1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአንዲት ወጣት ጭንቅላት ውስጥ 1.6 ኪ/ግ የሚመዝን ዕጢ በህክምና ተወገደ

እሑድ፣ ነሐሴ 26 2016

በአዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል ከአንዲት ሴት ጭንቅላት ውስጥ 1.3 ኪሎ ግራም (ኪ.ግ) የሚመዝን እጢ ማውጣት መቻላቸውን ዶክተሮች አስታወቁ፡፡ በሆስፒታሉ የአንጎል ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶ/ር ገረመው ሰንበታ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ከ6፡00 ሰዓት በላይ በፈጀው ስኬታማ ያሉት ቀዶ ጥገናው ታካሚዋ በውስን ቀናት ብቻ ከህመም ማገገም ችላለች፡፡

https://p.dw.com/p/4k8G5
Äthiopien Bahirdar | Komplizierte Schädeloperation
ምስል Privat

ውስብስብ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና ተደረገ

ከአንዲት ወጣት ሴት የወጣው ከባድ የጭንቅላት እጢ

በአዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል ከአንዲት ሴት ጭንቅላት ውስጥ 1.3 ኪሎ ግራም (ኪ.ግ) የሚመዝን እጢ ማውጣት መቻላቸውን ዶክተሮች አስታወቁ፡፡

በሆስፒታሉ የአንጎልና ህብረሰረሰር ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶ/ር ገረመው ሰንበታ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ከ6፡00 ሰዓት በላይ በፈጀው ስኬታማ ያሉት ቀዶ ጥገናው ታካሚዋ በውስን ቀናት ብቻ ከህመም ማገገም ችላለች፡፡

 

የ28 ዓመት እድሜ ወጣት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ተነስታ ወደ አዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል እንድታቀና ያስገደዳት ይሰማት የነበረው ከባድ እራስ ምታትና ለሁለት ዓመታት የከረመባትን በጭንቅላቷ ላይ የታየው እብጠት ለመታከም ነው፡፡ የጠባይ መቀያየር፣ መነጫነጭና ማንቀጥቀጥ በታማሚዋ ላይ ይስተዋሉ ከነበሩ የህመሙ ምልክቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸውም ተብሏል፡፡ የልጆች እናት የሆነችው የ28 ዓመት ወጣቷ ታከካሚ ላይ ይታይ የነበረው እብጠትም የቀዶ ህክምና እንደሚፈልግ ያመኑት የሆስፕላቱ ዶክተሮች ባለማንገራገር ለቀዶ ህክምና የሚሰጠውን መድሃኒት አስቀድሞ በመስጠት ያስተኙአታል፡፡ በአለርት ሆስፒታል የአንጎልና ህብረሰረሰር ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶ/ር ገረመው ሰንበታ የቀዶ ህክምናው ቡድን መሪ ናቸው፡፡

የጭንቅላት ዕጢ እና ያለው ህክምና

“እንደደረሰች ያየንባት አንጎሏ ከፊትለፊት በኩል በጣም አብጧል፡፡ እንደነገረችንም የራስ ምታትና መንቀጥቀጥ ነበረባትና መድሃኒት ሰጥተናት፤ የኤም.አር.አይ. ምርመራም ስደረግላት እጢው አንጎል ውስጥ የአንጎል ሽፋኑን አጥንቷንም ሙሉ በሙሉ መብላቱን እንዲሁም ወደ ውጪም ማደጉን ተመልክተን ብቸኛው አማራጩ በቀዶ ትገና ማስወገድ በመሆኑ ወደዚያው ገባን” ይላሉ፡፡

ለታካሚዋ የቀዶ ጥገናው ስሰራላት የመጀመሪያው ስራ የነበረው ከአንጎል አጥንት ውጪ ያለውን እጢ ማውጣት ነበር፡፡ ከዚያም ስራው ቀጠለ፡፡ “ቀጥለን እጢው ባለበት በኩል በፊትለፊቱ በኩል ተቆርጦ ወጣ፡፡ ከዚያም አንጎል ውስጥ የቀረው እጢ ተቆርጦ እንዲወጣ አደረግን” ብለዋል፡፡

ውስብስብ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና
ለታካሚዋ የቀዶ ጥገናው ስሰራላት የመጀመሪያው ስራ የነበረው ከአንጎል አጥንት ውጪ ያለውን እጢ ማውጣት ነበር፡፡ ምስል Privat

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን መጠቀም ትሻለች

ነሃሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከናወነው ይህ የአንጎልና ራስቅል ቀዶ ጥገና ከስድስት ሰዓታት በላይ የፈጀ ከባድ የቀዶ ጥገና ህክምና መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ “መሰል ህክምናን አስቸጋሪ የሚያደርገው ያው ከፍተኛ ደም መፍሰሱ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ከእጢው ስር ከአንጎላችን ደም ሰብስቦ ወደ ሌላው ሰውነት አካል ሚመልስ ትልቅ የደም ባምቧ አለ፡፡ ከዚያ መለየት ነው ትልቁን ጊዜ የወሰደው፡፡ በመሆኑም እንደዚህ አይነት ህክምና ከፍተኛ የደም መፍሰስ እንደሚኖረው ተረድተን በቂ ደም አዘጋጅተን ነው ወደ ቀዶ ጥገናው ገባነውና ምንም አይነት እክል ሳያጋጥመን ነው ህክምናውን በስኬት ያጠናቀቅነው” ብለዋል የአንጎልና ህብረሰረሰር ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ገረመው፡፡

የልብ ቀዶ ሐኪሙ ዶክተር አበበ ኪቢ ገመቹ 

ረጅም ሰዓታትን በፈጀው በዚህ ከባድና ውስብስብ የቀዶ-ጥገና ህክምናም 1.3 ኪ.ግ. የሚመዝን ከባድ እጢ ከአንዲት ታካሚ ሴት ጭንቅላት ተወገደ፡፡ “ከአጥንቱ ውጪ ያለው እጢው ብቻ 1.3 ኪ.ግ ነው የሚመዝነው፡፡ አጥንቱም በእጢው ብበላም የተጋነነ ይሆናል በሚል በዚህ ሚዛን ውስጥ አላካተትንም” ነው ያሉት፡፡

ለ18 ሺህ ኢትዮጵያዉያን የዓይን ሞራ ቀዶ ጥገና ተደረገ

መሰል ውስብስብ የቀዶ ጥገና ህክምናን አገር ውስጥ ማድረግ መጀመሩንና አቅሙም እየዳበረ መምጣቱን ውጪ አገር ሄደው መታከም ለማይችሉ ዜጎች ትልቅ እድል መሆኑንም ያነሱት የአንጎልና ህብረሰረሰር ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ባለሙያው፤ ለታካሚዋ የተደረገው የቀዶ ጥገና ህክምናው እጅግ ስኬታማ በመሆኑ ታካሚዋ በአራት ቀናት ውስት አገግማ ከሆስፒታል መውጣት መቻሏንም ገልጸዋል፡፡

የህክማና ባለሙያው በመጨረሻም በሰጡት ሙያዊ ምክር “መሰል የህመም ምልክት የታየበት ሰው ቀደም ብሎ ወደ ህክምናው መምጣት ችግሮችን ከማወሳሰብ ስለምታደግ ህክምናው የተወሳሰበና አስቸጋሪ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ቀድሞ መታከም ብቻል ይቀላል” ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ