1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaቅዳሜ፣ ሐምሌ 20 2016

https://p.dw.com/p/4ipIf

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከ230 በላይ ሰዎች ህይወት የቀጠፈውን የጎፋ የመሬት መንሸራተት አደጋ ዛሬ በአካል ተገኝተው ተመለከቱ ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሀገሪቱ የመሬት መንሸራተት አደጋ ታሪክ አሰቃቂ ነው የተባለለትን አደጋ የተመለከተቱት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሀዘን ካወጀ በኋላ ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ጎድዚ ቀበሌ በደረሰው በዚሁ አስከፊ አደጋ የሞቱ የ231 ሰዎች አስክሬን ተገኝቶ መቀበሩን የፌደራል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።

በአደጋው እስካሁን የደረሱበት ያልታወቀ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተከትሎ ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።

እንደመንግስታቱ ድርጅት ዘገባ ከሆነ ደግሞ በአደጋው እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ነው። አደጋውን ተከትሎ ሌሎች 500 ያህል ሰዎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል። ድርቅ እና ጎርፍን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚፈራረቁባት ኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን ዜጎቿ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እርዳታ ጠባቂ ሆነውባታል።

 

የዩጋንዳ ፖሊስ ሙስናን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ከ100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋለ ።

የሀገሪቱ ፖሊስ ትናንት አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ ተቃዋሚዎቹ ህግና ስነስረዓት የመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የዩጋንዳ መንግስት በአጠቃላይ 104 ተቃዋሚዎችን ያሰረ ሲሆን ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ግን ብርቱ ትችት እና ነቀፋ አስከትሎበታል።

አሜሪካን ጨምሮ የመብት ተሟጋቾች ተቃዎሞው ሰላማዊ እንደነበር ጠቅሰው የሀገሪቱ መንግስትን እርምጃ ነቅፈዋል። በዩጋንዳ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ መንግስት ታሳሪዎችን ለመመርመር ኃይል መጠቀሙን ገልጿል።

ወጣት ዩጋንዳዊያን በሀገሪቱ ተንሰራፍቷል ያሉትን ሙስና እና ሊደረግ በታቀደው የግብር ማሻሻያ ላይ ተቃዉሟቸውን ለማሰማት ባለፉት ማክሰኞ እና ሐሙስ ቀናት አደባባይ ወጥተው ነበር። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የዩጋንዳ መንግስት ታሳሪዎቹን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቃቸው አሳስቧል።

 

በናይጄሪያ የተሰየመ ልዩ ፍርድ ቤት ከጽንፈኛው ቦኮ ሃራም ቡድን የሽብር ተግባር ጋር ግንኙነት አላችሁ የተባሉ 125 ሰዎችን በእስራት ቀጣ።

  ፍርድ ቤቱ በርካታ ሰዎችን ለፍርድ ሲያቀርብ ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል። የእስራት ብያኔ የተላለፈባቸው ሰዎቹ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ የዕገታ እና የአጥፍቶ መጥፋት የሽብር ተግባራት ተባባሪ በመሆን ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው።

የናይጄሪያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና የፍትህ ሚንስትሩ ላቴፍ ፋግቤሚ እንዳሉት 85 ሰዎች ለሽብር ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ  ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። የተቀሩት 22 ሰዎች ደግሞ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በሰዎች ላይ ስቅየት መፈጸምን የመሳሰሉ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎችን ፈጽመው የተገኙ ናቸው ።

የተቀሩት በተለያዩ የሽብር ተግባራት ተሳትፈው የተገኙ መሆናቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።  ከጎርጎርሳውያኑ 2009 አንስቶ በናይጄሪያ የሽብር ጥቃት እንደጀመረ የሚነገርለት ቦኮ ሃራም ከ35 ሺ ለሚልቁ ሰዎች ሞት እና በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል በዋነኛነት ይጠቀሳል።

 

 

እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ባደረሰችው  የአየር  ጥቃት ሰላሳ ያህል ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን የፍልስጥኤም የጤና ባለስልጣናት አስታወቁ  ።

እስራኤል በበኩሏ ጥቃቱን የሰነዘርኩት በሃማስ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ነው ብላለች።

በጋዛ ሃማስ የሚያስተዳድረው የጤና ባለስጣናት እንዳሉት የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ያደረሰው በተፈናቃዮች በተጨናነቀው ዴር አል ባላህ ትምህርት ቤት ላይ ነው። በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቆስለዋል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የአየር ጥቃቱ ዒላማ በማዕከላዊ ጋዛ የሃማስ ወታደራዊ ማዘዣ በሚገኝበት ካዲጃ ትምህርት ቤት ላይ ነው። ትምህርት ቤቱ የከባድ ጦር መሳሪያ ማስወንጨፊያ ነበር ያለው ጦሩ ሰላማዊ ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ መልዕክት ተላልፎ ነበር ብሏል።

በጋዛ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ39 ሺ በላይ ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን የፍልስጥኤም የጤና ሚኒስቴር ዐስታውቋል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ በጦርነቱ  14 ሺ የሃማስ  እና እስላማዊ ጂሃድ ቡድኖች ተዋጊዎችን ገድያለሁ ብሏል። በአንጻሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿ መገደላቸውንም እስራኤል አስታውቃለች።

 

ትናንት አርብ ጠዋት ጥቃት የተፈጸመበት የፈረንሳይ የባቡር መሰረተ ልማት ለሁለተኛ ቀን ተጓዦችን አስተጓጉሏል።

የቃጠሎ አደጋ የደረሰበት መስመሩ እስከ መጪው ሰኞ ተጠግኖ ሊደርስ እንዳማይችልም ተጠቁሟል። የኤስ ኤን ሲ ኤኤፍ የባቡር መስመር ኃላፊ ጄን ፒየር እንዳሉት የባቡር አገልግሎቱ ሰኞ እንዲቀጥል ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው።

የሃገሪቱ የትራንስፖርት ሚንስቴር በበኩሉ እንዳለው የባቡር መስመሩ በመስተጓጎሉ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ለመጓዝ ካቀዱት ውስጥ ከ160 ሺ በላይ ተጓዦች የጉዞ መስመር ተስተጓጉሏል።

በአደጋው ምክንያት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ መስመሮች የጉዞ ዕቅዶች ተሰርዘዋል።

በፈረንሳይ እና እንግሊዝ መካከል የሚከንፈው ፈጣኑ የዩሮስታር ባቡር አንድ አራተኛው ጉዞ መሰረዙ ታውቋል። ትናንት አርብ ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ከ250 ሺ በላይ ሰዎች ጉዞ መስተጓጎሉን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ገብሬል አታል እንዳሉት  በባቡር መሰረተ ልማቱ ላይ የተፈጸመው የእሳት አደጋ ሆን ተብሎ እና ታቅዶ የተፈጸመ ሴራ ነው። ነገር ግን ጥቃቱን በማድረስ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም።

33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ የተወካይ ሃገራት ልዑካንን በሴን ወንዝ ላይ ባደረጉት የጀልባ ጉዞ ጨምሮ የሀገሪቱ መለያ በሆነው የአይፍል ማማ ዙርያ ደማቅ የመክፈቻ ስነ ስረዓት ተከናውኗል።

 

ትናንት ምሽት በይፋ የተከፈተው 33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ ዛሬ በመጀመሪያ ቀን በተከናወኑ የኦሎምፒክ ጫወታዎች ስድስት ሃገራት በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገቡ።

ዛሬ በተደረጉ ከሜዳ ውጭ ተግባራት የፍጻሜ ውድድሮች ቻይና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ትመራለች። አውስትራሊያ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እንግሊዝ እና ዩናይትድ ስቴትስ አንድ የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ይከተላሉ። ደቡብ ኮሪያ አንድ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም ካዛኪስታን አንድ የነሃስ ሜዳሊያ በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ ተካተዋል።

የአትሌቲክስ ውድድሮች  የፊታችን ረቡዕ በሚደረጉ የሁለቱም ጾታዎች የፍጻሜ የእርምጃ ውድድሮች ይጀመራሉ ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው እና ተጠባቂዎቹ የመካከለኛ እና የረዥም ርቀት ያማጣሪያ ውድድሮች ደግሞ በቀጣዩ ቀን ሀሙስ በአምስት ሺ ሜትር የማጣሪያ ውድድሮች ይቀጥላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በወንዶች በማራቶን ኢትዮጵያን የወከለው እና ከሁሉም የተሻለ ፈጣን ሰዓት የነበረው ሲሳይ ለማ በገጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ ከውድድር ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል። በእርሱ ምትክ በተጠባባቂነት ተይዞ የነበረው ታምራት ቶላ ሲሳይን ተክቶ የማራቶን ቡድኑን ይቀላቀላል። በወንዶች የማራቶን ውድድር አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ደረሰ ገለታ አስቀድመው በቡድኑ ውስጥ የተካተቱ አትሌቶች ናቸው ።

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።