1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ፤ በናይሮቢ የአስክሬን ቁርጥራጮች መገኘትና ህዝባዊ ተቃዉሞ

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016

የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በሃገሪቱ የግብር ጭማሪ ለማድረግ እቅድ መያዛቸዉን ተከትሎ ኬንያን ሲያናዉጥ የነበረዉ ተቃዉሞ ጋብ ቢልም ተቃዋሚዎች ሌላ የተቃዉሞ ሰልፍ ለማድረግ እቅድ መያዛቸዉን እየገለፁ ነዉ። የኬንያ ፖሊስ፤ ከግድያዉ ጋር በተያያዘ አንድ ተጠርጣሪ ገለሰብን በቁጥጥር ስር አዉሏል።

https://p.dw.com/p/4iJLP
 በናይሮቢ የአስክሪን ቁርጥራጮች መገኘትና ፖሊስ ላይ የደረሰ ያለዉ ጫና
በናይሮቢ የአስክሪን ቁርጥራጮች መገኘትና ፖሊስ ላይ የደረሰ ያለዉ ጫናምስል Monicah Mwangi/REUTERS

ኬንያ፤ በናይሮቢ የአስክሪን ቁርጥራጮች መገኘትና ፖሊስ ላይ የደረሰ ያለዉ ጫና

ኬንያ፤ በናይሮቢ የአስክሪን ቁርጥራጮች መገኘት እና ፖሊስ ላይ የደረሰ ያለዉ ጫና

የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በሃገሪቱ  የግብር ጭማሪ ለማድረግ እቅድ መያዛቸዉን ተከትሎ ኬንያን ሲያናዉጥ የነበረዉ ተቃዉሞ ጋብ ቢልም ተቃዋሚዎች ሌላ የተቃዉሞ ሰልፍ ለማድረግ እቅድ መያዛቸዉን እየገለፁ ነዉ። ባለፈዉ ቅዳሜ ሐምሌ ስድስት ቀን መዲና ናይሮቢ በሚገኝ ግዙፍ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ የተቆራረጡ የሴት አካላት የተሞሉ  ከረጢቶች መገኘታቸዉን ፖሊስ ይፋ ማድረጉ በህዝቡ ዘንድ ሌላ ጥርጣሬ እና ቁጣን ቀስቅሶ ነበር የሰነበተዉ። የኬንያ ፖሊስ ዛሬ እንዳስታወቀዉ ፤ ከግድያዉ ጋር በተያያዘ አንድ ተጠርጣሪ ገለሰብ መያዙን አስታዉቋል።  

ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ ኬንያ ናይሮቢ ዉስጥ በሚገኝ ግዙፍ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በፕላስቲክ ከረጢት ታጭቆ የተገኘዉ የሴት አካላት ቁርጥራጭ በሃገሪቱ ተጨማሪ ቁጣን ቀስቅሶ ነዉ የሰነበተዉ። ፖሊስ ቀደም ሲል ናይሮቢ ላይ በሰጠዉ መግለጫ፤ ሰዎቹ ህይወታቸዉ ያለፈዉ ከከባድ ባዕድ አምልኮ ጋር በተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ሲል ገልፆ ነበር። ዛሬ የኬንያ ፖሊስ ይፋ እንዳደረገዉ፤ ሰዎችን በተገዳዳይ ሲገድል የነበረ የ 33 ዓመት ግለሰብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና  ድርጊቱንም ማመኑን አስታዉቋል። ተጠርጣሪው 42 ሴቶችን ከገደለ በኋላ የተቆራረጠ አካላቸውን በአንድ የናይሮቢ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማከማቸቱንም ፖሊስ አስታውቋል። ግለሰቡ ከጎርጎረሳዉያኑ 2022 ጀምሮ ህጋዊ ሚስቱን  ጨምሮ 42 ሴቶችን እስከ አለፈዉ ሳምንት ድረስ ዚገድል መቆየቱን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።  በኬንያ የግብር ጭማሪን ተከትሎ በሃገሪቱ የታየዉን ከፍተኛ ፀረ መንግስት ተቃዉሞን ለመመበተን የፖሊስ መኮንኖች ሰፊ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽመዋል በሚል ክስ እቀረበበ ባለበት የተቆራረጡ አስክሬኖች በቆሻሻ ስፍራ ተጥለዉ መገኘታቸዉ የተቃዋሚን ጥርጣሬ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎት ነበር የሰነበተዉ። አንዲት የኬንያ ነዋሪ ወጣት ቀደም ሲል ለዶቼ ቬለ እንደገለፀችዉ፤ የዘጠኙ ሴቶች አገዳደል ሁኔታ አጠራጣሪ ነዉ።  

"ጠዋት ላይ የስድስት ሴቶች አስከሬን ተገኘ። አሁን ደግሞ የሁለት ሴቶች አስክሪን ቁርጥራጭ ተገኝቷል። እነዚህ ሰዎች ከተቃውሞ ሰልፍ ላይ ታፍነው ከተወሰዱት ሰዎች መካከል ስለመሆን አለመሆናቸዉ የምናዉቀዉ ነገር የለም። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የአካላት ቁርጥራጮች የሴቶች በመሆናቸዉ፤ በሴቶች  ላይ ያነጣጠረ ወንጀል ይሁን አልያም  በተቃዉሞ ሰልፉ ላይ በመሳተፋቸዉ የተገደሉ ስለመሆናቸዉ እርግጠኞች አይደለንም።"

በኬንያ የግብር ጭማሪ እቅድ ያስነሳዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ

በኬንያ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀሰቀሰዉን ፀረ መንግሥት ተቃዉሞ ተከትሎ ፖሊሶች በርካታ ሰዎችን በጥይት መተዉ ገድለዋል፤ አቁስለዋል ብሎም በዘፈቀደ አስረዋል ሲሉ  የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፖሊሶችን ተጠያቂ አድርገዋል። ይህን ተከትሎ የሃገሪቱ የፖሊስ ዋና አዛዥ ባለፈዉ አርብ የስራ መልቀቅያ ደብዳቤ ማስገባታቸዉ አይዘነጋም።

 በናይሮቢ የአስክሪን ቁርጥራጮች መገኘትና ፖሊስ ላይ የደረሰ ያለዉ ጫና
በናይሮቢ የአስክሪን ቁርጥራጮች መገኘትና ፖሊስ ላይ የደረሰ ያለዉ ጫናምስል AP Photo/picture alliance

በኬንያዉ ሀገር አቀፍ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሃገሪቱ የሚታየዉ ሙስናን እና መጥፎ አስተዳደር እንዲቆም፤ ፕሬዚዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ  የሚጠይቅም ነው። 

«በዚህች ሀገር ሙስና ይቁም። ለሴቶች እና ህጻናት እንክብካቤና ክብር መሰጠት አለበት። ዛሬ ይህን ስንናገር የፓርላማ አባላት ደሞዛቸው እየጨመረ ነው ።  የመምህራን ግን የሰሩበት ደሞዝ እንኳን አልተከፈላቸውም። መንግሥት ግን ስለ በጀት እያወራ ነው።»

« እኛ ምንም አይነት ዉይይት አንፈልግም ግምፅነት እና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ብቻ እንፈልጋለን። የፕሬዚደንቱን ይቅርታ አንፈልግም» በኬንያ በሰላማዊ መንገድ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ አመጽ፣ ዘረፋና ሥርዓት አልበኝነት ሁኔታን በመያዙ በርካታ የሃገሪቱን ህዝብ ስጋት ላይ መጣሉ አልቀረም። የኬንያ ሰላማዊ ተቃዉሞ አስተባባሪዎች ለነገ ማክሰኞ ህዝብ ለተቃዉሞ ሰልፍ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል። 

አዜብ ታደሰ / አይዛክ ካሊጂ

ታምራት ዲንሳ