1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጉዳት የተመለሰው ቀነኒሳ በቀለ የበርሊን ማራቶንን አሸነፈ

እሑድ፣ መስከረም 18 2012

ቀነኒሳ በቀለ እና አሼቴ በከሬ በበርሊን ማራቶን አሸነፉ። ቀነኒሳ በውድድሩ ከዓለም ክብረ ወሰን ሁለት ሰከንድ ብቻ ዘግይቶ ገብቷል። «በጣም አዝናለሁ። እድለኛ አይደለሁም። የግሌን ምርጥ ሰዓት መሮጥ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። አቅሜን አውቀዋለሁ። ተስፋ አልቆርጥም» ያለው ቀነኒሳ የዓለም ክብረ ወሰንን ለማሻሻል ሙከራውን እንደሚቀጥል ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/3QRcs
Berlin Marathon 2019
ምስል Imago Images/A. Gora

ቀነኒሳ ጉዳት ላይ መቆየቱ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ተናግሯል

ከጉዳት የተመለሰው ቀነኒሳ በቀለ ኢትዮጵያውያን የበላይ የሆኑበትን የበርሊን ማራቶን በ2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል። የ37 አመቱ ቀነኒሳ 42.195 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ውድድር ያጠናቀቀበት ሰዓት ከዓለም ክብረ ወሰን በሁለት ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነው።

በበርሊን በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. የተካሔደውን ውድድር በ2 ሰዓት ከ3 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ ያጠናቀቀው ቀነኒሳ በዛሬው ውድድር የግሉን ሰዓት ቢያሻሽልም «ደስተኛ አይደለሁም» ብሏል።

«በጣም አዝናለሁ። እድለኛ አይደለሁም። የግሌን ምርጥ ሰዓት መሮጥ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። አቅሜን አውቀዋለሁ። ተስፋ አልቆርጥም» ያለው ቀነኒሳ የዓለም ክብረ ወሰንን ለማሻሻል ሙከራውን እንደሚቀጥል ተናግሯል።

Berlin Marathon 2019
ምስል Imago Images/A. Gora

ቀነኒሳ ከውድድሩ ቀደም ብሎ እንደተናገረው ከገጠመው ጉዳት ካገገመ በኋላ ለበርሊን ማራቶን የሶስት ወር ዝግጅት ብቻ ነበር ያደረገው። የውድድሩን ግማሽ በ1 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ ከተጠበቀው በፈጠነ ሰዓት ሮጧል። ቀነኒሳ 21 ኪሎ ሜትር ሲሮጥ ኢትዮጵያውያኑ ብርሐኑ ለገሰ፣ ሲሳይ ለማ፣ ልዑል ገብረ ስላሴ እና ኬንያዊው ጆናታን ኮሪር አብረውት ነበሩ። በውድድሩ መካከል የቀነኒሳ ፍጥነት ሲቀዛቀዝ ታይቷል።

Deutschland Berlin Marathon Kenenisa Bekele
ምስል DW/Y. H. Hinz

ቀነኒሳ ውድድሩን ካጠናቀቀ በኋላ "ታፋዬ ላይ ችግር ነበረብኝ። ከጉዳት ገና ማገገሜ ነው። ዝግጅቴ በቂ አልነበረም» ሲል ተናግሯል።

በውድድሩ ብርሀኑ ለገሰ በ2 ከ2 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ ቀነኒሳን ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላው ኢትዮጵያዊ ሲሳይ ለማ በ2 ሰዓት ከ3 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል።

የበርሊን ማራቶንን በ2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ በእለተ እሁድ በተካሔደው ውድድር ይሳተፋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ሳይገኝ ቀርቷል።

ኪፕቾጌ በመጪው ጥቅምት ወር በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና በሚዘጋጅ ልዩ ውድድር ማራቶንን ከ ሁለት ሰዓት በታች በማጠናቀቅ የመጀመሪያው አትሌት ለመሆን በሚያደርገው ዝግጅት ሳይሳተፍ መቅረቱ ተሰምቷል።

በሴቶች በተደረገው የበርሊን ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አሼቴ በከሬ አሸናፊ ሆናለች። አሼቴ ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ አጠናቃለች። ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ማሬ ዲባባ በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ውድድሩን በማጠናቀቅ ሁለተኛ፣ ኬንያዊቷ ሳሊ ቼፒዬጎ በ2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ6 ሰከንድ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

እሸቴ በቀለ