1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሊቢያ የሚመለሱት አፍሪቃውያን ስደተኞች

ዓርብ፣ ግንቦት 4 2015

ወደ ኢጣሊያ በጀልባ የሚገቡት የስደተኞች ቁጥር በአራት እጥፍ ጨምሯል። አብዛኞቹ ከሰሀራ በስተ ደቡብ የሚገኙ ሃገራት ስደተኞች ተሳክቶላቸው አውሮጳ ቢደርሱ፤ ሌሎች ሜዲትራንያን ላይ ሞተው የሚቀሩ ወይም በሊቢያ በቃኝ ብለው መመለስ የሚፈልጉት ስደተኞች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ነው የዶይቸ ቬለዋ ማርቲና ሺቪኮቭስኪ ዘገባ የሚጠቁመው።

https://p.dw.com/p/4RFjo
ከሊቢያ የሚመለሱት አፍሪቃውያን ስደተኞች
ከሊቢያ የሚመለሱት አፍሪቃውያን ስደተኞችምስል Yousef Murad/AP/picture alliance

ከሊቢያ የሚመለሱት አፍሪቃውያን ስደተኞች

 ሰሞኑን የናይጄሪያዋ ሌጎስ አይሮፕላን ማረፊያ ከሊቢያ በሚመለሱ የናይጄሪያ ስደተኞች ተጨናንቆ ነበር። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ13,000 በላይ ናይጄሪያውያን በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም)  እና በናይጄሪያ መንግሥት ድጋፍ በገዛ ፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።  ከእነዚህ ናይጄሪያውያን አንዷ ሰሞኑን ሀገሯ የገባችው የ 20 ዓመቷ ፌሊሲቲ ናት። ከአስከፊ የስደት ጊዜ በኋላ ወደ ሀገሯ በመመለሷ ደስተኛ እንደሆነች ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።  «ወደ ሀገር ቤት መመለስ ደስ ይላል። ከሀገር የተሻለ ነገር የለም። የነበርንበት ቦታ ሀገራችን አልነበረም። አሁን ወደ ቤታችን ተመልሰናል። ደህንነት ይሰማናል። ማንም በንቀት አይመለከተንም ። በመመለሳችን በጣም ደስተኛ ነን።»
ወጣቷ ፌሊሲቲ እጎአ በ2020 ዓ ም ነበር የኒዠር በርሃን አቋርጣ በአደገኛ ሁኔታ ወደ ሊቢያ የተሰደደችው።  አላማዋ አውሮጳ መግባት ነበር። እንደ በርካታ የሀገሯ ዜጎች ግን ከሊቢያ ፈቅ ማለት አልቻለችም። ወጣቷ አልፎ አልፎ ሊቢያ ውስጥ የቀን ሥራ እየሠራች ወደ አውሮጳ ለመሰደድ ብትሞክርም ጥረቷ ህልም ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ይልቁንስ ፌሊሲቲ ስጋት እና ዘረኝነት ነበር ሊቢያ ላይ የጠበቃት። 
ተመላሽ ናይጄሪያውያኑ  ሀገራቸው ሲደርሱ ለእነሱ በተዘጋጀ ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ተመዝግበው የምግብ፣ የመጠለያ እና የህክምና እርዳታ ያገኛሉ። በሌጎስ ጊዜያዊ ማቆያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ሠራተኛ የሆኑት ቪክቶር ሉተንኮ «ትልቁ ፈተና የስደተኞቹ የስነ ልቦና ሁኔታ ነው» ይላሉ።« ከስደተኞቹ ትልቁ ፈተና አንዱ የስነ-ልቦና እና የአዕምሮ ጤናቸው ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለሆነም የእነዚህን ሰዎች አንዳንድ ቁሳዊ ፍላጎቶች ከማሟላት በተጨማሪ ለአእምሮ ጤንነታቸው ቅድሚያ እንሰጣለን።» 
«ናይጄሪያን ለነሱ ምቹ ለማድረግ በተቻልን አቅም እየሞከርን ነው» የሚሉት የ አይ ኦ ኤም ሠራተኛ ናይጄሪያውያኑ ተመልሰው ዳግም እንዳይሰደዱ የሚደረግላቸው አቀባበል ከእንኳን ደህና መጣችሁ ያለፈ እንደሆነ ይናገራሉ።  ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ቤተሰባቸውን በማፈላለግ ድርጅቶቹ እንደሚረዱም ገልጸዋል። እስካሁን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች አፍሪቃውያን በሊቢያ እስር ቤቶች ይገኛሉ። በሰው አሸጋጋሪዎች ከፍተኛ በደል ይደርስባቸዋል። ይህ ሁሉ ስቃይ እንዳለ እያወቁ የሚሰደዱትም ብዙ ናቸው። 
የጣሊያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስካለፈው ዓርብ ድረስ 41,000 የሚጠጉ የጀልባ ስደተኞች ወደ ጣሊያን ገብተዋል። ይህም ቁጥር ካለፈው ጎርጎሮዮሳዊው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በአራት እጥፍ ጨምሯል። 
የስደተኞች ጉዳይ በጣሊያን እና ፈረንሳይ መካከል ዳግም ክርክር አስነስቷል። የፈረንሳዩ ፖለቲከኛ ስቴፈን ሴዮርነ ረቡዕ ዕለት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒን የስደተኞች አያያዝ አጥብቀው በመተቸት «ኢ ፍትሃዊ እና ኢሰብአዊ አያያዝ» ብለውታል።

ሜድትራንያን ባሕር ላይ በተደጋጋሚ ብዙዎች እየሞቱ ነው
ሜድትራንያን ባሕር ላይ በተደጋጋሚ ብዙዎች እየሞቱ ነውምስል Ärzte ohne Grenzen/dpa/picture alliance

በሜድትራንያን ባሕር ላይ በተደጋጋሚ ብዙዎች እየሞቱ ነው። የቱኒዚያ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ከሁለት ሣምንት በፊት ወደ 210 የሚደርስ የስደተኞች አስከሬን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። አብዛኞቹ ሟቾች ከሰሐራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ዜጎች ነበሩ።

የአፍሪቃውያን ስደት ወደ አውሮጳ እና መካከለኛው ምሥራቅ ብቻ አይደለም። እንደ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መረጃ 21 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪቃውያን በጎርጎሮሲያዊው 2020 በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ይኖሩ ነበር።  70 በመቶ ያህሉ ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ወደ ጎረቤት ሃገራት የተሰደዱ ናቸው። 

እንደቱኒዚያ ባለሥልጣናት ከሀገሪቱ 12 ሚሊየን ዜጋ 21 ሺህው መንግሥት የሚያውቃቸው ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ ሃገራት የመጡ አፍሪቃውያን ናቸው። በተጨማሪም በሕገወጥ ወደ ቱኒዚያ የገቡት ቁጥር ከዚህ እንደሚበልጥ ይገመታል። እነዚህ ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደ አውሮጳ ለመሻገር ያለሙ ናቸው። ቱኒዚያ ውስጥ የስደተኞቹ ቁጥር መበራከት ደግሞ ሀገሬውን ለመበረዝ ያለመ ነው የሚል ስጋትን ማስከተሉን ፖለቲከኞቹ በይፋ እየገለጹ ነው።  
የቱኒዚያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ የታቀደ ስላሉት ነባር ህዝብን መለወጥ የተመከተ መግለጫ በኋላ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ ሃገራት በመጡ አፍሪካውያን ላይ የሚፈፀመው የዘረኝነት ጥቃት ጨመሩን እዚያ የሚኖሩት አፍሪቃውያን ይናገራሉ።  

Tunesien Migranten Protest UNHCR
ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ ሃገራት በመጡ አፍሪካውያን ላይ በቱኒዚያ የሚፈፀመው የዘረኝነት ጥቃት ጨመሩን አፍሪቃውያን ይናገራሉምስል Hasan Mrad/Zumapress/dpa/IMAGESLIVE /picture alliance

ስደት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተመላሽ የሚደረጉ ስደተኞችም ቁጥር ጨምሯል። አልጄሪያ ለምሳሌ ሰዎችን በገፍ ለዓመታት ስትመልስ ቆይታለች።
ከጥር እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ከ10,200 የሚበልጡ ስደተኞች በኒጀር ድንበር አቅራቢያ ተመላሽ ተደርገዋል ሲል በሳህል ዞን ለሚገኙ ስደተኞች የሚሟገተው አላርም ፎር ሳሃራ ዘግቧል። 
የድርጅቱ ዳይሬክተር ሞክታር ዳን ያዬ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት የማጓጓዣዎቹ አይነቶች በሁለት ቡድን ሊከፈሉ ይችላሉ። « «ሕጋዊ» በሚባለው መጓጓዣ ውስጥ በዋነኝነት የኒጀር ዜጎች ይገኛሉ። በኒጀር እና በአልጄሪያ መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት በቀጥታ ወደ ትንሿ ከተማ አሳማካ ይወሰዳሉ ከዚያም በኒጀር ባለሥልጣናት ወደ አርሊት ወይም አጋዴዝ ይወሰዳሉ። በሌላ በኩል «ሕጋዊ ባልሆነው» ደግሞ ከምዕራብ እና ከመካከለኛው አፍሪካ የመጡ ሰዎች ናቸው። ከአረብ ሃገራት ወይም የእስያ ዜጎችንም ይጨምራል። እነሱ በጭነት መኪና በበረሃ ይወሰዱ እና በአልጄሪያ-ኒጀር ድንበር ላይ የማንም መሬት በሚባለው "Point Zero" በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እንዲወርዱ ይደረጋል።»

ለስደተኞች መብት የሚሟገቱት ያዬ  በአውሮጳ ሃገራትም ይሁን በአፍሪቃ ጭምር ስለስደተኞች የሚወራው በዘረኝነት እና በጥላቻ ንግግር የተሞላ ነው፣  ኤ ፒ ስ ለአፍሪካ ሕብረት የስደተኞችን ጥበቃ እንዲያረጋግጥ ያቀረበው አቤቱታም ብዙ ያመጣው ፋይዳ የለም። « ከሰሃራ በስተ ደቡብ ካሉ ሃገራት የመጡ በርካታ ወጣቶች በአሁኑ ሰዓት ቱኒዚያ ውስጥ መውጫ አጥተው ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ወጥመድ ውስጥ የገቡት ብዙ ጊዜ በህዝቡ እና በባለሥልጣናት ስለሚዋከቡ ነው።»
ሲሉም ያዬ ይተቻሉ።  እንደሳቸው ገለፃ አብዛኞቹ ዕድሜያቸው 20 እና 30 ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። አልፎ አልፎም እርጉዝ ሴቶች ፤ ሕጻናት እና ጎልማሶች በመካከላቸው ይገኛሉ። 

ከኒጀር ወደ ሊቢያ የሚሰደዱ
ከኒጀር ወደ ሊቢያ የሚሰደዱምስል Jerome Delay/AP/picture alliance

የአላርም ፎር ሰሃራ አጋር ድርጅት የሆነው ሜዲኮ ኢንተርናሽናል የተባለው የእርዳታ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትም በእነዚህ ስደተኞች ላይ ስለሚደርሰው በደል ቅሬታ ያቀርባል። በሜዲኮ ኢንተርናሽናል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኬረም ሻምበርገር «ሰዎች በጠራራ ፀሐይ ያለ ምግብ፣ ያለ በቂ የመጠጥ ውኃ በበረሃ እየተመለሱ ነው» ሲሉ ለDW ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት 24,000 ሰዎች በአልጄሪያ የጸጥታ ሃይሎች በሌሊት ድንበር አቋርጠው እንዲባረሩ ተደርጓል ብዙዎቹም ቆስለዋል ይላሉ። የሜዲኮ ኢንተርናሽናል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሻምበርገር ይህ የስደት ፖሊሲ ከአውሮጳ ሕብረት ጥቅም ነው።
«ይህን በ 2015 ኒጀር ላይ አስተውለናል። በአውሮጳውያን ግፊት በአንድ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው ውል ወደ ሰሜን የሚደረግ ስደትን እንደ ወንጀል ይታያል።  በዚህ ምክንያት ሹፌሮች እንደ ሰው አዟዟሪ፤ ምግብ ሻጮች ወይም ቤት አከራዮችን እንደ ሕገወጥ ስደት ተባባሪዎች እንዲታዩ ያደርጋል»
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅትንም ቢሆን ሻምበርገር አጥብቀው ይተቻሉ።  እንደሳቸው ከሆነ አይ ኦ ኤም «በፈቃደኝነት የሚመለሱ ስደተኞች» በሚል «የድንበር ማስተዳደር» ሥራ እየሠራ ይገኛል። እውነታው ግን ስደተኞች መውጫ መንገድ እንዳይኖራቸው ተደርገው ነው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት» ባይ ናቸው።
በውዴታ ወደ ሀገሯ እንደተመለሰች የምትናገረው ናይጄሪያዊቷ ፌሊሲቲ በበኩሏ ወደፊት ትምህርት ቤት ተመልሳ የመግባት እቅድ እንዳላት ነግራናለች። ጓደኞቿን እና ቤተሰቦቿን ለማግኘትም ቸኩላለች። «በርካታ የቤተሰቤ አባላት ጋር ስልክ ደውያለሁ። ድምፄን በመስማታቸው ደስተኞች ናቸው። እኔም ደስተኛ ነኝ። በተለይ የአባቴን ድምፅ በመስማቴ ተደስቻለሁ።»
እንደዚያም ሆኖ ወደ ናይጄሪያ መመለስ ለፌሊሲቲ ቀላል አልነበረም። እንደ እሷ ያሉ በርካታ ናይጄሪያውያን ሊቢያ መቆየቱን መርጠዋል። ይህም እቅዳቸው ሳይሳካ ወደ ሀገራቸው መመለሱ ስላሳፈራቸውም ወይም ስሜታቸው በመነካቱ ነው። ሌሎች ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ደውለው ስላሉበት ሁኔታ መንገር እንኳን ስለማይደፍሩ ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም። 

ማርቲና  ሺቪኮቭስኪ /ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ