1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልዩ ኃይል ጉዳይ ያጫረው ቁጣና የጋዜጠኞች መታሰር

ዓርብ፣ ሚያዝያ 6 2015

የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና «ለማደራጀት» የሚለው ውሳኔ በአማራ ክልል ለተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ተቃውሞና ሕዝባዊ ቁጣ አስተጋብቷል ። ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ለጥቃት ተጋላጭ በሆነበት ወቅት ልዩ ኃይሉን ትቅጥ አስፈትቶ ለመበተን እየሞከረ ነው ሱሉ በርካቶች በብርቱ ተቃውመዋል ። የጋዜጠኞች እስርም ቀጥሏል ። አስተያየቶችን አሰባስበናል ።

https://p.dw.com/p/4Q1Ip
Äthiopien Wiederaufnahme der Transportdienste in Bahirdar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና «ለማደራጀት» በሚል የተወሰነው ውሳኔ በአማራ ክልል ለተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ተቃውሞ እና ሕዝባዊ ቁጣ አስተጋብቷል ። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ለጥቃት ተጋላጭ በሆነበት ወቅት ልዩ ኃይሉን ትቅጥ አስፈትቶ ለመበተን እየሞከረ ነው ሲሉ በብርቱ ተቃውመዋል ። የክልሉ ሕዝብ ከሕወሓት እና ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች በማንኛውም ጊዜ ሊቃጣ በሚችል ጥቃት በተጋለጠበት ወቅት የተላለፈው የጥድፊያ ውሳኔ አንዳች ተንኮል ያዘለ ነው ሲሉም ተደምጠዋል ። ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ ጉዳዩ ጥናት የተኪያሄደበት እና አስቀድሞም በክልሎች ኃላፊዎች ዘንድ ለውይይት መቅረቡን ገልጧል ። በአማራ ክልል ብርቱ ተቃውሞ ወቅት እና ከዚያም ቀደም ብሎ በርካታ የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውን በመቃወምም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል።  

የልዩ ኃይል ጉዳይና ተቃውሞ

የክልል ልዩ ኃይሎችን «ማደራጀት» በሚል ለአብዛኛው ኅብረተሰብ ዱብዳ በሆነ መልኩ በአማራ ክልል ሰሞኑን ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ ሙከራ ብርቱ ተቃውሞ ከዳር እስከ ዳር እንዲያስተጋባ አድርጓል ። በተለይ ቁጣው ረቡዕ ዕለት ጋብ ከማለቱ ቀደም ብሎ በነበሩ ቀናት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል፤ በርካቶች ቆስለዋል ። ሙሐመድ ሁሴን ፌስቡክ ላይ ያሰፈሩት መልእክት በርካቶች ያስተጋቡት ነው ። «እኛ አማራዎች ስጋት አለብን ። በወዲህ ኦነግ ይጨፈጭፈናል፤ በሰሜን ሕወሓት ስለዚህ እንዴት ትጥቅ ፍቱ እንባላለን? » በሚል ይነበባል መልእክታቸው ።

«ያለችን አገር አንድ ናት ። ሊኖረን የሚገባን መከላከያ የአገር መከላከያ ብቻ ነው» ሲሉ ጽሑፋቸውን ትዊተር ላይ ያሰፈሩት ደግሞ ለገሠ ሾማ ናቸው ። «የክልሎች ልዩ ኃይል ወደ መከላከያ መቀላቀል 100% እንደግፋለን ። ይህን የሚቃወሙት የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎች ናቸው » ብለዋል ።

ይሁኖ ዓምላክ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ አንድ ሁለት እያሉ መልእክታቸውን አስፍረዋል ። «1. ወያኔ መከላከያን (ሰሜን እዝን) ጨፈጨፈ 2. የአማራ ልዩ ኃይል መከላከያን ረድቶ አሸነፉ 3 መከላከያና ወያኔ ታረቁ 4. የአማራ ልዩ ኃይል ትጥቅ ፍታ ተብሎ በመከላከያ ተወጋ … ፊልም የሚመስል የዘመኑ የክህደት ታሪክ ። መዝግበናል» በሚል ይነበባል ።

ተቃውሞ በአማራ ክልል፤ ፎቶ ከክምችት ማኅደር
ተቃውሞ በአማራ ክልል፤ ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል Alemenew Mekonnen/DW

«ሰላም ይሻላል መረረን እኮ ሁልጊዜ መገዳደል» ያሉት ደግሞ ፋሲል አዓባይ ናቸው ፌስቡክ ላይ በአጭሩ ። ተቃውሞው በአማራ ክልል በበረታበት ወቅት፦ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ውሳኔው ቀደም ብሎ ውይይት የተደረገበት ስለመሆኑ በአጭር ጊዜ ግን ደግሞ በተከታታይ ማስተባበያዎችን አሰምተዋል ። ማስተባበያዎች ካሰሙ ሰዎች መካከል ናትናኤል መኮንን የተባሉ በርካታ ተከታይ ያላቸው የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የሶማሊ ክልል ካቢኔ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ ለማድረግ የተወሰነው ውሳኔ ዕቅድ በሙሉ ድምጽ ደግፎታል» ሲሉ ሰኞ ዕለት ዘለግ ያለ ጽሑፍ በትዊተር አስፍረዋል ።

«በሁሉም ክልሎች እኩል ይተገበራል አልተባለም?» ይጠይቃሉ ሞላ ታደሰ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ። «ስለዚህ አማራ ክልል ምክር ቤት ሳይወያይ ለምንድ ነው የተቻኮለው?» አሁንም ይጠይቃሉ ። «ዛሬ» ሲሉ በተደጋጋሚ የጥያቄ መልእክት ጥያቄያቸውን ያንደረደሩት ደግሞ ዓለሙ በቃ ናቸው እዛው ትዊተር ላይ ። «አማራ እምቢ ሲል አዲስ ሥራ ጀመራችሁ። እምቢታችን ትክክል እንደነበረ እየመሰከራችሁ ነው። ለአማራ ብቻ ነበር ሴራው የተዘጋጀው» ብለዋል ።

ሮዚና ንጉሤ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ የሶማሊ ክልል ፕሬዚደንት ሙስጠፋ ዑመርን ይፋዊ የትዊተር መልእክት በማያያዝ «ጸደቀ» በሚል የተላለፈው መልእክት የማምታታት እንደሆነ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ገልጠዋል ። «የትዊተር መልእክቱ የትኛው ክፍል ያን እንደሚል ግራ ገብቶኛል ። ሰዎችን ማምታታህን አቁም ። ሙስጠፋ ዑመር ያቀረቡት መልእክት ይህ ነው» በሚል መልእክቱን አያይዘዋል ። በእንግሊዝኛ የቀረበው የክልሉ ፕሬዚደንት መልእክት የሚከተለው ነው ።

«12ኛው የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ ስብሰባ በሚቀጥለው ዓመት (2016) የበጀት ቅድሚያዎች ላይ ተወያይቶ ስምምነት ላይ ደርሷል። ካቢኔው የብሔራዊ እና ክልላዊ የፀጥታ መዋቅሮች መጣጣምን በተመለከተም ማብራሪያ ተደርጎለታል ። «የተሳሳተ መልእክት አታስተላልፉ። እሱ ያለው ወይይት እንደተደረገበት ነው። የደገፉት ሀሳብ ግን በፖሊስ ሪፎርሙ ላይ ነው » ያሉት ጥሩ ሰዓል የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው ።

ሶማሌ ክልል ፊቅ ከተማ ውስጥ የልዩ ኃይል «ይደራጅ» ከተባለው ውሳኔ ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ገልጠዋል ።  ሳሚ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «በሶማሌ ክልል ኤረር ዞን ፊቅ ከተማ የልዩ ኃይል መፍረስን በመቃወም ሕዝቡ አደባባይ ወጥቷል » ሲሉ ጽፈዋል ። ፎቶግራፎችንም አያይዘዋል ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የልዩ ኃይል አደረጃጀት ስምሪት አቁሟል ሲሉ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ናቸው ።  ጥቁር ሰው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ኧረ መሸዋወድ» ብለዋል ። «መታለልስ አንዴ» ሲሉ በአጭሩ የጻፉት ደግሞ ዳንኤል ታደሰ ናቸው ፌስቡክ ላይ ። «በጣም አሪፍ ነው ቀጥሉበት» ይሄ ደግሞ የጌት ከበደ መልእክት ነው ። «እሱማ አይፈርሥም ተባለ እኮ ማንን ለማታለል ነው አሁን ክልሉ እንደ አዲስ የሚዘላብደው» መልእክቱ የማትበገር ኢትዮጵያ በሚል የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ነው ። «ማሰብ ማለት ይህ ነዉ»  የሲቆ ባሌ አደም አጭር መልእክት ነው ። ወደቀጣዩ ርእስ እንሻገር

የጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ተቺዎች እስር

የኢትዮጵያ መንግስት የግል ጋዜጠኞችን፣ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ አሰራጮችን፣ተቺዎችንና የፖለቲካ አቀንቃኞችን ማሰሩን እንደቀጠለ ነዉ ። የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጩ ሐሙስ ዕለት እንደዘገበዉ ኢትዮ ሰላም የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ አውታር  መስራች እና የፖለቲካ ተቺ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው እንዲሁም  «አራት ኪሎ ሚዲያ» የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ አውታር አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጧል ። የጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ቤተሰቦች እንዳሉት በፀጥታ ኃይላት «ትፈለጋሕ» ተብሎ ከቤቱ ከመወሰዱ ዉጪ የተያዘበትን ትክክለኛ ምክንያት አያዉቁም ።  «አሁንስ አበዙት ይሄንን ልጅ በቅርብ አስረውት ነበር ፈቱት አሁን ደግሞ አሰሩት» የፌስቡክ አስተያየቱ በዳዊት መስፍን ነው የተሰጠው ። በሽር ቦኑ፦ «ምን አጠፋ?» ሲሉ ጠይቀዋል ። ኡሹ ተሻ የተባሉ የፌስቡ ተጠቃሚ፦ በአጭሩ፦ «የሚችሉት ብቸኛ ነገር ይሄ እኮ ነው» ብለዋል ።

የኢትጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን፤ «አል ዐይን ኒውስ» ን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ሲሠራ የነበረዉ  እንዲሁም «አራት ኪሎ ሚዲያ» የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻዉም ባሕርዳር ዉስጥ ታስሯል። የዳዊት ባልደረቦችና ጓደኞች እንዳስታወቁት ጋዜጠኛዉ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕርዳር የሔደዉ የሚሰራበት ቁሳቁስ በመዘረፉ ለእረፍትና ርዳታ ለማሰባሰብ ነበር ።  የዳዊትን እስር በተመለከተ አራት ኪሎ ሚዲያ፦ «ማንነት ተኮሩ የሚዲያ አፈና ቀጥሏል» ሲል ሐሙስ ዕለት ጽፏል ። በቅርቡ ዘረፈ የተፈጸመበት «የኢትዮ 251 ሚዲያ» ላይም ወከባ ስለመቀጠሉ ሐሙስ ዕለት ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር በፌስቡክ ጽፏል ።  «የኢትዮ 251 ሚዲያ ስቱዲዮ በፀጥታ ኃይሎች ተከቧል » ሲል ይነበባል ጽሁፉ ። «መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም ኢትዮ 251 ሚዲያ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሚዲያው ዘረፋ እንደተፈፀመበት ይታወቃል» የሚልም መልእክት ሰፍሯል ።የሙሉጌታ ጽሑፍ፦ «ከበባ የተፈፀመበት የኢትዮ 251 ሚዲያ ስቱዲዮ አራት ኪሎ ሚዲያ እና ነገር ወልቃይት ሚዲያ በጋራ የሚጠቀሙበት መሆኑ ይታወቃል» በሚልም ይነበባል ።

የጋዜጠኝነት አፈናን ለማሳየት መቅረጸ ድምፅና እጅ በሰንሰለት ተጠፍረው
የጋዜጠኝነት አፈናን ለማሳየት መቅረጸ ድምፅና እጅ በሰንሰለት ተጠፍረውምስል Sorapop/Panthermedia/imago images

ኢንተርኔትን መሠረት አድርገው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚሠሩ እና የመረጃ ትንተና የሚሰጡ ሦስት ሴቶችን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ሰሞኑን እየታሠሩ ይገኛሉ ። መምህርት እና «ኢትዮ ንቃት» የተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ መሥራች መስከረም አበራ እሁድ ምሽት የፌዴራል ፖሊስ መለዮ በለበሱ ሰዎች ለሦስተኛ ጊዜ መታሰሯን ባለቤቷ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።«በዘራፊ የምትመራ ፤ የፀጥታም ኃይል ያላት የማፊያ አገር አድርገዋት አረፉት» ሲሉ የጻፉት ዳዊት ተስፋዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ።

ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ለእስር ስትዳረግ ለቅርብ ሰው ደውላ የተላለፈ የተባለው የስልክ መልእክት በማኅበራዊ መገናኛ አውታር በስፋት ተሰራጭቷል ። ጋዜጠኛዋን ክብረ ነክ ስድቦች ሲሳደቡ እና ሲመቷትም በተቀረጸው የስልክ መልእክት ይደመጠላል ። ክብሩ ይስፋ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የአብይ አህመድ አውሬ የደህንነት ሰዎች ጋዜጠኛ ገነት አስማማውን እንደዚህ አጸያፊ ስድብ እና ድብደባ በመፈጸም ነው አፍነው የወሰዷት!» በማለት የድምፅ መልእክቱን አያይዘዋል ።

«የአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ፣ የየኔታቲዩብ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፣ የወልቃይት ተወላጆች ማኅበር ሰብሳቢና የተባበሩት አማራ በጎ አድራጎት ድርጅት ም/ቦርድ ሰብሳቢ እና የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር አሰፋ አዳነና ላቀው በቀለ ታሰሩ» ሲሉ የጻፉት ደግሞ እሙ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው ።

የኢትዮጵያ መንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች ባለፉት ሁለት ሳምንት ዉስጥ 6 ጋዜጠኞች፣ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ሠራተኞችና የፖለቲካ ተቺዎችን ማሰራቸዉ ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ