1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐሙስ ነሀሴ 16 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tsehay Filatieሐሙስ፣ ነሐሴ 16 2016

DW Amharic- ህወሃት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርን በአዳዲስ ተሿሚዎች ለመቀየር ውይይት እንደሚጀምር ማስታወቁ- ሶማሊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገሪቱ የሚያደርገውን በረራ እንደምታግድ መግለጿ- በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች የመሬት መንሸራተት በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ- የኬንያ ፖሊስ ከ40 በላይ ሴቶችን በመግደል ከዕስር ያመለጠ አንድ ተጠርጣሪን ለጠቆመ የገንዘብ ወሮታ እንደሚከፍል ማስታወቁ-ታሊባን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢን ወደ አፍጋኒስታን እንዳይገቡ ማገዱ

https://p.dw.com/p/4jnt8


ህወሃት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርን በአዳዲስ ተሿሚዎች ለመቀየር   ውይይት እንደሚጀምር ማስታወቁ


በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን የትግራይን ግዚያዊ አስተዳደር በአዳዲስ ተሿሚዎች ለመቀየር  ህወሃት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚጀምር የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለፁ።በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ  ከአስተዳደሩ እውቅና ውጭ ማንኛውም ስብሰባ እንዳይደረግ የስራ መመርያ አሰራጭቷል።
ከፍተኛ አመራሮቹ እንዲሁም አባላት በከፊል ያልተሳተፉበት የሰባት ቀኑ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ፤ የፓርቲው  ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል  ትናንት ነሐሴ 15 ቀን  2016 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከዚህ ቀደም ህወሓትን ወክለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የገቡ አመራሮች፣ በአሁኑ ጉባኤ ባለመሳተፋቸው እና ባለመመረጣቸው ህወሓትን እንደማይወክሉ ገልፀዋል።በመሆኑም  አስቀድሞ ህወሓትን ወክሎ ወደ ትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የገባው አመራር በአሁኑ ወቅት ከህወሓት ጋር በመለያየቱ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ግዚያዊ አስተዳደሩን ካቋቋሙ አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል። ክፍፍል ላይ ሆኖ ጉባኤ ያደረገው እና አዲስ አመራር መምረጡን ያስታወቀው ህወሓት፤ ፓርቲው  በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስላለው ውክልናም ከፌደራል መንግስቱ ጋር እንደሚነጋገር  ሊቀመንበሩ ገልፀዋል።
 በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ  ከአስተዳደሩ እውቅና ውጭ ማንኛውም ስብሰባ እንዳይደረግ የስራ መመርያ አሰራጭቷል።
የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮቹ በከፋፈለው  የህወሓት ጉባኤ፤ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት  በዚህ ጉባኤ ሳይገኙ መቅረታቸው ይታወሳል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገሪቱ የሚያደርገውን በረራ እንደምታግድ መግለጿ

የሶማሊያ አቪዬሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገሪቱ የሚያደርገውን በረራ ሊያግድ  እንደሚችል ገለፀ። በቅርቡ በሶማሌ ላንድ እና በኢትዮጵያ የተደረገው የወደብ ስምምነት  የፈጠረው አለመግባባት ውጤት ነው ተብሏል።
የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ትናንት እንዳስታወቀው፣የሶማሊያ አቪዬሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገሪቱ የሚያደርገውን በረራ ሊያግድ  እንደሚችል ገልጿል።
እንደ ዘገባው እርምጃው በቅርቡ በተፈፈፀመው የሶማሌ ላንድ እና የኢትዮጵያ ስምምነት  ሳቢያ የተፈጠረው አለመግባባት የመጨረሻው ድርጊት ነው።
የሶማሌ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም በ«ሉዓላዊነት ጉዳዮች» ላይ የተነሱ ቅሬታዎችን አልፈታም ማለቱንም ዘገባው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሶማሌላንድ ትልቁ ከተማ ሃርጌሳ፣ እንዲሁም ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ እና ወደ አራት የሶማሊያ  ከተሞች በረራ ያደርጋል።
ሶማሌላንድ በጎርጎሪያኑ ያለፈው ጥር ወር ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር  እንድታቋቁም ስምምነት ከደረሰች በኋላ፤ ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል። ስምምነቱ ሶማሊያ የግዛቷ ዋና አካል አድርጋ በምትወስደው አካባቢ ኢትዮጵያ  የባህር በር  እንድታገኝ የሚያስችል ነው።

በአማራ ክልል  ሁለት ዞኖች የመሬት መንሸራተት በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ


በአማራ ክልል  ሁለት ዞኖች የመሬት መንሸራተት በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የየዞኖቹ ባለስልጣናት ገለፁ።
በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባው መለስ ለዶቼ ቬሌ እንደተናገሩት በዞኑ 8 ወረዳዎች  የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ 
በዚህም ከ264 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል ወድሟል፣ 166 ቤቶች ፈርሰዋል፣  5 ሄክተር የግጦሽ መሬት፣ የውሀ ተቋማትና መንገዶች ለብልሽት መዳረጋቸውን ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በክልሉ በሚታየው  የፀጥታ ችግር ምክንያት አደጋው ስለደረሰባቸውን ሰዎች የተጠቃለለ መረጃ አለመገኘቱን የገለፁት ሃላፊው፤በኤፍራታና ጣምራ በር ወረዳዎች  218 የቤተሰብ አባወራዎች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
 በዚሁ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርም ባለፉት 3 ቀናት የጣለው ከባድ ዝንብ  ባስከተለው ናዳ፤ ዳህና ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው ዋና ጎዳና  አገልግሎት ማቋረጡንና በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የአስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ አመልክተዋል፡፡
በሰዎች ላይ እስካሁን የሞት ጉዳት አለመድረሱን ያመለከቱት አቶ ምህረት፤ 80 እንስሳት በናዳው ሞተዋል ። 14 ቤቶች ደግሞ መፈራረሳቸውን ገልጠዋል። በ2700 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ወድሟል፡፡93 ሰዎች ደግሞ ከአካባቢው እንዲለቁ ተደርጓል። 

 የኬንያ ፖሊስ ከዕስር ያመለጠ አንድ ተጠርጣሪን ለጠቆመ የገንዘብ ወሮታ እንደሚከፍል ማስታወቁ

የኬንያ ፖሊስ ከዕስር ያመለጠ  አንድ ተጠርጣሪን ለጠቆመ የገንዘብ ወሮታ እንደሚከፍል አስታወቀ።ተጠርጣሪው ከ40 በላይ ሴቶችን በመግደል  ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኝ ነበር።
እንደ  አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ በርካታ ሴቶችን  በመግደል እና አካል ቆራርጦ በመጣል የተከሰሰው ኮሊንስ ጁማሲሲ ከ12 ኤርትራዊያን ጋር በመሆን ከዕስር አምልጧል።
እንደ ዘገባው በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኘው ሙኩሩ ሰፈር  በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ በርካታ የሴት አስከሬኖች መገኘቱን ተከትሎ ነበር የ33 አመቱ ጁማአይሲ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው።
የሞቹቹ አስከሬን ከተገኘበት 100 ሜትር ርቀት  የሚገኝ  አንድ ፖሊስ ጣቢያን ሰብሮ  ካመለጠ ካለፈው ከማክሰኞ ወዲህ  ፖሊስ ተጠርጣሪውን ማደን ጀምሯል።
ይህንን ተከትሎ የኬንያ ፖሊስ ዛሬ እንዳስታወቀው  ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል  መረጃ ለሚሰጥ ሰው  የገንዘብ ሽልማት ማዘጋጄቱን ገልጿል።
ተጠርጣሪው ከጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ባለቤቱን ጨምሮ  42 ሴቶችን መግደሉን የኬንያ ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ከእስር ቤት እንዲያመልጥ በማድረግ የተጠረጠሩ  አምስት የፖሊስ መኮንኖች ረቡዕ እለት ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን ፤ በ200,000 የኬንያ ሺሊንግ (1,500 ዶላር) ዋስትና መለቀቃቸው ታውቋል።አቃቤ ህጎች ግን ለ14 ቀናት በእስር እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጥተው ነበር ተብሏል።
በናይሮቢ በከፍተኛ ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ከታሰረበት ሲያመልጥ በስድስት ወራት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም  ዘገባው ያመለክታል።

ታሊባን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢን ወደ አፍጋኒስታን እንዳይገቡ ማገዱ

ታሊባን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢን ወደ አፍጋኒስታን እንዳይገቡ አገደ። በአፍጋኒስታን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢ ሪቻርድ ቤኔት  በታሊባን መታገዳቸው ስራቸውን እንደማያደናቅፍ ተናግረዋል።ታሊባን፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢ ሪቻርድ ቤኔትንሪቻርድ ቤኔት  «በአፍጋኒስታን የተሾመው ፕሮፓጋንዳ እንዲያሰራጭ ስለሆነ እና ቃሉን የምናምነው ሰው ስላልሆነ ታግዷል» ሲል ገልጿል።
በአፍጋኒስታን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢ ሪቻርድ ቤኔት  በታሊባን መታገዳቸው ስራቸውን እንደማያደናቅፍ ተናግረዋል።
የታሊባንን  ውሳኔ አጥብቀው ያወገዙት ቤኔት፤“ከታሊባን ባለሥልጣናት ጋር በግልፅ ለመነጋገር  ቢፈልጉም አለመሳካቱን ገልፀዋል።ባለስልጣናቱ ውሣኔያቸውን ደግመው እንዲያጤኑት ጠይቀዋል።
ያም ሆኖ መታገዳቸው በሀገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከመዘገብ  እንደማይከለክላቸው ገልፀዋል።
ወግ አጥባቂው እስላማዊ ቡድን ታሊባን፤ ከዛሬ ሶስት አመት በፊት በጎርጎሪያኑ ነሀሴ 2021 ዓ/ም አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ ወዲህ፤ ሴቶችን ከእይታ በማገድ እና ከህብረተሰቡ እንዲገለሉ በማድረጉ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ በርካታ ትችት እየደረበት ነው።በታሊባን አስተዳደር ሴቶች በአፍጋኒስታን በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ላይ እንዳይሰማሩ እገዳ ተጥሎባቸዋል።ይህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ታሊባንን እንደ ህጋዊ ገዥ እውቅና እንዳይሰጥ አድርጎታል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።