን።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።