1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ወንጀሉን አልፈጸምንም” እነ አቶ ጃዋር መሃመድ

ሰኞ፣ መጋቢት 13 2013

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በተፈጠረው ሁከት ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የተከሰሱት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ አመራሮች ዛሬ የእምነት ክዴት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

https://p.dw.com/p/3qxdh
Äthiopien Jawar Mohammed
ምስል Tiksa Negeri/Reuters

«ኦሮሞና አማራ የዚህ ሀገር ግንድ ህዝብ እንደመሆናቸው ልሂቃንን በማቀራረብ ታግያለሁ» ጃዋር መሃመድ

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በተፈጠረው ሁከት ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የተከሰሱት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ አመራሮች ዛሬ የእምነት ክዴት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

በእለቱ ከቆዩበት የረሃብ አድማ ባለማገገማቸው በሃኪሞቻቸው እረፍት ተሰጥቶአቸዋል የተባሉት አቶ ጃዋር መሃመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሃምዛ አዳነን ጨምሮ የተቀሩት አምስት ተከሳሾች የእምነት ክዴት ቃላቸውን ዛሬ ሰጥተዋል፡፡

የዛሬ ሳምንት ማለትም መጋቢት 6 በዋለው ችሎት ላይ ያልተገኙት አራት ተከሳሾች ማለትም አቶ ጃዋር መሃመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ አዳኔ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ዛሬ የእምነት-ክደት ቃላቸውን የሰጡት በጽሁፍ እንዲያመጡ የተጠየቁት የሃኪም ማስረጃን አቅርበው ነው፡፡ ቀሪው አንድ ተከሳሽም በእለቱ አስተርጓሚ ባለመዘጋጀቱ ለዛሬ ባደረው መዝገብ በአፋን ኦሮሞ በአስተርጓሚ የእምነት ክደት ቃሉን ሰጥተዋል፡፡

ዛሬ በቀዳሚነት የእምነት ክደት ቃላቸውን የሰጡት ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ የተመሰረተባቸውን ሶስት ክሶች አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ጃዋር እራሳቸውን በተከላከሉበት ንግግራቸውም “የተመሰረተብኝ ክስ እኔና ፓርትዬ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ኦፌኮን ከምርጫ ለማግለል እና በህዝብ ዘንድ መልካም ስሜን ለማጥፋት ነው” ብለዋል፡፡

አቶ ጃዋር የተከሰሱበት ብሔርን በብሔር ላይ የማነሳሳት፣ አመራር ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ማዘዝ እና በትጥቅና በኃል መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ አስረሃል የሚሉትን ክሶች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውበት ተከላክለዋል፡፡

ከክርስቲያን እና ሙስሊም ቤተሰቦች ተወልደው በማደግ የክርስትና እምነት ተከታይ የትዳር አጋር ጋር ተጣምረው መኖራቸውን ጠቁመው፤ “በተከሰስኩበት ፋይል እንኳ የኦርቶዶክስ እና ፕሮተስታንት እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታዮች እያሉ በአንድ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ቅስቀሳ ካደረኩ እንደምን ከኔ ጋር ሊተባበሩ ቻሉ” በማለት ክሱን አጣጥለውታል፡፡

ክሱ ለስም ማጥፋት የተመሰረተብኝ ነው ያሉት አቶ ጃዋር በኦሮሞ ትግል ውስጥ ጥርስ እንደነቀለና ለእኩልነት እንደመታገሌ እንዴት የብሔር ግጭት አነሳሳለሁ፤ ሕወሃት መራሽ ያሉት አመራር ከስልጣን ለማውረድ አንድም የትግራይ ተወላጅ ላይ በኦሮሚያ ጥቃት አለመነጣጠሩን አነሱ፡፡

Äthiopien Politiker Bekele Gerba
ምስል Addis Standard Magazine

ኦሮሞ እና አማራ የዚህ ሀገር ግንድ ህዝብ እንደመሆናቸው ታሪካዊ ቁርሾ ተገፎ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ መፍትሄ እንዲመጣ ልሂቃንን በማቀራረብ ታግያለሁ ያሉት አቶ ጃዋር በሶማሌና ኦሮሞ አዋሳኝ፣ በሀረረር እና በድሬዳዋ የሚታይ ያሉት ሰላም እንዲመጣ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን አስታውሰው የብሔር ግጭት መፍጠር በሚል የተመሰረተባቸውን ክስ አጣጥለዋል፡፡

በትጥቅ መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ የቀረበባቸውን ክስ በማስመልከትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢ የነበረውን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ህይወታቸውን ጭምር አደጋ ላይ ጥለው ከአባገዳዎች ጋር ሆነው ትጥቅ ለማስፈታት ሰራሁ ያሉትን ተግባር አስታውሰው፤ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ያደርጋል ያሉትን ኦፌኮን መቀላቀላቸውን በማንሳት የሀሰት ክስ ሰለባ የፖለቲካም እስረኛ መሆናቸውን አብራርተዋል አቶ ጃዋር፡፡

ሌላው ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ በሰጡት የእምነት ክደት ቃል የተከሰሱበትን ወንጀል አለመፈፀማቸውን ከሚያራምዱት የፖለቲካ ርዕዮት ጋር አያይዘው ነው ያብራሩት፡፡ አስተዳደጌም እምነቴም ብሔርን በብሔር ላይ ለማነሳሳት አይፈቅዱልኝም ሲሉ የሞገቱት አቶ በቀለ፤ ለሁሉም ብሔር ክብር እንዳላቸውና ለሰላማዊ ትግል ቦታ በመስጠት የማህተመጋንዲ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተከታይ ለመሆናቸው ጽፈው ያስቀመጡት መፅኃፍት ዋቢ መሆናቸውን አመለከቱ፡፡

መንግስት ላይ ህዝብ በማነሳሳት ቀርቦብኛል ላሉት ክስም አቶ በቀለ የሰጡት ማብራሪያ “እኔ ግለሰብ አይደለሁም፡፡ የአንድ ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር እንደመሆነ የለውጥ መንግስት ሀዲዱን በመሳቱ ህዝብ እንዳይመርጣቸው በሰላማዊ መንገድ ቅስቀሳ አድርጌያለሁ፤ ይህ ሊያስከስሰኝ አይገባም” ነው ያሉት፡፡

Symbolbild Gericht Gesetz Waage und Hammer
ምስል Fotolia/Sebastian Duda

“የኦሮሞን ህዝብ የገደለው ነፍጠኛ ነው በዚያ ስር አትተዳደሩም” ብለሀል በሚል ክስ እንደቀረበባቸው ያመለከቱት አቶ በቀለ፤ የነፍጠኛን ስርዓት ከአንድ ብሔር ጋር አያይዘው ማንሳት ፍጹም የማያምኑበት እና የተሳሳተ ትርጉም የተሰጠው ነው በማለት የክሱን አካሄድ ተችተዋል፡፡ ይህንንም የምለው ክሱን ለማምለጥ ሳይሆን ፍጹም ስለማምንበት ነው ያሉት ፖለቲከኛ በቀለ ገርባ በኢትዮጵያ ብዝሃነትን ለማስፈን ከሚሰሩት ጎራ እንደሚሰለፉ ተናግረው፤ የቀረበባቸውን ክስ በተራ ውንጀላ በመፈረጅ ዓላመውን ፖለቲካዊ ማግለል ብለው ገልጸውታል፡፡

አቶ ሃምዛ አዳኔም የቤተሰባቸውና የአስተዳደጋቸው የኋላ ታሪክን በማጣቀስ የተከሰሱበት የብሔር ግጭት የማነሳሳት ወንጀል ከመንግስታዊ ለውጡ በኋላ ተዟዙረው ሲሰሩ ከነበረበት ተግባርም ጋር የሚጻረር መሆኑን በማንሳት የተጠረጠሩት ወንጀል ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ክስ በማለት ወንጀሉን አልፈጸምኩም ወንጀለኛም አይደሉም ሲሉ የእምነት ክደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

9ኛ ተከሳሽ አቶ አለማየሁ ገለታ እና 13ኛ ተከሳሽ አቶ ሸምሰዲን ጠሃም ወንጀል አለመፈፀማቸውንና ለምን በእስር ላይ እንደሆኑ እንደማያውቁ ነው የተናገሩት፡፡

ይህን ተከትሎም የተከሳሾች ጠበቆች ለአብዛኞቹ የዋስትና መብት ተጠብቆላቸው እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም፤ የአቃቤ ህግ ተወካይ ምንም እንኳ ተከሳሾች ወንጀሉን አልፈጸምንም ቢሉም የተከሰሱበት ወንጀል የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ የዋስትና መብትም የማያሰጥ በመሆኑ ክሱ እንዲቀጥል ተከራክሯል፡፡

የዋስትና መብትን የተመለከቱ ጥያቄዎች በቀጣይ ቀጠሮዎች ይታያሉ ያለው ፍርድ ቤቱም መጋቢት 28 የምስክሮች ጥበቃ ላይ ብይን ሰጥቶ መጋቢት 29 እና 30 እንዲሁም ሚያዚያ 5፣ 6፣ 7፣ 12፣ 13 እና 14 2013 ዓ.ም. የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል እንዲሰማ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ