1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራዉያን ተገን ጠያቂዎችና የሱዳን ስደተኞች በሊቢያ

ቅዳሜ፣ መስከረም 17 2012

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ባስጠለለችዉ ጀርመን በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን ስደተኞች ይገኛሉ። ከቅርብ ጌዜ ወዲህ ግን የኤርትራዉያን  የተገን ጥያቄ «የኢኮኖሚ ነዉ» በሚል እያወዛገበ ነዉ። ምክንያቱ ደግሞ  በቅርቡ  የኤርትራ መንግስት በኖሮዌ ኦስሎ ባዘጋጀዉ አንድ ዝግጅት ላይ ኤርትራዉያን ሲታደሙ መታየታቸዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3QNpj
Äthiopien/Eriträea - Veränderungen nach Grenzöffnung
ምስል DW/J. Jeffreys

የኤርትራዉያን  የተገን ጥያቄ እያወዛገበ ነዉ።



በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ባስጠለለችዉ ጀርመን በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን ስደተኞች ይገኛሉ። ከቅርብ ጌዜ ወዲህ ግን የኤርትራዉያን  የተገን ጥያቄ «የኢኮኖሚ ነዉ» በሚል እያወዛገበ ነዉ። ምክንያቱ ደግሞ  በቅርቡ  የኤርትራ መንግስት በኖሮዌ ኦስሎ ባዘጋጀዉ አንድ ዝግጅት ላይ ኤርትራዉያን ሲታደሙ መታየታቸዉ ነዉ።  የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ከተገን ጠያቂዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ አካላት ግን በጉዳዩ ላይ ተገቢዉ ማጣራት ሳይደረግ የተገን ጠያቂዎቹን ችግር «የኢኮኖሚ ነዉ» የሚል ድምዳሜ ከመስጠት መቆጠብ ያስፈልጋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ከነዚህም መካከል አቶ ተከስተ አዎት አንዱ ናቸዉ።
አቶ ተከሰተ አወት በልጅነት ዕድሜያቸዉ ነበር ከሀገራቸዉ  ኤርትራ  የተሰደዱት። ጀርመን ዉስጥ  ቩፐርታል በተባለ ከተማ  የሚኖሩት አቶ ተከሰተ ከዛሬ 34 ዓመት በፊት ነበር በወቅቱ ይካሄድ የነበረዉን የርስ በርስ  ጦርነት ሽሽት ከቤተሰቸው ጋር በሱዳን በኩል ወደ ጀርመን የመጡት። አቶ ተከሰተ የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛ ሲሆኑ ከስቸራዉ ጎን ለጎን በፌደራሉ የስደትና የስደተኞች ሚንስቴር ለተገን ጠያቂ ኤርትራዉያን  አስተርጓሚ ሆነው  ይሰራሉ። እናም ያሳለፉት የስደት ህይወት አሁንም አብሯቸው ነዉ። በአስተርጓሚነት ስራቸዉ  በርካታ የሀገራቸው ልጆች  ከሀገር ለመዉጣት ያጋጠማቸዉን ችግር በየቀኑ ሲተርኩና ሲመሰክሩ ይዉላሉ። በጀርመን በየዓመቱ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ተገን ይጠይቃሉ። ምክንያታቸዉ ደግሞ «የሀገሪቱን አምባገነናዊ ስርዓት በመፍራትና ተስፋ በመቁረጥ ነዉ»ይላሉ አቶ ተከስተ። 
« በአሁኑ ስዓት ሰዎች ወደዚህ የሚሰደዱበት ምክንያት በኤርትራ ለዓመታት ከተደረገዉ የነፃነት ትግል በኋላ አምባገነናዊ አገዛዝ በመፈጠሩ  ይህንን ተከትሎም ወጣቶች ለማያቋርጥ የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት በመዳረጋቸዉና  በሀገሪቱ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመኖሩ  ኤርትራ ዉስጥ ተስፋ ስለማይታያቸዉ ነዉ።»
እናም ለአቶ ተከስተ ከኤርትራ የመጡ ተገን ጠያቂዎች  የኢኮኖሚ ስደተኞች አይደሉም። ለዚህም ሰዎች በአስቸጋሪዉ የስደት ጉዞ የሚያጋጥማቸዉን እንግልትና ሞት  በተለይም ስደተኞች ለመሻጋገሪያነት በሚጠቀሟት  ሊቢያ ያለዉን አሳዛኝ የሰብአዊ  ሁኔታ ይጠቅሳሉ። በኢኮኖሚ ችግር  ማንም ይህን መከራ አይቀበልም ሲሉም ይከራከራሉ። 
ምንም እንኳን የኤርትራው  ፕሬዝዳንት  ኢሳያስ  አፈወርቂ  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ከኢትዮጵያ ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ቢሆንም፤ እንደ አቶ ተከስተ ለአብዛኛዎቹ  ኤርትራውያን  በተለይም ለወጣቶች ሁኔታዉ ብዙም አልተለወጠም። የዶቼቬሌዋ ማርቲና ሽዋኮቭስኪ ያነጋገረቻቸዉ ሂዉማን ራይትስ ወች የተባለዉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሊቲሽያ ባደርም የአቶ ተከስተን ሀሳብ ያጠናክራሉ።
«ኤርትራ  አሁንም ቢሆን በዓለም ላይ ከፍተኛ ጭቆና ካለባቸዉ  ሀገሮች አንዷ ነች። በሀምሌ ወር 2018 የተደረገዉን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ኤርትራ ዉስጥ ያለዉ የከፋ  በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ መሻሻል ይመጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ይህ የለዉጥ ተስፋ እዉን አልሆነም። ከነዚህ ዉስጥ አንዳቸዉም አልተፈፀሙም። የፖለቲካ  ተችዎች፣ ጋዜጠኞችና እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ቡድን አባላት ቤተሰቦቻቸዉ ሊጎበኛቸዉ በማይችሉበት ሁኔታ በአሰቃቂ ሁኔታ በየማጎሪያዉ ታስረዉ ይገኛሉ» ብለዋል።
ባደር የግዳጅ ብሄራዊ ዉትድርናም ለኤርትራ ወጣቶች ሌላዉ የስደት ምክንያት ነዉ ይላሉ።
« አገዛዙ ኅብረተሰቡን የሚቆጣጠረዉ ሐሳብ የመግለፅ ነፃነትና የሃይማኖት ነፃነትን በመገደብና በመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን አብዛኛዉን የኅብረተሰብ ክፍል ለብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎት በማስገደድ ጭምር ነዉ» ብለዋል።
ያም ሆኖ ግን በቅርቡ  የኤርትራ መንግስት በኖሮዌ ኦስሎ  የብሄራዊ ዉትድርናን 25ኛ ዓመት ለማክበር ባዘጋጀዉ አንድ ዝግጅት ላይ ኤርትራዉያን ሲታደሙ መታየታቸዉ  የሀገሪቱን ተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ሌላ መልክ እንዲይዝ አድርጎታል። ኤርትራዉያኑን ለስደት እየዳረገ ነዉ ተብሎ በሚታመነዉ የግዳጅ ብሄራዊ ዉትድርናን  ለመዘከር በመንግስት ተወካዮች በተዘጋጀ በዓል ላይ መገታቸዉ  የኖሮዌ መንግስት ተቀባይነት ሊያገኙ የነበሩ 150  የተገን ፋይሎችን እንደገና ለመመርመር መዘጋጀቱ እየተነገረ ነዉ።
ተመራማሪዋ ሊቲሺያ ባደር ግን ጉዳዩ ኤርትራ ዉስጥ ያለዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት መሸፈኛ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ኤርትራዉያን በዉጭ ሀገር ሆነዉም በቤተሰቦቻችን ላይ አደጋ ይደርሳል በሚል መንግስታቸዉን እንደሚፈሩት የሚያሳይ ነዉ በሚል ይከራከራሉ። አቶ ተከስተ በበኩላቸዉ በሚኖሩበት ጀርመን ሀገርም አገዛዙን የሚፈሩ ኤርትራዉያን መኖራቸዉን ይገልፃሉ። በኖሮዌ የተከሰተዉ ሁኔታ በጀርመን ለሚገኙ ተገን ጠያቂዎች ተፅዕኖ ይኖረዉ ይሆን በሚል ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ «ኮኔክሽን» ከተባለዉ የሰብአዊ መብት ጠበቃ ድርጅት ሩዲ ፍሬዲሪሽ ደግሞ ሌላ ምክንያት ያቀርባሉ። ፍሬዲሪሽ እንደሚሉት በጀርመን ያለዉ የኤርትራ ስደተኞች አቀባበልም የፖለቲካ  ሳይሆን ሰብአዊ ከለላ የመስጠት በመሆኑ ስደተኞቹ ከሀገራቸዉ ቆንስላ ጽ/ቤት ፓስፖርት እንዲያመጡ ይጠየቃሉ። ያ በመሆኑም ኤርትራዉያኑ ከመንግስት ጋር ሳይወዱ በግድ ግንኙነት እንዲፈጥሩና ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚገደዱበት ሁኔታ አለ ይላሉ።
«የኤርትራ ቆንስላ ሰራተኞች «ሁሉንም ነገር አምኜና ተቀብዬ ሁለት በመቶ  ለመክፈል ዝግጁ ነኝ»  በሚል ሰነድ  ላይ በማስፈረም ስደተኞቹ ተጨማሪ የኅሊና ፀፀት እንዲያድርባቸዉ ያደርጋሉ» በማለት የተገን ጠያቂዎቹ ችግር መልከ ብዙ መሆኑን አስረድተዋል። ሁለት በመቶው ግብር የኤርትራ መንግስት ውጭ ሃገራት ከሚኖሩ ኤርትራውያን እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነው።
አሁን ባለዉ መረጃ መሰረት ኤርትራ በርካታ ስደተኞች ከሚመጡባቸዉ አሥር ሃገራት ዘጠነኛ ላይ ስትገኝ፤  የኤርትራውያን የተገን ጥያቄም ከ72 በመቶ በላይ ተቀባይነት ሲያገኝ ቆይቷል።  የፌደራሉ የስደተኞች ጉዳይ ለዶቼ ቬለ በቅርቡ በላከዉ መግለጫ  የስደተኞች የተገን  ጥያቄ ተገቢዉ ማጣራት ተደርጎበትና ተአማኒነቱ ተመርምሮ መወሰን  እንዳለበት አስታዉቋል። 

Eritrea Flüchtlingslager in der Region Tigrai Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri
Äthiopien/Eriträea - Veränderungen nach Grenzöffnung
ምስል DW/J. Jeffrey

 

የሱዳን ስደተኞች በሊቢያ


አፍሪቃዉያን ስደተኞች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አዉሮፓ ለመሻገር  ሊቢያን እንደመሸጋገሪያ ይጠቀማሉ።ያም ሆኖ በሊቢያ የሚያጋጥማቸዉ ሞትና እንግልት ቀላል አይደለም። የሱሌማን ህይወት ለዚህ ማሳያ ነዉ።ሱዳናዊዉ ሱሌማን ወደ አዉሮፓ ለመሻገር ብዙ ሺህ ኪሎሜትሮችን  ተጎዞ ነዉ ሊቢያ የደረሰ ዉ።በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰዉ በሊቢያ የሰነቀዉን ተስፋ እዉን ማድረግ እንደማይችል የተገነዘበዉ ግን በቅርቡ ነዉ።ሱሌማን  በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ በርካታ ስደተኞች ባሉበት አንድ መጠለያ ጣቢያ ከባሌቤቱና ከሰባት ልጆቹ ጋር ይኖራል።በዚህ ቦታ የዕለት ጉርስ ማግኜት ለሱሌማንና ቤተሰቡ አስቸጋሪ ነዉ።
«አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ምግብ ይሰጡናል።ስራ ለማግኜት ሞክሬ ነበር ነገር ግን በጣም አስቸጋሪ ነዉ።ለስራ ፍለጋ እንደወጣሁ ላልመለስ እችላለሁ የሚል ስጋት አለኝ።ይህ በአንኛዉ  ልጄ ላይ ደርሷል።ለስራ እንደወጣ ለዕስራት ተዳርጎ ሳይመለስ በዚያዉ ቀርቷል።»
እሱና ቤተሰቦቹ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ተመዝግበዉ የሚገኙ ቢሆንም ምንም አይነት እርዳታ አያገኙም። ዉሃ የሚያገኙት እንኳ በአቅራቢያቸዉ ካለ መስጊድ የዉሃ ማጠራቀሚያ ነዉ።እናም የዕርሱንና የቤተሰቡን ህይወት ለማቆየት በዕየለቱ ይታገላል።ያም ሆኖ ግን በዉስጡ አንድ ግብ አለዉ።
«ፍላጎቴ ሊቢያ መቆየት አልነበረም።ልጆቼን ይዤ ወደ አዉሮፓ ለመሻገር እፈልጋለሁ።አስቸጋሪ መሆኑን አዉቃለሁ።ነገር ግን በዉሳኔዬ እፀናለሁ።የኔ ህልም አዉሮፓ መሄድ ነዉ።»ይላል።
ሱሌማን ይህን ይበል እንጅ ያም ሆኖ ወደ አዉሮፓ ለመሻገር የሚደረገዉ የሜዲቴራኒያን ባህር ጉዞ እጅግ አደገኛ ነዉ።እሱም ይንን ያዉቃል።አንድ የቅርብ ጓደኛዉ በዚሁ ጉዞ ልጁን አጥቷል።የሊቢያ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች የስደተኞችን ህይወት ለመታደግ ከጉዞ ወደ ባህር ዳርቻ ይመልሷቸዋል።በዚህ ሁኔታ የተያዘ ስደተኛ ግን የሚጠብቀዉ  የማጎሩያ ካምፖች መግባት ነዉ።እንደ ድንደበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን እነዚህ የማጎሪያ ካምፖች በቂ ንፅህና የሌላቸዉ፣ የተፋፈጉ በቂ ብርሃንና አየር የማገኙ ናቸዉ።ሱሌማን ይህን ያዉቃል።እናም በየብስ ወደ ቱኒዚያ ለመሄድን ይመርጣል።ለሱሌማን ወደ ሀገሩ ሱዳን መመለስ የማይታሰብ ነዉ።ኩርዱፋን ከተባላ ተራራማ የሱዳን አካባቢ የመጣ ሲሆን እርሱ እንደሚለዉ በቅርቡ ከስልጣን በወረዱት ኦማር አልበሽር ዘንድ ተዘንግቶ የቆየ አካባቢ በመሆኑ መሰረተ ልማት ፣ትምህርትና የጤና አገልግሎት የለሌለዉና ተስፋ የማይታይበት ቦታ ነዉ።
«ስደትን የመረጥኩት ልጆቼን ለመታደግ ነዉ።ብዙ ችግሮችና አደጋዎች አሉት።ነገር ግን ጌታ ይረዳናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ለልጆቼ የተሻለ  የወደፊት ዕድል ይሰጣቸዋል ብዬ አምናለሁ።በኮርዶፋን ትምህርት ቤቶች የሉም እስካሁን ሰወች የቧንቧ ዉሃ አያዉቁም።እናም የልጆቼን  እጣ ፋንታ መታደግ እፈልጋለሁ።»
በሊቢያ እንደ ሱሌማንና ቤተሰቡ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ አዉሮፓ ለመሻገር ፈልገዉ ሞትና እንግልት የሚያጋጥማቸዉ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አሉ።ከነዚህም ዉስጥ ወደ 7 ሺህ የሚጠጉት ሱዳናዉያን ናቸዉ።የኤርትራ፣ የሶማሊያና የኢትዮጵያ ስደተኞችም እዚያዉ ይገኛሉ።

Mittelmeer-Flüchtlinge auf der Sea Watch 3
ምስል Sea-Watch/Chris Grodotzki
Mittelmeer Rettungsschiff Sea-Watch mit Flüchtlingen
ምስል Sea-Watch.org/Chris Grodotzki

 

ፀሀይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ