1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 22 ቀን 2016 የዓለም ዜና

Lidet Abebeሰኞ፣ ሐምሌ 22 2016

* በሲዳማ ክልል በተከሰተ የመሬት መንሸራታት 11 ሰዎች ሞቱ * የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ላይ ማሻሻያ አደረገ *የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት ውሳኔዎች አስተላለፈ *ፆታዊ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሱዳን *እስራኤል፤ በሂዝቦላህ ላይ ወታደራዊ ርምጃ ለመውሰድ ወሰነች * ፈረንሳይ፤ በኢንተርኔት አገልግሎት መስመሮች ላይ ጥቃት ተፈፀመ

https://p.dw.com/p/4isYB

በሲዳማ ክልል በተከሰተ የመሬት መንሸራታት 11 ሰዎች ሞቱ

በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራታት አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 11 ደረሰ። በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል።  ትናንት ሌሊት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት መንስዔ በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ ሲሆን አደጋው የደረሰው በወረዳው ግሽሬ፤ ጉዱሞ ቀበሌ ውስጥ መሆኑን የወረዳው ባለሥልጣናት ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል ፡፡ 
« በዚህ አደጋ 16  የሚጠጉ ሰዎች ናቸው የተጎዱት ።ከነዚህ ውስጥ  የ10 ሰዎች ህይወት አልፏል። የስምንቱ አስክሬን ተገንቷል። የመሬት መንሸራተቱ የደረሰበት ቦታ ትልቅ ወንዝ ስላለ የተሸራተተው መሬት የሁለቱ ሰዎች ህይወት ይዞ ሄዷል ።» የወንሾ ወረዳ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከያሙ ኪምቢቻ አክለው እንደገፁት በቤት እንስሶች እና ንብረት ላይም ከባድ አደጋ ደርሷል።
በስተበደቡባዊ የኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ ከሚከሰት የመሬት እና የጎርፍ አደጋዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜትሮሎጂ አገልግሎት እያሳሰበ ይገኛል ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ሰኞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በተከሰተው አስከፊ የመሬት መንሸራተት  ከ230 በላይ ሰዎች አስክሬን ተገኝቶ መቀበሩን የፌደራል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መግለፁ ይታወሳል።  በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን  500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ላይ ማሻሻያ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ስርአቱ ላይ ማሻሻያዎች አደረገ። ባንኩ ዛሬ እንዳስታወቀው የተደረጉት ማሻሻያዎች በሀገሪቱ መንግሥት ትናንት ይፋ የሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንዱ አካል ነው። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓት ትከተላለች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አበዕት ያላቸውን 13  የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያዎች ያስታወቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፤  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና ገበያውን የማረጋጋት ብቻ ይሆናል፣ ተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲቋቋሙ እና የስራ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፣  ቀደም ሲል በ 38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረውም እገዳ ይነሳል። 
ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከውጭ የሚላክላቸውን የኃዋላ ገንዘብ ወይም ክፍያ በውጭ ሀገር ገንዘብ አካውንት ከፍተው ማስቀመጥ ወይም በዛ ገንዘብ መገበያየት ያስችላቸዋል።
ከዛሬ አንስቶ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ማሻሻያ ተከትሎ የብር ምንዛሪ ዛሬ በ30 በመቶ ዋጋው ሊቀንስ ችሏል።  

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት ውሳኔዎች አስተላለፈ

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት በከተማዋ የሚታዩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ያስችላል ያለውን ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ የፀጥታ ምክር ቤቱ ትናንት ባሰራጨው መረጃ እንዳመለከተው በተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ፣ በጦር መሳሪያ አያያዝ፣ በቤት አከራዮችና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ክልከላዎችንና ግዴታዎችን አስቀምጧል፡፡
ምክር ቤቱ ማንኛውም ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ (ባጃጅ) ለዝናብ እና ለነፋስ በሚል በግራና በቀኝ  እንደመጋረጃ የሚጠቀሙበትን ሸራ እንዳይጠቀሙ ከልክሏል፣ የመንቀሳቀሻ ጊዜያቸውም ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ብቻ እንዲሆን እገዳ ጥሏል፡፡ በባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች ላይ የተጣለውን የሸራ ማንሳትና የሰዓት ገደብ በተመለከተ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ውሳኔው ወቅቱን ያላገናዘበ ነው ሲሉ ይቃወሙታል፡፡ « ክረምት ነው። አብዛኛው ሰው ዝናብ እየመታው መሄድ አይችልም። በዚህ ሰዓት ደግሞ ደንበኛ ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም። የወጣው አዋጅ ትክክለኛ ያልሆነ እና ህብረተሰቡን ያላገናዘበ ነው። በዚህ የዝናብ ሰዓት አምሽተው የሚገቡ ብዙ ሰዎች አሉ። እና ሰዓቱ መሻሻል አለበት።»
ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶች ላልተወሰነ ጊዜ ድረስ በከተማዋ እንዳይሽከረከሩ የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ምክር ቤት አሳውቋል፡፡እግረኞችን ጨምሮ የመንግሥትም ሆነ የግለሰብ ማንኛዉም አይነት ተሽከርካሪዎች፣ እስከ ምሽት 3 ሰዓት ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ መመርያዉ አዟል፡፡ በፀጥታ ስራ ላይ የተሰማሩ አምቡላንሶች እና የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች ግን ይህ እገዳ አይመለከታቸውም ተብሏል። ይሁንና በማነኛውም ጊዜ ፍተሻ ሊደረግባቸዉ እንደሚችል ተመልክቶአል። 
የፀጥታ ምክር ቤቱ ከፀጥታ አስከባሪ አካላት ውጪ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል አክሎ አስታዉቋል።  ቤት አከራዮችም የተከራዮቻቸውን ማንነት ለሚኖሩበት ቀበሌና ፖሊስ ጣቢያ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸዉ ጠቅሷል፡፡ 
በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ለሚፈፀሙ ውንብድና እና ዘረፋ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች ዋና አጋዥ ሆነው እንደሚጠቀሱ የባህር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዜና ያመላክታል።
 

ፆታዊ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሱዳን

በሱዳን ያሉ ተፋላሚ ኃይሎች ፆታዊ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ሲል  የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት "ሂዩማን ራይትስ ዎች" ወነጀለ።  በተለይ ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጋር እየተዋጋ የሚገኘው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በምህፃሩ  RSF ሴቶችን በቡድን መድፈርን ጨምሮ በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሟል፣ ሴት ልጆችም በግዳጅ ጋብቻ እንዲፈፅሙ አድርጓል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በሱዳን ከ15 ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት «ማብቂያ ምልክት አይታይም» ያለው  ሂውማን ራይትስ ዎች በዘገባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እና የአፍሪካ ህብረት የሲቪሉን ማህበረሰብ ለመታደግ የጋራ ተልዕኮ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖች የወነጀለው ድርጅቱ ተጎጂዎች ወሳኝ የሆነ የድንገተኛ ጊዜ ህክምና እንዳያገኙ እና የጦር ኃይሉም ሆነ ብሎ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አካባቢዎች የሰብአዊ ርዳታዎች እና የህክምና መገልገያዎች እንዳይገቡ ከጥቅምት ወር አንስቶ ከልክሏል ሲል ወቅሷል።
 

እስራኤል፤ በሂዝቦላህ ላይ ወታደራዊ ርምጃ ለመውሰድ ወሰነች

የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ በሂዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ዛሬ ተስማማ። ካቢኔው የተሰበሰበው የእስራኤል ይዞታ ወደሆነው ጎላን ተራራ ሮኬቶች ከሊባኖስ ከተወነጨፈ እና ቢያንስ 12 ህፃናት ቅዳሜ ዕለት ከተገደሉ በኋላ ነው። ካቢኔው ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጆአቭ ጋላንት አሸባሪ የተባለው ሂዝቦላ ላይ የሚወሰደውን ርምጃ እና የጊዜ ሰሌዳ እንዲወስኑ ስልጣን ሰጥቷቸዋል። ሂዝቦላህ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጀርመን እና በተለያዩ የአረብ ሀገራት በአሸባሪነት ተፈርጇል።  ኔታንያሁ ትናንት እሁድ ሂዝቦላህ “ከዚህ በፊት ከፍሎት የማያውቀው ዓይነት ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ ዝተዋል።
የጀርመን አየር መንገድ ሉፍታንዛ እና የፈረንሳዩ ኤር ፍራንስ ከቅዳሜው ሮኬት ጥቃት በኋላ ወደ ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት የሚያደርጉትን በረራዎች አቋርጠዋል።  የጀርመን ፌደራል መንግስት ደግሞ በሊባኖስ የሚገኙ ጀርመናውያን በአፋጣኝ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ሲል ዛሬ አሳስቧል። 
ባለፈው ቅዳሜ በጎላን ተራራ አካባቢ እግር ኳስ ሜዳ ላይ ሲጫወቱ በነበሩ አዳጊ ሕጻናት ላይ ሂዝቦላህ ሰንዝሮታል በተባለው ጥቃት ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 16 የሚገመት 12 እስራኤላውያን ተገድለዋል። 
 

ፈረንሳይ፤ በኢንተርኔት አገልግሎት መስመሮች ላይ ጥቃት ተፈፀመ

በፈረንሳይ የኢንተርኔት አገልግሎት መስመሮች ላይ ሆን ተብሎ ጥቃት መሰንዘሩን የሀገሪቱ ፖሊስ ዛሬ አስታወቀ።  ይህ የሆነው የፈረንሳይ የባቡር አገልግሎት ላይ ጥቃት በተፈፀመ ሦስተኛ ቀኑ ነው። ፖሊስ እንዳስታወቀው የበርካታ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ መስመሮች በፈረንሳይ ስድስት አካባቢዎች ከእሁድ እስከ ሰኞ አጥቢያ ድረስ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል።
ከአገልግሎት ሰጪዎቹ አንዱ የሆነው በምህፃሩ SFR እንዳስታወቀው የኢንተርኔት ገመዶቹን በመጥረቢያ ወይም በኤሌክትሪክ መጋዝ» በመቁረጥ  እንዲበላሹ ተደርገዋል። ፍሪ የተባለው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢም የዚህ ጥቃት ሰለባ መሆኑን አስታውቋል። ኦሎምፒክ የሚካሄድባት ፓሪስ ከተማ ግን ከጥቃቱ መትረፏ ተዘግቧል። 
ፖሊስ በሁለቱ ጥቃቶች መካከል ግንኙነት ስለመኖሩ ገና ርግጠኛ አይደለም። የኦሎምፒክ መክፈቻ ቀን  በባቡር መሠረተ ልማቱ ላይ  ሆን ተብሎ እና ታቅዶ ተፈፅሟል ለተባለው ሴራም ይሁን ለዛሬው ጥቃት እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። ዓርብ ዕለት ለተፈፀመው ጥቃት ግን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ግራ ዘመመሞችን እንደሚጠረጥር ዛሬ አስታውቋል። 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።