እርዳው ነጋሽ ሚኮ «መንጅክሶ ጸዴ» እስከ ጀርመንዋ ኮሎኝ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 1 2015በሙያቸው መካኒካል መሐንዲስ ቢሆኑም በዚህ ማዕረግ መጠራት አይፈልጉም። ከዚያ ይልቅ ለወጡበት ማኅበረሰብ ባደረጉት መልካም ሥራ ቢነሱ ይመርጣሉ። የምዕራብ ጀርመንዋ የኮሎኝ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በጎ አድራጊው በዚሁ ከተማ በሚገኘው ፎርድ በተባለው ታዋቂ የአሜሪካን የመኪና ኩባንያ ለ30 ዓመታት አገልግለዋል። ኮሎኝ ከሚገኙ ወዳጆቻቸው ጋር ከጥቂት ዓመታት በፊት በመሰረቱት ማኅበር አማካይነት ደግሞ፣ በትውልድ መንደራቸው «መንጅክሶ ፀዴ» እና 18 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው «ጨፌ ዶንሳ» ከተማ ትምህርት ቤቶችን አስገንብተዋል፤ ለተማሪዎችም የደንብ ልብስን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመለገስ ለአስተማሪዎችም በትምህርት ቤት አቅራቢያ መኖሪያ ቤት በመስራት ትልቁን ምኞታቸውን ማሳካት ችለዋል። እርዳው ነጋሽ ሚኮ ይባላሉ። የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ከትውልድ መንደራቸው በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ጨፌዶንሳ በተባለችው የገጠር ከተማ ነው የተማሩት። ጨፌዶንሳ በሰንዳፋና በደብረ ዘይት መካከል የሚገኝ ከተማ ነው። አቶ እርዳው እስከ ስምንተኛ ክፍል ጨፌዶንሳ ሲማሩ 18 ኪሎሜትር መጓዝ ነበረባቸው። ስምንተኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ወላጆቻቸው ትምሕርቱ ይብቃህ ሲሏቸው ፣ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ ።አዲስ አበባ ግን የሚያስጠጋቸው አልነበረም።
እድል ቀንቷቸው ምሥራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ገቡ። አነስተኛ ስራ መኖሪያም አገኙ። ምሥራቅ አጠቃላይ እስከ አስረኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ጥሩ ውጤት አምጥተው ተግባረ እድ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ትምሕርት ቤት ገቡ።ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቃቸው የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው የዛሬ 41 ዓመት ጀርመን መጡ።
ላይፕሲሽ በተባለችው የምሥራቅ ጀርመን ከተማ መካኒካል ምህንድስና ተማሩ በዚሁ የትምሕርት ዘርፍ ከፍተኛ ትምሕርታቸውን መቀጠል ቢፈልጉም ሳይሳካላቸው ቀረና ወደ ምሥራቅ በርሊን ከዚያም አሁን ወደ ሚኖሩባት ኮሎኝ ከተማ ገቡ። በዚያም ጀርመንና አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀው ፤የጀርመኑ ሲዘገይ የአሜሪካኑ ተሳክቶ ዳላስ ቴክሳስ ሄዱ።ዳላስ እየተማሩ እየሰሩም ሳለ የደረሳቸው አንድ ደብዳቤ ሃሳባቸውን አስቀየረ።
የልጆቻቸው እናትም ከጀርመን ዳላስ ተክትለዋቸው መጡ።ሆኖም እዚያ መቆየት ስላልፈለጉ ጀርመን መመለሳቸው ግድ ሆነ። ከተመለሱ በኋላም በቴክኒክ ሞያ ሰልጥነው ፎርድ ኩባንያ መስራት ጀመሩ።ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ለ30 ዓመታት አገልግለዋል።አቶ እርዳው እንደሚሉት ሁለት ፕሮጀክቶች ነበሯቸው የመጀመሪያው ፕሮጀክታቸው ለቤተሰባቸው ያዘጋጁት ፕሮጀክት ነበር።ዘመዶቻቸው ከሀገራቸው እንዳይሰደዱ ባያሉበት ራሳቸውን የማስቻል ፕሮጀክት ነበር። ይህን ያደረግኩበት ምክንያት አለኝ ይላሉ።
አንደኛው ፕሮጀክት ካለቀ በኋላ ደግሞ የወጡበትን ማኅበረሰብ ወደ ሚረዱት ወደ ሁለተኛው ፕሮጀክት ፊታቸውን አዞሩ። ከፍጻሜ ያደረሱት ይህ ፕሮጀክት እጅግ የረኩበት መሆኑን ይናገራሉ።በትውልድ አካባቢያቸው ባካሄዱት በዚህ ፕሮጀክት ተማሪዎች መምህራንና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆኗል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ