1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

ከአዲስ አበባ ወደ ከሚሴ ሲጓዙ የተገደሉት ሰዎች

ረቡዕ፣ የካቲት 20 2016

ባለፈው ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከሚሴ ሲጓዙ የነበሩ መምህራንና ሌሎች ሰዎች ከህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ወርደው መገደላቸው ተሰምቷል። የእረፍት ጊዜያቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር አሳልፈው የትምህርት መጀመርን ተከትሎ ወደ ከሚሴ ሲጓዙ ከተገደሉ አንዱ መምህር ኤፍሬም እንዳሉ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4czxp
ከሚሴ ከተማ
ከሚሴ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ከአዲስ አበባ ወደ ከሚሴ ሲጓዙ የተገደሉት ሰዎች

የቤተሰብ አስተያየት

ኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ ተወልደው ያደጉት ሟች መምህር ኤፍሬም እንዳሉ የ44 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ በከሚሴ አካባቢ ለ15 ዓመታ ገደማ በመምህርነት ማገልገላቸውን ወንድማቸው ፈይሳ እንዳሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የሟች ወንድም እንደሚሉት መምህር ኤፍሬም ከውስን ጓደኞቻቸው እና ሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር ሆነው ከአዲስ አበባ ወደ ከሚሴ በሚጓዙበት ወቅት ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በታጣቂዎች ተወስደው ህልፈታቸውን በሶስተኛው ቀን መስማታቸውን ገልጸዋልም።

እንደ የሟች ቤተሰብ ገለጻም የመምህር ኤፍሬም አስከሬን ከሌሎች ስምንት ሟቾች ጋር በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከተገደሉበት ወደ ሰንበቴ ጤና ጣቢያ ከተወሰደ በኋላ በዚያው በጂሌ ዱሙጋ ሰንበቴ ከተማ ተቀብሯል። ኤቢሴ መገርሳ ደግሞ የሟች መምህር ኤፍሬም እንዳሉ ባለቤት ናቸው። ሁለት ልጆችም አፍርተዋል። እሳቸውም ከመምህር ባለቤታቸው ጋር በተመሳሳይ ሙያ በዚያው በኦሮሞብሔረሰብ ልዩ ዞን ለዓመታ ቢያገለግሉም እየከፋ የመጣው የጸጥታ ሁኔታ አካባቢውን እንዲለቁ አስገደዳቸው። ባለቤታቸው ግን በዚያው ለመቆየት ግድ ሆነባቸው።

«ለሁለት ሳምንት እረፍት ነበር እኔና ልጆቹን ለመጠየቅ ጥር 27 መጥቶ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደዚያው ወደ መምህርነት ስራው እየተመለሰ የነበረው። ከመኪና ውስጥ አውርደው ካሰቃዩዋቸው በኋላ ነው ይህን የከፋ ጉዳት ያደረሱባቸው።» በማለትም የደረሰውን ያስረዳሉ።

ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ
ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ

የሟች መምህር ኤፍሬም ባለቤት ወ/ሮ ኤቢሴ ረቡዕ የካቲት 13 ባለቤታቸው እንደተያዘ መደወሉንም ገልጸዋል። «ከተያዘ በኋላ እኩለ ቀን ለስድስት 20 ጉዳይ አከባቢ ደውሎ ተይዣለሁ የምንማርም አይመስለኝም ልጆቼን አደራ አሳዲጊልኝ፤ ቻው አለኝ» ሲሉ በመጨረሻው ሰዓት በስልክ ያስተላለፉትን መልእክትም ዘርዝረዋል። ፡

የሟቾች የቀብር ሁኔታ

መምህራኖች እና ከመኪና እንዲወርዱ ተደርገው የተገደሉ ስምንት ሰዎች አስከሬን ወደ ጂሌ ዱሙጋ ሰንበቴ ከተማ ተወስዶ እንደየሃይማኖታቸው በእስልምና፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና መካነ የሱስ የቀብር ስፍራዎች መቀበራቸውን የገለጹልን ደግሞ ነዋሪነታቸውን በሰንበቴ ያደረጉና መምህር ኤፍሬምን ጨምሮ የተገደሉትን ሦስት መምህራኖች በቅርበት የሚያውቋቸው ግለሰብ ናቸው። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ መምህር ኤፍሬም ዓይነስውር እናቱን እና ሌሎች ተናናሾቹንም በዚሁ ሥራው ያስተዳድራቸው ነበር። ከዓርቡ ጥቃት በኋላ የፌዴራል መንግሥት ከደብረብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደውን አውራ ጎዳና መዝጋቱን አሳውቋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ