ዓለም አቀፍ ፀረ የሞት ቅጣት ቀን እና ጋምቢያ
ረቡዕ፣ መስከረም 30 2005አላማው ሰዎች በፍርድ የማይገደሉባት አለም ለመፍጠር ታስቦ ነው። ዛሬ ምንም እንኳን በርካታ አገሮች ራሳቸውን ከሞት ፍርድ ቢያገሉም በአለም ዙሪያ 57 ሀገሮች የሞት ቅጣትን አላስወገዱም። ምንም እንኳን ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ጋምቢያ እአአ ከ1981 ወዲህ የሞት ቅጣት ብይን አሳልፋ ባታውቅም፣ ባለፈው ነሀሴ ወር መጨረሻ በሀገርዋ የተፈፀመው ግድያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ብርቱ ቁጣ ነበር የቀሰቀሰው።
እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል መዘርዝር በአሁኑ ጊዜ ወደ 20 000 የሚጠጉ ሰዎች የሞት ብይን ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ። አፍሪቃ ውስጥ ከ54 አገሮች 38ቱ የሞት ቅጣት ቀርቶዋል።
በፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜ አገዛዝ ስር የምትገኘዋ ጋምቢያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታይባት ሀገር ሆና ብትታወቅም ባለፈው ነሀሴ መጨረሻ በእስረኞች ላይ የሞቱን ቅጣት መፈፀምዋ ብዙ ትችት መቀስቀሱን የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የጋምቢያ ተንታኝ ሊዛ ሼርማን ኒኮላውስ ሲገልጹ። « ሰዎች በፖለቲካ ዘርፍ ስህተት ከሰሩና በሀገር ክህደት ከተወነጀሉ የሞት ቅጣት ይበየንባቸዋል። ይህ የአለም አቀፉን መመሪያን እጥሳል። ስለ ቁም ስቅል እና ሀሳብን በነፃ በመግለፅ ላይ ጭቆና እንደሚደረግ ሰምተናል። ስለሆነም እኛን የሚያሳስቡን በርከት ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመለከቱ ችግሮች አሉ።»
እአአ በ 1994 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የጨበጡትፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜ ከዚያን ወዲህ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት ይጥራሉ። እስረኞች «ማይል ቱ ሴንትራል» በተባሉ ጣቢያዎች ይታሰራሉ። ይህ ራሱን የቻለ የሞት ቅጣት ነው ይላሉ ባንካ ማኔ፤ ከሰባት የጋምቢያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የተውጣጣ የሲቪክ ድርጅት ሊቀመንበር ናቸው።
« የማይል ቱ ወህኒ ቤት የእስራት ሁኔታ አሰቃቂ ከመሆኑ የተነሳ አንድም እዛው ወህኒ ቤት እንዳለህ ፣ አልያም እስራቱ ባስከተለብህ ጉዳት ትሞታለህ። አብዛኛውን ጊዜ ወይ በወታደሮች ወይንም በፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ነው የሞት ቅጣት ወይም የዕድሜ ልክ እስራት የሚበየነው። የወህኒ ቤቱ አሰራር ይህን ይመስላል። የሚቀርበው ምግብ እጅጉን የተበላሸ በመሆኑ፣ ቤሪቤሪ የተባለ በሽታ ይይዝህና ሰውነትህ አብጦ እጅግ አስከፊ አሟሟት ትሞታለህ።»
በነሃሴ መጨረሻ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሁለቱ የሴኔጋል ዜጎች ነበሩ። በዚህም የተነሳ በጎሬቤት ሀገር ሴኔጋል የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።በተጨማሪም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋምቢያ ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ዝቷል። እንዲሁም ፕሬዚዳንት ጃሜም አለም አቀፉን ደረጃ እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል። ጥሩው ነገር የጋምቢያ መንግስት ለመስከረም አጋማሽ የሞት ፍርድ የበየነባቸውን 38 ሰዎች እስካሁን አልረሸነም። የሞቱ ቅጣት ለጊዜው መቆሙን የፕሬዚደንታዊው ጽህፈት ቤት አስታወቋል። ማኔ ይህንን ውሳኔ በቀና ቢቀበሉም ስጋት አላቸው።
«ይህ ጥሩ ዜና ነው። ይህ መንግስት »ሞራቶሪውም» ሲል ይጠራዋል። ያም ማለት አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ የሞቱን ቅጣት እንደገና ስራ ላይ ሊውል ይችላል። ያህያ ጃሜን እና ባለፉት አመታት የሰሯቸውን ተግባራት የሚያውቅ ሁሉ ለሰው ህይወት ከበሬታ እንደሌላቸው ያውቃል። አንድ ቀን ተነስተው የግድያውን ቅጣት እንደገና ጀምሬያለሁ ሊሉ ይችላል።»
የአውሮፓ ህብረት የሞቱ ቅጣትለጊዜው ቆሞዋል የተባለበትን ውሳኔ ተከተሎ በርግጥ የዛተውን ማዕቀብ መጣሉ ገና በውል አልታወቀም። ዓለም አቀፍ የሞት ቅጣት ውግዘት ቀን ዛሬ ታስቦ በዋለበት ቀን የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪቃ ጠበብት የሞቱን ቅጣት ማስቀረት ስለሚቻልበት ጉዳይ ለሚመለከተው የአውሮፓ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሀሳብ ያቀርባሉ። ምክር ቤቱ ውሳኔ እስኪደርስ ግን ብዙ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።
ኤሪክ ሴጉንዳ
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ