1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሊቢያ ወደ ሩዋንዳ የተወሰዱ ተሰዳጆች

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 15 2012

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በሊቢያ የነበሩ አፍሪቃውያን ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ማሻገር ጀምሯል። በሩዋንዳዋ ጋሾራ ከተማ በሚገኘው ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያ ከ100 በላይ ተሰዳጆች ይገኛሉ። ሁሉም ወደ አውሮጳ የመሻገር ምኞት ነው ያላቸው። የዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ኬንያዊቱ የIT ባለሙያ እና የሴቶች መብት ተሟጋች አሸንፋለች። 

https://p.dw.com/p/3RxtU
Erste Flüchtlinge aus libyschen Lagern in Ruanda angekommen
ምስል AFP/C. Ndegeya

«ስደተኖች በሩዋንዳ፤ ኬንያዊቱ የጀርመን አፍሪቃ ተሸላሚ»

ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚመኙ 189 ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የመጡ ተሰዳጆች በሩዋንዳዋ ጋሾራ ከተማ በሚገኘው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባዘጋጀው መጠያ ውስጥ ይገኛሉ። ወጣት ወንዶች እና ሴቶች፣ ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች፣ ብቻቸውን የሆኑ ልጆች እንዲሁም ቤተሰቦች በተሰባሰቡት በዚህ መሸጋገሪያ ስፍራ ነው በተባለው ማዕከል ግቢ ውስጥ ገሚሱ መረብ ኳስ ሲጫወቱ ቀሪዎቹ በየፊናቸው በተለያዩ ተግባራት ተጠምደዋል። አብዛኞቹ በአስቸጋሪው የስደት ጉዟው በሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች አሰቃቂ በደሎች እንደተፈጸሙባቸው ይናገራሉ። ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ የተነሱት እነዚህ ተሰዳጆች ሜዲትራኒያን ባሕርን አቋርጠው አውሮጳ ለመግባት ቢመኙም ሊቢያን ማለፍ አልቻሉም። ባለፈው መስከረም ወር UNHCR የስደት ጉዳያቸውን አጣርቶ እና አስተካክሎ ወደሦስተኛ ሀገር እስኪወስዳቸው ድረስ ለጊዜው እዚያ እንዲቀመጡ ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ነው ወደዚህ የመጡት። ሩዋንዳ ውስጥ የተደረገላቸው አቀባበልም ሆነ የሚገኙበት ሁኔታ መልካም ቢሆንም ከዳርፉር አካባቢ የተሰደደው ሱዳናዊው አብዱላ ሮድዋን የተሻለ ኑሮ ለመኖር ከአፍሪቃ ውጭ መሄድን እንደሚመርጥ ይናገራል።

« ከዚህ መውጣት አለብን፤  ወደአውሮጳ ነው መሄድ የምንፈልገው፤ ምክንያቱም ሁላችንም ያ ነው ግባችን። አሁን ከነበርነት የመውጣት እና ወደ ሩዋንዳ የመምጣት ዕድል አግኝተናል ። ለዚያ እናመሰግናለን። ሆኖም ሁላችንም አሁን ወደሌላ ሀገር ለመሄድ እየተጠባበቅን ነው። ወደ ተሻለ ቦታ ወደ አውሮጳ፣ አሜሪካ ወይም ካናዳ ወይም ወደ ሆነው ቦታ እንድንሻገር እንፈልጋለን። በቃ የምንፈልገው መሄድ ነው። አንዳንዶች አፍሪቃ ስለመኖር ዕድል ሲናገሩ እሰማለሁ፤ ሆኖም ግን አፍሪቃ ዛሬ ሰላም ቢሆን ነገር በቀላሉ መጥፎ ነገር እንደሚከሰት እናውቃለን። የሚሆነው አይታወቅም፤ ለዚህ ነው በሌሎች ሃገራት የተሻለ ሕይወት ለመኖር የምንፈልገው።»

የ18 ዓመቱ አብዱላ ጦርነት ካወደማት ዳርፉት ከተሰደደ 3 ዓመት ሆኖታል። አብረውት 300 ተሰዳጆች ነበር። ሆኖም አብዛኞች ዛሬ በሕይወት የሉም፤ በረሃ ላይ ረግፈዋል። በሩዋንዳው ጊዜያዊ የስደተኞች  መጠለያ ማዕከል የሚገኙት ሁሉ ወደ ሌላ ሀገር የመሻገር ፍላጎት እንዳላቸውም በአፅንኦት ያስረዳል። ኢትዮጵያዊው ገብረመስቀል አያልነህም ይህን ይጋራዋል።

«በእርግጥ እዚህ ስላሳረፉን በጣም እናመሰግናለን። አየሩም ልክ የኢትዮጵያን አየር ነው የሚመስለው። ለዚህ ከልብ ልናመሰግን ይገባናል፤ ግን እዚህ ልንኖር እና ሕይወታችን ሊስተካከል አይችልም።»

Erste Flüchtlinge aus libyschen Lagern in Ruanda angekommen
ከሊቢያ ወደሩዋንዳ የመጡት ስደተኞች አቀባበልምስል AFP/C. Ndegeya

ነው የሚለው። ሊቢያ ውስጥ ከነበሩትበት አስከፊ እስር ቤቶች መውጣት የቻሉት እነዚህ ተሰዳጆች ሩዋንዳ ውስጥ ላገኙት እፎይታም ሆነ ክብካቤ አመስጋኞች መሆናቸውን ቢገልፁም የጉዟቸው ግብ ገና እንዳልደረሰ ነው የሚያስረዱት። በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ሁኔታቸውን ለመናገር ያልፈለጉት ኢትዮጵያውያን ሴት ተሰዳጆች በበኩላቸው በሊቢያ እስር ቤት የደረሰባቸውን በለቅሶ ስሜታቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል።

የUNHCR አስተርጓሚ እንደገለፁት የደረሰባቸው ስቃት ሰቀቀን ላይ የጣላቸው እነዚህ ወገኖች ከሊቢያው መከራ ወጥተው ሩዋንዳ መግባታቸው ጊዜያዊ እፎይታ ቢፈጥርላቸውም እዚያ መኖር ግን አይፈልጉም። በሩዋንዳ የUNHCR ቃል አቀባይ የሆኑት ኤሊሴ ቪለቸለን ለረዥም ጊዜያት ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ተቋርጦ የነበረው ስደተኞች ከወዳጅ ዘመድ ሊገናኙበት የሚያስችላቸውን መስመር ለማመቻቸት እየሠሩ እንደሆነ ይናገራሉ።

«እዚህ ግቢ ውስጥ ቴሌቪዥን የሚመለከቱት በክፍል አለ፤ ዜናም መከታተል ይችላሉ። በቅርቡ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በኢንተርኔት መስመር መገናኘት እንዲችሉ ኮምፕዩተር እንዲያገኙ እናደርጋለን። የመገናኛ ዕድሉ መመቻቸቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመነጋገር እንዲችሉም ሆነ ለመማር እና በሌላው ዓለም ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳቸዋል። ምክንያቱም ከማኅበራዊ ግንኙነት ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ነበር።»

ከአስከፊዎቹ የሊቢያ እስር ቤቶች ወጥተው ወደ ሩዋንዳ የመወሰድ ዕድል ካገኙት ከእነዚህ በተጨማሪ በቅርቡ 120 የሚሆኑት ደግሞ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንዲያም ሆኖ ገና 3 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች እንደሚገኙ የUNHCR ባልደረባዋ ተናግረዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ወደ አውሮጳ ለመግባት  ለመግባት የተመኙ አፍሪቃውያን ተሰዳጆች ገሚሱ በበረሀ፣ ገሚሱ በሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች እጅ ሕይወታቸው ሲቀጠፍ ገሚሱን ደግሞ ባሕር እንደዋዛ ውጧቸዋል።  በሕይወት የተረፉት ከሚሰቃዩባቸው የሊቢያ እስር ቤቶች ወጥተው ፅዱ  እና ለም ወደሆነችው ሩዋንዳ ቢገቡም ብዙ ሺህ ዶላር ለሕገወጥ አሸጋጋሪዎች የከፈሉትን እያሰሉ ጉዟ ገና እንዳላበቃ እየተናገሩ ነው። በጎርጎሪዮሳዊው 1994 ዓ ም የዘር ማጥፋት እልቂት ሲፈፀምባት 2 ሚሊየን ዜጎቿ ወደለያዩ ሃገራት የተሰደዱባት ሩዋንዳ ዛሬ ለተሰዳጆች መጠለያ ለመሆን በቅታለች።

Verleihung Deutscher Afrika-Preis 2019
መራጊተ መንግሥት አንጌላ ሜርል ሽልማቱን ለጁሊያና ሮች ሲሰጡምስል Deutsche Afrika-Stiftung/S. Wasserhäuptl

ከሰሞኑ ነው ኬንያዊቷ ጁሊያና ሮች የጎርጎሪዮሳዊው 2019ን የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት የተቀበለችው። ለሽልማት የበቃችው ለሴቶች መብት የምትሟገተው  የIT ባለሙያ ራሷ ያቋቋመችው ዑሻሂዲ የተሰኘ የመረጃ መለዋወጫ መረብም ሥራ አስኪያጅ ናት። ዋና አገልግሎቱ ደግሞ በቀውስ አካባቢ የሚገኙ ኬንያውያን መረጃ እንዲለዋወጡ ማስቻሉ ነው። የ42 ዓመቷ ሮች ሽልማቱን  ስትቀበል መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባደረጉት ንግግር የIT ባለሙያዋ ኬንያዊት ለአፍሪቃውያን ሴቶች የምትፈጥረው መነቃቃት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

«የሚስስ ሮች ስኬት ለአፍሪቃውያን ሴቶች መነቃቃትን እና ከምንም በላይ አርአያነትን ይፈጥራል። አንድ ሰው ግሩም ሃሳብ እና ቁርጠኝነት ካለው በኤኮኖሚው፤ በማኅበረሰቡ ብቻ ሳይሆን ድንበር አልፎ  እንዴት እና ምን ምን ያህል መንቀሳቀስ እንደሚችል አሳይታለች። እንደሷ ያሉ አዳዲስ ነገሮች የሚያፈልቁ እና ሌሎች ላይም ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ሰዎችን እንፈልጋለን።»

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና ኬንያዊቱ ጁሊያና ሮች ለሁለተኛ ጊዜ መገናኘታቸው ነው። ከዚህ ቀደም ጀርመን የቡድን 20 ሃገራት ፕሬዝደንት በነበረችበት በጎርጎሪዮሳዊው 2017 በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ሜርክል ንቁዋን ኬንያዊት አይተዋታል። አሁን ደግሞ ሲሸልሟት፤ እናም አጋጣሚው ደስታ እንደፈጠረላቸውን አልሸሸጉም። ሮች ዑሻሂዲ የተሰኘውን ኩባንያዋን ስትከፍት ሀገሯ ኬንያ ጨለማ የተባለው ታሪኳ ላይ ነበረች። በጎርጎሪዮሳዊው 2007 ዓ ም ከተካሄደው አወዛጋቢ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ1300 የሚበልጡ ሰዎች ሞተዋል። በቀውስ አካባቢዎች ሰዎች መረጃዎችን እንዲልኩ እና እንዲያጋሩ የሚረዳው ዑሻይዲ በወቅቱ ስለአመፁ መረጃዎችን ማሰራጨት ችሏል። ጁኒያና ሮች ያቀረበችውን አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ ተግባራትን እየተከታተሉ መረጃ ለማጋራት የሚያስችል ነው።  በአሁኑ ጊዜ ከ160 ሃገራት በላይ የዚህ ቴክኒዎሎጂ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ጦርነት ባደቀቃት ሶርያ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ በጎዳቸው ኔፓል እና ሃይቲ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ወቅት የጥላቻ ንግግር ተከታትለው በመሰነዱ በኩል ትልቅ አገልግሎት ሰጥቷል። ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለች የሚነገርላት ኬንያዊቱ የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት የዘንድሮ አሸናፊ ግን የሚፈጠረው የሥራ ዕልድ ቁጥሩ የበረከተውን የአፍሪቃ ወጣት ሙሉ ለሙሉ ገና ማስተናገድ አለመቻሉን ትናገራለች።

Talk: The future of the digital economy
ምስል DW/F. Görner

«ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት አፍሪቃ፤ በተለይ ደግሞ ኬንያ ቁጥሩ የሚበዛው ወጣት ወደ ሥራው ዓለም እየገባ ነው። እናም እኛ የምንፈጥራቸው ኩባንያዎች እና፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል በቂ አይደለም ማለት ይቻላል። ማመጣጠን አልቻልንም።»

ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ ም በርሊን ላይ ተገኝታ ሽልማቷን በተቀበለችበት ዕለት ዲጂታል ኤኮኖሚ አይኖርም ተብሎ በሚገመትባት አፍሪቃ ይህ መገኘቱ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ ያመለከተችው ጁሊያና ሮች፣ ሽልማቱ ለእሷ ብቻ ሳይሆን መሸለሟን ለሚሰሙ እና ፎቶውንም ለሞመለከቱ ወጣት አፍሪቃውያን ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጻለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ