1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ/ም ዓለም ዜና

Tamirat Geletaዓርብ፣ ሐምሌ 19 2016

https://p.dw.com/p/4inDU

በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን የተነጠቁ ዜጎችን ለማሰብ በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ታወጀ።

በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 260 ገደማ ደርሷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአደጋው ሕይወታቸውን የተነጠቁ ዜጎች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል አስታውቆ ነበር።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአደጋው ሕይታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን ለማሰብ ከሐምሌ 20 ቀን 2016 ጀምሮ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን መታወጁን አስታውቋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ባወጡት መግለጫ ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ “በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ” የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መወሰኑን አስታውቀዋል።

 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የሦስት ሰዎች ህይወት አለፈ ፡፡

አደጋው ትናንት ሀሙስ ሌሊት  በዞኑ ዴቻ ወረዳ ሚዲዮ ጎምበራ በተሰኘች ቀበሌ  ውስጥ መድረሱን  የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በመሬት መንሸራተቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ  አባትና ሁለት ልጆች ወዲያው ህይወታቸው ማለፉን በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው እና በህይወት የተረፉት  የቤተሰቡ እናት ለህክምና ወደ ጤና ተቋም መወሰዳቸውን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል ፡፡

አደጋው  ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል በመስጋት 148 አባወራዎች  አካባቢውን እንዲለቁ መደረጉንም ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ጨምረው ገልጸዋል ፡፡ በመገባደድ ላይ ባለው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት በጎፋ ዞን በደረሰ ተመሳሳይ የመሬት መንሸራተት አደጋ በሀገሪቱ አስከፊ ነው በተባለለት አደጋ 230 ገደማ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።  የካፋ ዞን በሀገሪቱ ውስጥ ጥብቅ እና ጥቅጥቅ ደኖች ከሚገኙባው እና ዝናባማ አካባቢዎች አንዱ እና ተጠቃሽ ነው።

 

የሶማሊያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ላይ የሚያቀርቧቸውን ውንጀላዎች መሰረተ ቢስ ሲል አጣጣለ።

መሥሪያ ቤቱ የሶማሊያን ክሶች እንደማይቀበል አስታውቋል።

 ሚኒስቴሩ ዛሬ በይፋዊ የትስስር ገጹ ባወጣው የጽሁፍ መግለጫ እንዳለው የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት « ኃላፊነት የጎደላቸው » ያላቸውን መግለጫዎች ተቀባይነት የሌላቸው ብሏቸዋል።

ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሃገራት ህዝቦች  ሰላም እና መረጋጋት  ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ዋጋ መክፈሏን የጠቀሰው የሚንስቴሩ መግለጫ ነገር ግን ከሶማሊያ ባለስልጣናት የሚሰሙ ክሶች ኢትዮጵያ በሶማሊያ መልሶ ግንባታ ውስጥ የነበራትን ከፍተኛ ሚና የካደ ነው ብሏል።

ሚኒስቴሩ የትኞቹ የሶማሊያ ባለስልጣናት መቼ እና በምን ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያን ወነጀሉ ስለሚለው ጉዳይ በዝርዝር ያለው ነገር የለም።

ነገር ግን ኢትዮጵያ  ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ስጋት ባጠላበት የአፍሪቃ ቀንድ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በትኩረት እየተከታተለች መሆኗ በመግለጫው ተመላክቷል።

ሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በተደጋጋሚ ድንበሬን ጥሰው እየገቡ ነው ብላ ስትከስ ቆይታለች። በተጨማሪም በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ስር ሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ መጠየቁ ተዘግቧል።

 

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ እና የጸጥታ ኃይላቸው በሀገሪቱ ኬንያን መሰል ብጥብጥ ለማስነሳት የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠነቀቁ ። የፕሬዚዳንቱ እና የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይላት ማስጠንቀቂያ የተሰማው በናይጄሪያ ጣሪያ የነካውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ በቀጣዩ ሳምንት የተቃዉሞ ሰልፍ መጠራቱን ተከትሎ ነው።

 ናይጄሪያ ተግባራዊ ያደረገችው የኤኮኖሚ ማሻሻያ በሀሪቱ የዋጋ ግሽበቱን ከ40 በመቶ በላይ አንሮታል። እንዲያም ሆኖ ግን ናይጄሪያ በኑሮ ውድነት ምክንያት የጎላ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሳታስተናግድ ቆይታለች። አሁን ግን በማህበራዊ የመገናኛ ትስስር ገጾች የፊታችን ሐሙስ ተቃዉሞ ለማድረግ የተላለፉ ጥሪዎች የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት አስቆጥቷል።

 ፕሬዚዳንት ቦላ አህመድ ትናንት ሐሙስ «ተቃውሞን አንፈራም፤ ስጋታችን ለተራው ህዝብ ነው ፤ ስጋታችን ተቃዉሞን ተከትሎ ስለሚፈጠሩ ጥፋቶች ነው» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። «ሀገሪቱ እንደ ሱዳን እንድትሆንም አንፈቅድም» ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የሀገሪቱ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የጦር ባለስልጣናት ወጣቶች በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዳይሳተፉ እያሳሰቡ ነው።

ናይጄሪያ ከፍተኛ የሆነውን የመንግስት ተቃውሞ ሰልፍ ያስተናገደችው በጎርጎርሳዉያኑ 2020 ሲሆን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ SARS የተሰኘው የአድማ ብተና ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሰዎች  10 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካቶች ቆስለዋል።

 

ፓሪስ 33ኛውን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስረዓት ለመጀመር  ጥቂት ሰዓታት በቀሩበት በፈረንሳይ የፈጣን ባቡር መስመር ላይ ጥቃት ተፈጸመ።

በጥቃቱ የደረሰ ሰብአዊ ጉዳት ባይኖርም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የባቡር ተጓዦችን ጉዞ አስተጓጉሏል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ገብሬል አታል እንዳሉት  በባቡር መሰረተ ልማቱ ላይ የተፈጸመው የእሳት አደጋ ሆን ተብሎ እና ታቅዶ የተፈጸመ ሴራ ነው።

ጥቃቱ ለወትሮም ከእረፍት በሚመለሱ ሰዎች ጉዞ የሚጨናነቀውን  የፈርንሳይ አትላንቲክ ፤ ሰሜናዊ እማ ምስራቃዊ የባቡር መስመሮች የጉዞ ሰዓት አዘግይቷል፤ አልያም እንዲሰረዙ አድርጓል ነው የተባለው። ብርቱ ጉዳት የደረሰበት የባቡር መስመሩ እስኪጠገን በርካታ የሰው ኃይል እና ረዘም ያለ ጊዜ መጠየቁ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እስከ 880 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ከጉዞ ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።  ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

የዛሬ ጠዋቱ ጥቃት መዲናዋ ፓሪስ የኦሎምፒክ ተሳታፊ ስፖርተኞች እና የክብር እንግዶችን ጨምሮ እስከ 300 ሺ የሚደርሱ የመክፈቻ ስነስረዓት ታዳሚያንን ደህንነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ጥበቃ እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው።

33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ከአሁን በፊት ከተለመደው የመክፈቻ ስነስረዓት ድባብ በተለየ የተወካይ ሀገራት ልዑካን በሴን ወንዝ ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሃገራቸውን በሚያስተዋውቁበት ስነስረዓት ይጀመራል። በመክፈቻ ስነስረዓቱ የማራቶን ከዋክብቶቹ  አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና አትሌት ትዕግስት አሰፋ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድንን በመምራት ይሳተፋሉ። 

 

የአውሮጳ ህብረት እንዳይንቀሳቀስ ካገደው የሩስያ መዋዕለ ነዋይ የተገኘ 1.5 ቢሊዮን ዩሮ ትርፍ ለዩክሬን ለማስተላለፉ ምላሽ የምትሰጥበትን ሁኔታ በጥንቃቄ እየመረመረች መሆኗን ሩስያ አስታወቀች።

ሩስያ ለህብረቱ እርምጃ ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀች መሆኗን የገለጸችው የህብረቱ ኮሚሽን ንፕሬዚዳንት ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን ከሩስያ ዕግድ ሃብት በወለድ የተገኘውን ገንዘብ ለዩክሬን መስጠታቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው።

ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት  ከሩስያ ዕግድ ሀብት በወለድ መልክ የተገኘው ገንዘብ «ለዩክሬን መከላከያ ማጠናከሪያ እና መልሶ ግንባታ ይውላል። የህብረቱን እርምጃ ተከትሎ የክሬምሊን ቃል አቃባይ ድሜትሪ ፔስኮቭ በሰጡት መግለጫ የህብረቱን እርምጃ «ሕገ ወጥ» ብለውታል።

 አያይዘውም ሩስያ ለድርጊቱ ተመጣጣኝ ነው ያለችውን እርምጃ «በደንብ እና በተጠና መንገድ ትመልሳለች ፤ የአውሮጳ ህብረት የፈጸመው ድርጊት መልስ ሳያገኝ የሚቀር ጉዳይ አይደለም» ብለዋል።

ሩስያ በዕግድ ከተያዘ ሃብቷ የሚገኝ መዋዕለ ነዋይ ለዩክሬን ተላልፎ እንዳይሰጥ በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች ።

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።