1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

የሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሪት ናዳ የ30 ሰዎች ሕይወት አለፈ። በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዚህም ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት አለ። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከሦስት መቶ በላይ ሠራተኞች ካለፈው አርብ አንስቶ የሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጎርጎሮሳዊው 2024ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ትናንት ራሳቸውን ማግለላቸውን ካሳወቁ በኋላ ዴሞክራቶች ባይደን በምርጫው እንዲወዳደሩ ለመረጧቸው ለምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው።

https://p.dw.com/p/4ibp1

ሀዋሳ በጎፋ ዞን በደረሰ ናዳ የ30 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የመሬት ናዳ 30 ሰዎችን ገደለ፡፡ የወረዳው መስተዳድር እንዳስታወቀው አደጋው ዛሬ ረፋድ 4 ሠዓት አካባቢ የደረሰው በወረዳው ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ነው ፡፡ አደጋው የደረሰው ሌሊቱን በጣለው ዝናብ በሦስት መኖሪያ ቤቶች ላይ የተጫነውን ናዳ ለማንሳት ጥረት እየተደረገ ባለበት ተጨማሪ ደራሽ ናዳ በመምጣቱ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

«አጋጣሚ ሦስት ቤተሰብ ላይ አደጋው ከደረሰ በኋላ ድጋፍ ለማድረግ የወጡ ቤተሰቦች የተጎዱበት ሁኔታ ስላለ ከ30 በላይ ነው አስከሬን እየወጣ ያለው»

እስከአሁን በተደረገ ፍለጋ የ30 ሰዎች አስከሬን መገኘቱንና የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለም አቶ ምስክር ጠቁመዋል ፡፡ ከሟቾቹ መካከል በህይወት አድን ሥራ ተሰማርተው የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎችና የወረዳው ፖሊስ አባላት እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የአስክሬን ፍለጋና የሕይወት አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም መናገራቸውን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሀዋሳ ዘግቧል።

ሀዋሳ   የሾኔ ሆስፒታል ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ ፡፡ቁጥራቸው ከሦስት መቶ በላይ የሚሆነው የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች ካለፈው ዓርብ አንስቶ የሥራ ማቆም አድማ ላይ መሆናቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት የሆስፒታሉ ሠራተኞች በወረዳው በተደጋጋሚ የደሞዝ ክፍያ ባለመፈጸሙ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን ገልጸዋል። የስራ ማቆም አድማ የመቱትም የሁለት ወር ደሞዛቸው እንዲከፈለቸው በመጠየቅ መሆኑንም አስረድተዋል። 

“ ያልተፈጸመው ክፍያ የግንቦት እና የሰኔ ወር ነው ፡፡ ነገር ግን የግንቦትን ዘለው የሰኔ ወር እንደሚከፈል ነግረውናል ፡፡ በዚህም አብዛኛው ሠራተኛ በግማሽ ክፍያው አልተስማማም ፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደር ጥያቄያችንን ሊመልስ ባለመቻሉ ሥራ አቁመን እንገኛለን “

ሠራተኞቹ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ሥራ ማቆማቸውን የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል  ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ አህመድ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡ ሠራተኞቹ ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ሥራ እንደማይገቡ ተፈራርመው ማስገባታቸውንም ተናግረዋል።

ዶቼ ቬለ የሃድያ ዞንና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤናና የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ቢሞክርም ሃላፊዎቹ የሥልክ ጥሪ ባለመመለሳቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለም ፡፡ የሾኔ ሆስፒታል ሜዲካል  ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ግን  የሆስፒታሉ አስተዳደር በአድማው ምክንያት ተገልጋዩ ማህበረሰብ እንዳይጉላላ ለማድረግ  ሠራተኞች እየሠሩ መብታቸውን እንዲጠይቁ በማድረግ ለማግባባት እየተሞከረ ነው ብለዋል ፡፡

ድምጽ ዶክተር መሐመድ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን መምህራንና ሀኪሞች  በተደጋጋሚ ቅሬታዎችንና ሲያሰሙና የሥራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ መቆየታቸው እንደሚታወስ ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዘግቧል።

 

ዋሽንግተን     ዴሞክራቶች ለሀራሴ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው

 

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጎርጎሮሳዊው 2024ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ትናንት ራሳቸውን ማግለላቸውን ካሳወቁ በኋላ ዴሞክራቶች ባይደን በምርጫው እንዲወዳደሩ ለመረጧቸው ለምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው። የ59 ዓመቷ ሀሪስ በባይደንና በሌሎች አንጋፋ ዴሞክራቶች በምርጫው እንዲወዳደሩ መመረጣቸው በጎርጎሮሳዊው ህዳር 5 ቀን 2024 ዓም ለሚካሄደው ምርጫ በባይደን ምትክ የዴሞክራቶች እጩ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ በሰፊት ተገምቷል። እስካሁን ድረስ ከዴሞክራቶች ፓርቲ ሀሪስን እፎካከራለሁ ያለ አንድም ታዋቂ ፖለቲከኛ የለም። ይሁንና ማን የዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ እንደሚሆን የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው  ከጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 22 ቺካጎ በሚካሄደው የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ነው። ያም ሆኖ ከጉባኤው በፊትም ፓርቲው በእጩ ተወዳዳሪ ስየማ ላይ ሊስማማም ይችላል።  ትናንት ለካማላ ሀሪስ ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ቃል የገቡት የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን እስከ ጎርጎሮሳዊው ጥር 2025 ዓም ድረስ የሚዘልቀውን የስልጣን ዘመናቸው እንደሚጨርሱ ተናግረዋል። 

 

መቅዲሾ     በአሸባብ ስለተፈጸሙ ጥቃቶች የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች ርስ በርስ ይጣረሳሉ

 

በቅርቡ በሶማሊያ ጦር ሰፈሮች ላይ አሸባሪ በሚባለው በአሸባብ ስለተፈጸሙ ጥቃቶች ርስ በርስ የሚጋጩ ዘገባዎች እየወጡ ነው። የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA እንደዘገበው አልሸባብ በደቡባዊ ሶማሊያ ይዞታዎቹን ለማስፋት የሚያደርገውን ሙከራ የሶማሊያ ጦር እየመከትኩ ነው ይላል። በጦሩ አገላለጽ አሸባብ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል። በነዚህ ሙከራዎች ቢያንስ 80 የአሸባብ ተዋጊዎች ተገድለዋል፤ ከሶማሊያ ጦር በኩል ደግሞ 5 ወታደሮች ብቻ ናቸው የሞቱት ሲል ተናግሯል። የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ የሟቾቹን ቁጥር ወደ 100 ያስጠጋዋል። አልሸባብ በበኩሉ በራድዮ ማሰራጫው 71 የመንግሥት ወታደሮች ገድያለሁ ብሏል። ሁለቱም በየፊናቸው ብዙ መግደላቸውን ቢናገሩም የሚሰጧቸውን መረጃዎች ግን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልተቻለም። የሶማሊያን መንግሥት የሚወጋው አሸባብ በአሁኑ ጊዜ የማዕከላዊ እና ሰሜን ሶማልያን የተወሰነ ክፍሎች እንደተቆጣጠረ ነው። ቡድኑ በተደጋጋሚ በዋና ከተማይቱ በመቅዲሾ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችንም ይፈጽማል።በቅርቡ ቡድኑ መቅዲሾ የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ በሚገኝ ታዋቂ ምግብ ቤት ውስጥ በጣለው ጥቃት አውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታን በመመልከት ላይ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ሞተዋል፤ የአካል ጉዳተኛም ሆነዋል።

 

አማን         በሱዳኑ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው ሲል ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አሳሰበ

 

ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የሱዳን ግጭት ሰላማዊ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እየተሰቃዩ ነው ሲል ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በምህጻሩ MSF አስታወቀ። ቡድኑ እንዳለው በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ውጊያ ፣ ሰላማዊ ሰዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፤ ይበደላሉ በሁለቱም ወገኖች ይበዘበዛሉ።  የሀገሪቱ የጤና ስርዓት መንኮታኮትና የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ ድጋፍ አለመኖርም፣ ውጊያው ያመጣቸውን አካላዊ እና አዕምሮአዊ ጠባሳዎች አባብሷል። በመኖሪያ ቤቶችና በጠቃሚ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም የቦምብና የከባድ መሣሪያዎች ድብደባ በደረሰባቸው አካባቢዎች  በሺህዎች የሚቆጠሩ የቆሰሉ ሰዎችን ቡድኑ ማከሙንም ገልጿል። በመላ  ሱዳን በተስፋፋው በሕክምና ግብዓቶች ዝርፍያ፣ የደኅንነት እጦት እና በሕሙማንና በጤና ባለሞያዎች ላይ በሚደርስ ጥቃትና የጤና አጠባበቁ መሰረተ ልማት በደረሰበት ብርቱ ጉዳት ምክንያት ሕይወት ለማትረፍ የሚደረግ ሕክምና በእጅጉ ተጽእኖ ውስጥ ነው የሚገኘው። MSF ውጊያ የሚያካሂዱትን የሱዳን ጦርን እና የፈጥኖ ደራሹን ኃይል የሰው ልጆች ሕይወትና ዓለም አቀፍ ሕግ ባለማክበር ከሷል።

ዋሽንግተን     ዴሞክራቶች ለሀራሴ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው

 

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጎርጎሮሳዊው 2024ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ትናንት ራሳቸውን ማግለላቸውን ካሳወቁ በኋላ ዴሞክራቶች ባይደን በምርጫው እንዲወዳደሩ ለመረጧቸው ለምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው። የ59 ዓመቷ ሀሪስ በባይደንና በሌሎች አንጋፋ ዴሞክራቶች በምርጫው እንዲወዳደሩ መመረጣቸው በጎርጎሮሳዊው ህዳር 5 ቀን 2024 ዓም ለሚካሄደው ምርጫ በባይደን ምትክ የዴሞክራቶች እጩ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ በሰፊት ተገምቷል። እስካሁን ድረስ ከዴሞክራቶች ፓርቲ ሀሪስን እፎካከራለሁ ያለ አንድም ታዋቂ ፖለቲከኛ የለም። ይሁንና ማን የዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ እንደሚሆን የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው  ከጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 22 ቺካጎ በሚካሄደው የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ነው። ያም ሆኖ ከጉባኤው በፊትም ፓርቲው በእጩ ተወዳዳሪ ስየማ ላይ ሊስማማም ይችላል።  ትናንት ለካማላ ሀሪስ ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ቃል የገቡት የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን እስከ ጎርጎሮሳዊው ጥር 2025 ዓም ድረስ የሚዘልቀውን የስልጣን ዘመናቸው እንደሚጨርሱ ተናግረዋል። 

ሆዴይዳ   በሆዴይዳ ፣የእስራኤል የአየር ድብደባ ያስነሳው ከፍተኛ እሳት ዛሬም አልበረደም

 

ባለፈው ቅዳሜ እስራኤል ሁቲዎች በሚቆጣጠሯት በየመንዋ ሆዴይዳ ወደብ ያካሄደችው የአየር ድብደባ ያስከተለው ከፍተኛ እሳት ዛሬም አልጠፋም። ድብደባው በወደቡ ላይ ያስከተለው ከፍተኛ የእሳት ነበልባል እና ጥቁር ጢስ ዛሬም ወደ ሰማይ ሲንቦለቦል ይታያል። ሁቲዎች በሚቆጣጠሯት በሆዴይዳ ወደብ የነዳጅ ዘይት ማከማቻዎችና በአንድ የኃይል ምንጭ ላይ ባካሄደችው ድብደባ ዛሬም የሚነደውን እሳት ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ተከላካዮች እየተረባረቡ ነው። ጥረቱ የቀጠለ ቢሆንም እሳቱ ከመጥፋት ይልቅ መስፋፋቱ ቀጥሏል። በቅዳሜው የአየር ጥቃት 6 ሰዎች ተገድለዋል። የነዳጅ ማከማቻውን የሚያስተዳድረው የየመን የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ትናንት ማምሻውን እንዳስታወቀው በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱት ሰዎች በሙሉ ሠራተኞቹ ናቸው። ሁቲዎች እንደሚሉት ሌሎች 80 ሰዎችም በጥቃቱ ቆስለዋል። የቅዳሜው የአየር ጥቃት እሥራኤል በድሀይቱ የአረብ ባሕረ ገብ መሬት ላይ የፈጸመችው የመጀመሪያው የአየር ጥቃት ነው ተብሏል። ሁቲዎች በማግስቱ በጣሉት የአጸፋ ጥቃት የእስራኤልን የአየር መከላከያ ጥሰው ቴላቪቭ ውስጥ አንድ ሰው ገድለዋል። 

 

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።