1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመጨረሻም ዊሊያም ሩቶ የምርጫ ኬንያ 2022 አሸናፊ ሆነዋል

ሰኞ፣ ነሐሴ 9 2014

መቼም ያ የደም መፋሰስ ዳግም እንዲመለስ የሚሻ አይኖርም ። ዉጤቱ ምንም ይሁን ምን በሰላም ማለቁ ለኬንያውያን ብቻ ሳይሆን ለተቀሩት አፍሪቃውያን መልካም ዜና ነው። ። ሁለቱን ጉምቱ ፖለቲከኞች አንገት ለአንገት ያተናነቀው ምርጫ ኬኒያ 2022 በዶሮ ነጋዴው እና ምክትል ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ አሸናፊነት ተጠናቋል።

https://p.dw.com/p/4FYvZ

ዊልያም ሩቶ ያሸነፉበት የኬንያ ምርጫ እና ቀጣዩ የኬንያ አንድምታ

መቼም ያ የደም መፋሰስ ዳግም እንዲመለስ የሚሻ አይኖርም ። ዉጤቱ ምንም ይሁን ምን በሰላም ማለቁ ለኬንያውያን ብቻ ሳይሆን ለተቀሩት አፍሪቃውያን መልካም ዜና ነው ። ሁለቱን ጉምቱ ፖለቲከኞች አንገት ለአንገት ያተናነቀው ምርጫ ኬኒያ 2022 በዶሮ ነጋዴው እና ምክትል ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ አሸናፊነት ተጠናቋል። ። ሂደቱ ዘገምተኛ ነበር። በእርግጥ አሸናፊው ማን ይሆን? አስብሏል ። ሽንፈት አይደንቄው እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አንጋፋው ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ ለአምስተኛ ጊዜ ሽንፈት ተከናንበዋል ። 
ኬንያ ለሁለት የሥልጣን ዘመን በፕሬዚደንትነት ያገለገሏትን ኡሁሩ ኬንያታን በይፋ አሰናብታ ምክት ፕሬዚዳንቷን አዲሱ  ፕሬዚደንት አድርጋ ለመቀበል ከጫፍ ደርሳለች። ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው የሕዝብ እንደራሴዎች እና የፕሬዚደታዊ ምርጫ ከአራቱ ዕጩ ፕሬዚደንቶች ሁለቱን ዋነኛ ፖለቲከኞች አስቀርቶ አሸናፊው አስቀድሞ ሳይታወቅ እስከ ዛሬ ዘልቋል።  ያም ሆኖ ግን የዕጩዎቹ ደጋፊዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እያሰራጩ የሚገኙት መረጃዎች ምናልባት የ2017ቱን ሁከት እና ብጥብጥ ዳግም እንዳይጋብዝ አስግቷል። የመንግስታዊ መገናኛ ብዙኃንም ዜጎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ብርቱ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ነው።
ኬንያ በአፍሪቃ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪቃ የተሻለ የምርጫ ስረዓት ፣የተረጋጋ ኤኮኖሚ እና አንጻራዊ ሰላም ካላቸው ሃገራት ተጠቃሽ ናት። ምንም እንኳ በጎረቤት ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ላለፉት አስር ዓመታት እና ከዚያ በላይ የጸጥታ እና ደህንነት ስጋቷ እንደሆነ ዛሬን መዝለቁ፤ በዚያው ልክ የሽብር ቡድኑ ያሳደረው ስጋት የቱሪዝም ገቢዋን አዳክሞ በምጣኔ ሃብቷ ዕድገት ላይ እንቅፋት መፍጠሩ ባያጠያይቅም። 
ኬንያ እንደ ጎረቤቶቿ ሁሉ የተፈጥሮ ጭካኔ በትር ቀማሽ መሆኗ በራሱ ያሳደረው ተጽዕኖም እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በሀገሪቱ የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው የተከታታይ ዓመታት ድርቅ እና ጎርፍ ፤ አለፍ ሲልም በተደጋጋሚ በሯን የሚያንኳኳው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዓመታዊ የሰብል ምርቱን አዳክሞ ከአራት ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን እርዳታ ጠባቂ አድርጎባታል።
ይህ ብቻ አይደለም በጎርጎርሳውያኑ 2017 የተደረገውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኬንያውያን መቼም ሊረሱት አይችሉም። የጎሳ ፖለቲካ ባጠላበት የወቅቱ ምርጫ የአሁኑ ዕጩ ፕሬዚደንት ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበልም ማለታቸውን ተከትሎ በተነሳ የሁለት ጊዜያት ሁከት ኬንያውያን እርስ በእርሳቸው  እንዲሁም ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ1200 በላይ  ሰዎች ተገድለዋል፤ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የንብረት ውድመቱም በቀላሉ የሚገመት አልነበረም። ይህ ለኬንያውያን ጥቁር ጠባሳቸው ነው።
ሰውዬው ዛሬም ድረስ ዘልቀው ነበር ። መወዳደርም መሸነፍም አይሰለቻቸውም ። ብርቱ የስልጣን ጥማት እንዳለባቸው ያለመታከት እና ተስፋ ባለመቁረጥ ለአምስተኛ ጊዜ መወዳደራቸው አሳብቆባቸዋል። ሽንፈት ቁርሳቸው ፣ ሽንፈት ምሳቸው ፤ ሽንፈት እራታቸው የሆነላቸው አይታክቴው ራይላ ኦዲንጋ ።
የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በሥልጣን ላይ የሚገኘው ጁብሊ ፓርቲ እና ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በጋራ የፈጠሩትን አዚሚዮ ላ ሞጃ የተባለ ጥምረት ይመራሉ። ኦዲንጋ የኬንያ ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን ያለፉትን ሶስት ዓመታት የአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማት ልዩ ልዑክ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
ኦዲንጋ የምርጫ ማኒፌስቷቸው የኬንያን ኤኮኖሚ መለወጥ ነው። አባታቸው ጃራሞንጊ ኦጊንጋ ኦጊንጋ የመጀመሪያው የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ። የ77 ዓመቱ ፖለቲከኛ ለኬንያ ፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የአሁኑ 5ኛቸው ነበር። ኦዲንጋ ቢመረጡ የህግ ባለሞያዋ  ማርታ ዋንጋሪ ካሩዋ ምክትላቸው ይሆኑም ነበር ። በነበር ባይቀር።
ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ ። «ብቻዬን ስላልታገልኩ ብቻዬን አልወድቅም» ብለው ነበር  ፤ እነዚያ እንደርሳቸው ተስፋ የማይቆርጡ ደጋፊዎቻቸውን በምርጫ ቅስቀሳው የመዝጊያ ዕለት።
 
አዲሱ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ።  ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሩቶ፤ ቱጃሩ ዶ/ር ዊሊያም ሳሞኢ አራፕ ሩቶ ፤ በቀድሞዎቹ የኬንያ ፕሬዚደንቶች ዳንኤል አራፕ ሞይ እና ምዋይ ኪባኪ ዘመነ መንግስታት ሹመኛ ነበሩ።
ሶስት ፓርቲዎች ያበጁትን ኬንያ ክዋንዛ የተባለ የፓርቲዎች ጥምረት የሚመሩት ዊሊያም ሩቶ ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሰርተዋል። ከዚያ በፊት የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች፤ የግብርና እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን መርተዋል።
በቅርቡ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የኬንያን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ያላቸውን ዕቅድ የ55 ዓመቱ እጩ ፕሬዝዳንት ተናግረው ነበር። ከገዢው ጁብሊ ፓርቲ የተለያዩት ባለፈው ዓመት ነው። ሪጋቲ ጋቻጉዋ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንትነት አብረዋቸው ተወዳድረው በለስ የቀናቸው የመጀመሪያዋ ኬንያዊት ሴት ምክትልፕሬዚደንት ሆነዋል ።
በ,ዚህ ሁሉ ስልጣን ውስጥ አልፈው ምክትልፕሬዚደንት የሆኑት ሩቶ ፤  ይህ ሁሉ አልበቃቸውም ፤አሁን ዋናውን ስልጣን ተቆናጠዋል። እርሳቸው ገንዘብ አላቸው ፤ የናጠጡ ሃብታም ናቸው ፤  ዋናውን ስልጣን ሲቆጣጠሩ ደግሞ ሁሉም ነገር ይቀየራል ። ኃይል ይጨምራሉ ፤ ብርቱም ይሆናሉ ፤ ሩቶ።  አሁን አሉ ሩቶ ፤ «አሁን የመጣነው እንደካሁን ቀደሙ ስልጣን ልንጋራ ሳይሆን የስልጣን ባለቤት ለመሆን ነው ። » 
ሩቶ ያሉትን አድርገዋል። ካሰቡበት ደርሰዋል። በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የምትብጠለጠለው ኬንያም ሴት ምክትል ፕሬዚደንት ማግኘቷ እርግጥ ሆኗል። ይህ የኬንያውያን ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን ከመሰረቱ ባይቀርፍም አንድ እርምጃ መራመዱ ግን የማይታበል ነው።
 
ይህን ለማየት ግን ኬንያውያን የመጨረሻውን ውጤት በተሰፋ መጠበቃቸው አያስገርምም ፤ ምክንያት አላቸው ። ከውጤቱ መታወቅ በኋላ ምን ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ አይቻልም።
በዘንድሮው የኬንያ ምርጫ ከሁለቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች በተጨማሪ ምንም እንኳ ተፎካካሪነታቸው እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም  ጠበቃ እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ዳቪድ ምዋሬ ምርጫውን ያሸንፋሉ የሚል ግምት ከተሰጣቸው ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ ጋር የሚወዳደሩ እጩ ናቸው። ሙስናን ለመዋጋት ቃል የገቡት ዳቪድ ምዋሬ ተሳክቶላቸው ቢመረጡ ሩዝ ሙቼሩ ሙቱዋ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ይሆናሉ።
ሩትስ የተባለ ፓርቲ የሚመሩት ጆርጅ ዋጃኮያህ ደግሞ አራተኛው እጩ ናቸው። ጆርጅ ዋጃኮያህ ቢመረጡ ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ እጽ ኬንያውያን ወደ ውጭ አገር በመላክ ትርፍ እንዲያገኙ ለኢንዱስትሪ እና የሕክምና አገልግሎት ሕጋዊ ሊያደርጉት ቃል ገብተዋል። እጩ ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት ገቢው ኬንያ ያለባትን ዕዳ እና ሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ያግዛል።
 
የዘንድሮው የኬንያውያን ምርጫን ምንም እንኳ  ከቅርብም ሆነ ከሩቅ የታዘቡቱ በርካታ አስተያየቶችን ሲሰጡ ይደመጣል። የወቅቱ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ከምክትላቸው ይልቅ ለቀድሞው ተቀናቃናቸው ድጋፋቸውን መስጠታቸው ደግሞ ምርጫው የበለጠ ተጠባቂ ፤ የበለጠ ቀልብ ሳቢ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አድርጓል። ምንም እንኳ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ኬንያውያን 20 ከመቶ ገደማ የሚሆኑቱ ድምጽ ሳይሰጡ መቅረታቸው ጥያቄ ማስነሳቱ ባይቀርም። ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የአፍሪቃ እና እስያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። የኬንያን ምርጫ እዚያው በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል። የምርጫው ሂደት ከተፎካካሪዎች ቅሬታ ያስነሱ አንዳንድ ችግሮች ያስተናገደ ቢሆንም አንጻራዊ ዴሞክራሲያዊነቱን ግን አልሸሸጉም።
የምርጫ ዘመን መጠናቀቅን ጠብቆ ለቀጣዩ ተወዳዳሪ ስልጣን መልቀቅ ብርቅ በሆነባት አፍሪቃ ኬንያ ይህን ማድረጓ በእርግጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለጠማቸው አፍሪቃውያን  ይህ ተስፋ ነው። በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት አንጋፋው ፖለቲከኛ መረራ ጉዲናም ምርጫውን ለመታዘብ ኬንያ ሰንብተዋል። በአፍሪቃ ምርጫ የሚመስል ነገር ማየታቸውን መረራ ይናገራሉ።
ኬንያውያን በምርጫ ስልጣን ማሸጋገር መጀመራቸው በእርግጥ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ካሁን ቀደም አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙትን ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ ሶስት ፕሬዚደንቶች በምርጫ ወደ ስልጣን መጥተዋል። የስልጣን ዘመናቸው ሲጠናቀቅም ስልጣናቸውን በሰላም አስረክበዋል። ይህ ኬንያውያን የተከተሉት የዴሞክራሲ ስረዓት ለአፍሪቃውያን መልካም ዕድል መሆኑ ነው የሚገለጸው። በምርጫው ለመታዘብ ከተጋበዙት አንዱ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ናቸው። የኬንያ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ሰራተኞች ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ያደረጉትን ጥረት በመልካምነቱ አንስተዋል።  
አንድ ነገር ግን ልብ ይሏል። ይህ ምርጫ ነው። እንኳንስ በዴሞክራሲም በኤኮኖሚም ገና ድክ ድክ የምትለው አ,ፍሪቃዊቷን ኬንያን ይቅር እና የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት እና የፈረጠመ ኤኮኖሚያዊ አቅም ያጎለበቱቱ ሃገራት በምርጫ ሲፈተኑ ይታያል። ለአብነት የዴሞክራሲ መጠለያ ነን የምትለው ታላቋ አሜሪካ ሳትቀር የተንገዳገደችበትን የቅርብ ጊዜውን ምርጫ ማስታወሱ ይበቃል። ኬንያውያን ዕጩ ፕሬዚደንቶች ምንም እንኳ ዉጤቱን በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ቢያሳውቁም ስለደጋፊዎች በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይህ በራሱ ስጋት ነው። የአፍሪቃ እና እስያ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶ/ር ሳሙኤል ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።
የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከመደረጉ ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ ኬንያውያን የሚደግፏቸው ዕጩዎች እንዳሸነፉ በመግለጽ በየፊናቸው አደባባይ ወጥተዋል። ራይላ ኦዲንጋ ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው በሚባለው የምዕራብ ኬንያ ግዛት በሆነችው ኪሱሙ በርካታ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተዋል። ይህ በራሱ አስፈሪ ነው። 
ምርጫው ከተደረገበት ዕለት አንስቶ በነበረው የድምጽ ቆጠራ ለጥቂት ቀናት የወቅቱ ምክትል ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በጥቂት የድምጽ ልዩነት የመሩ መስለው ነበር። ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ደግሞ በምርጫው ኮሚሽን በተረጋገጡ ቆጠራዎች የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ በጥቂት የድምጽ ልዩነት መምራት መጀመራቸው ተዘግቦ ነበር። ይህ ከ24 ሰዓታት አላለፈም ። የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ትናንት እሁድ 50 ከመቶውን ድምጽ ቆጥሮ ማረጋገጫ በሰጠበት ጊዜያዊ ውጤት ደግሞ ዊሊያም ሩቶ 51 ከመቶ ድምጽ በማግኘት እንደገና መምራት መጀመራቸው ይፋ ሆኗል። ዛሬ ሰኞ ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ አሸናፊነታቸው ይፋ ተደርጓል።   ነገር ግን አሁንም ቢሆን ጊዜው ገና ነው። የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በድምጽ ቆጠራ ማዕከላት ተጭበርብረናል በሚል በምርጫ ሰራተኞች ላይ እያደረሱ ያለው ውትወታ እና ወከባ የምርጫ ኮሚሽኑን ኃላፊዎች አሳዝኗል። ይህ ደግሞ የአድማ በታኝ ፖሊሶ እንዲሰማሩ እስከማስገደድም አድርሶነበር። ሁኔታው የድምጽ ቆጠራ ሂደቱንም የበለጠ ቀሰስተኛ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽዖ ስለማበርከቱ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ቀኑ መድረሱ አይቀርም ፤ እነሆ ደረሰ ። የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ስልጣን ከቤተሰባዊ ፉክክር እና ሽኩቻ ወጥቶ ከዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ የሀብት እና የስልጣን ማማ ላይ በደረሰው ዊሊያም ሩቶ አሸናፊነት ተደመደመ   ። አሁን የሚጠበቀው ኦዲንጋ እንደቃላቸው ሩቶን  እንኳን ደስ ያልዎት ብለው እጃቸውን ይጨብጡ ይሆን ? ወይስ ሌላ ሃሳብ ይኖራቸው ይሆን? ደጋፊዎችስ ከሁከት እና ብጥብጥ ታቅበው ለሰላም ተሸንፈው ሁሉም በጋራ አሸናፊነታቸውን ያረጋግጡ ይሆን?  ሰላም ለኬንያ አበቃሁ።
 ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ
 
 

Daniel Bekele | Leiter der äthiopischen Menschenrechtskommission
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images
Äthiopien Addis Abeba Oromo Federalist Congress (OFC)
ምስል Seyoum Getu/DW
Wahlen in Kenia I William Ruto
ምስል Mosa'ab Elshamy/AP/picture alliance
 Wahlen in Kenia I William Ruto
ምስል Brian Inganga/AP/picture alliance
Wahlen in Kenia I William Ruto
ምስል Mosa'ab Elshamy/AP/picture alliance