ኦሎምፒክ የህዝብ ጨዋታ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 21 2004ነገ የሚጀመረው የለንደኑ የ2012 የኦሎምፒክ ውድድር የልሂቃን ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው የሚደሰትብት ጨዋታ መሆኑን የብሪታኒያ ባለሥልጣናት አበክረው ያስገነዝባሉ ። በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ እንኳን የብሪታኒያን ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስብጥር ለማንፀባረቅ ተማሪዎች ነርሶችና ሌሎች ተራ ዜጎች ሁሉ እንዲሳተፉ ይደረጋል ። ይሁንና በሌላ በኩል ጨዋታዎቹን በስፍራው ተገኝቶ ለመከታተል የሚያስችል ቲኬት ማግኘት ግን እንዲህ ቀላል ሆኖ አልተገኘም ። ከዚህ ሌላ የለንደን ነዋሪዎች በጨዋታው ወቅት በከተማዋ እንደ ልብ መዘዋወር አዳጋች ሊሆንባቸውም ይችላል ። የዶቼቬለ የለንደን ወኪል ኒና ማርያ ፖትስ ያቀረበችውን ዘገባ ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
የለንደኑን ኦሎምፒክ በስፍራው ተገኝተው ለማየት ቲኬት የማግኘት ችግር ገጥሞዎት ከሆነ ይህ የርስዎ ችግር ብቻ አይደለም ትላለች ኒና ማርያ ። ከአጠቃላዩ 8.8 ሚሊዮን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የመግቢያ ቲኬቶች 7 ሚሊዮኑ ካለፈው አመት አንስቶ እስካለፈው ሰኔ ድረስ በኢንተርኔት በተካሄደ ጨረታ ተሸጠው አልቀዋል ። የዋና ዋናዎቹ ማራኪ ውድድሮች የመግቢያ ቲኬቶችም ከአሁኑ በውድ ዋጋ በጥቁር ገበያ ቀርበዋል ። በሌላ በኩል ደግሞ ከብዙዎች አቅም ባላይ የሆነ ዋጋ ያላቸው በርካታ ቲኬቶችም ይገኛሉ ። ከቲኬቶች ሽያጭ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የተለያዩ ወቀሳዎችን የኦሎምፒክ አትሌቲክስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ጆናታን ኤድዋርድስ ያስተባብላሉ ።
« ከቲኬቶች ጋር የተያያዘው ጉዳይ ቀላል ነው ። ለሽያጭ ከቀረበው ቲኬት በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ናቸው ቲኬት የሚፈልጉት ። ይህ ለኛ ለአዘጋጁ ኮሚቴ እፁብ ድንቅ ዜና ነው ። ምክንያቱም 25 በመቶ ገቢያችንን የምናገኘው ከቲኬት ሽያጭ ነው ። ለአለም ዓቀፉ አዘጋጅ ኮሚቴና ለአለም አትሌቶች ቃል ከገባናቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በህዝብ በተሞላ ስታድዮም ውድድሮቹን እንደሚያካሂዱ ነው ። የሚያገኙትም ይህንኑ ነው ። ይህ ደግሞ በእውነት ለአትሌቶቹም አስፈላጊ ነው ። »
ከዚህ ሌላ ኤድዋርድስ እንደሚሉት ከውድድሮቹ በተጨማሪ የሚካሄዱ ሌሎች የባህል መርሃ ግብሮችም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚችል ህዝብን ይበልጥ የሚያሳትፉ ዝግጅቶች ናቸው ። ይሁንና ሁሉም ነዋሪዎች ተመሳሳይ ስሜት የላቸውም ። ለምሳሌ በኦሎምፒክ ፓርክ አቅርቢያ በሚገኘው በኒውሃማ የሚገኙ ነዋሪዎች ከተጠቀሱት ዝግጅቶች አንዱም የሚያመጣላቸው ጥቅም ያለ አይመስላቸውም ። የኦሎምፒክ ባለሥልጣናት ግን በተራ ዜጎች በተዘጋጁ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉም መካፈል ይችላል ባይ ናቸው ። ጆን አርሚት ከባለሥልጣናቱ አንዱ ናቸው ።
« በለንደን የተለያዩ አካባቢዎች በግሪንዊች መናፈሻ በማዕከላዊ ለንደን በ whitewall በ Horse Guards parade ና በ Hyde መናፈሻ እጅግ ብዙ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ ። በ Stratford ብቻ ሳይሆን ለንደን ውስጥ በሌሎችም ስፍራዎች እንቅስቃሲዎች የሚካሄዱባቸው ቦታዎች አሉ ። ይህ ህዝብን እጅግ የሚያቀራርብ መናፈሻ ነው ። ሰዉ የግድ ቲኬት መግዛት አይኖርበትም ። ስታድዮምም መገኘት የለበትም ። ወንዙን እና የመልከዓ ምድሩን አቀማመጥ እያደነቀ በትላልቅ ቴሌቪዥኖች ጨዋታዎቹን እየተከታተለ በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄዱትንም ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ማየት ይችላል ። ሰዉ ሊዝናናባቸው የሚችል በርካታ እንቅስቃሲዎች ይኖራሉ »
ያም ሆኖ ውድድሩ በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅር መሰኘታቸው አልቀረም ። አንዳንድ የለንደን መንገዶች በከፊል ለትላልቅ እንግዶችና ለኦሎምፒክ ባለሥልጣናት ተለይተው መያዛቸው የለንደን የታክሲ ሾፌሮችን አበሳጭቷል ። እርምጃው ገበያችን ያዳክማል ነው የሚሉት ። የለንደን ታክሲ ሾፌሮች ማህበር ቃል አቀባይ ስቲቭ ማክናማራ
«ኦሎምፒክ በጣም ተፅዕኖ ያሳድርብናል ። የሚዘጋው የመንገድ ክፍል ስፋት እኛን በጣም ከሚያሳስቡን ጉዳዮች አንዱ ነው ። አብዛኛዎቹ የለንደን ዋና ዋናዎቹ መንገዶች በከፊል ይታገዳሉ ። እንደሚመስለኝ 38 ማይል ይሆናሉ ። እነዚህን መንገዶች መጠቀም አንችልም ። በዚህ ተበሳጭተናል ። »
ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ የለንደን ነዋሪዎች ቲኬት ኖራቸውም አልኖራቸው የውድድሮቹን ውጤቶች በትጋት ይከታተላሉ የኦሎምፒክ መንፈስም ያድርባቸዋል የሚል ተስፋ አለ ። ዘንድሮ የኦሎምፒክ ውድድር ቲኬት ከሌላቸውና በዚህም ውድድር እለታዊ ኑሮአቸው ከሚታወከው ሌላ ውድድሩ የሚስበው ምን ያህሉ እንደሆነ በተጨማሪ የሚነሳ ጥያቄ ነው ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ