የሁለቱ ሱዳኖች ስምምነት
ሐሙስ፣ መስከረም 17 2005ማስታወቂያ
4 ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ የተደራደሩት ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ወሰናቸውን ለማስጠበቅና የነዳጅ ዘይት ምርትና ንግድን ለመቀጠል የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈራረሙ ። የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽርና የደቡብ ሱዳኑ አቻቸው ሳልቫ ኪየር የትብብር ስምምነት ፣ እንዲሁም የሁለቱ ሃገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ደግሞ በወሰናቸው ላይ ከጦር እንቅስቃሴ ነፃ የሆነ ቀጣና ለመከለል የሚያስችል ስምምነት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተፈራርመዋል ። ሁለቱ ወገኖች ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት የተቋረጠው ወሳኙ የነዳጅ ዘይት ምርትና ሽያጭ ይቀጥላል ። የደረሱበት ስምምነት ደቡብ ሱዳን በሱዳኑ የቀይ ባህር ወደብ በኩል ነዳጅ ዘይት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያስችላታል ። ሆኖም በአሁኑ ድርድር ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃ በወጣችበት ወቅት ያልተፈቱ የአብዮ ግዛትን ጨምሮ ሌሎች አወዛጋቢ ጉዳዮች መፍትሄ አላገኙም ። ሁለቱ ሱዳኖች ስምምነት የተፈራረሙት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ልዩነቶቻቸውን እንዲያስወግዱ ለሶስተኛ ጊዜ ያሰቀመጠው የጊዜ ገደብ ዛሬ ሊያበቃ ሲል ነው ።
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ