1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ውስጥ የተበራከተው የጡት ካንሰር

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24 2013

በየዓመቱ በመላው ዓለም 2,1 ሚሊየን ሴቶች  ለጡት ካንሰር መጋለጣቸው በምርመራ እንደሚረጋገጥ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያ ውስጥም በካንሰር ከሚያዙት 34 በመቶው የጡት ካንሰር ታማሚዎች መሆናቸው ነው የሚነገረው።

https://p.dw.com/p/3kp0x
Krebs Krebszelle Illustration Symbolbild
ምስል Colourbox

«ካንሰር የሕይወት መጨረሻ ተደርጎ መታሰብ የለበትም»

ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ። በተለይም የጡት ካንሰር ታማሚዎቹ በሽታው ስር ሰድዶ ወደ ህክምና የሚሄዱ መሆናቸው ደግሞ ለህክምናው ከማስቸገሩ ሌላ ሕይወታቸውን የሚያስከፍላቸውም ጥቂት አይደሉም። በጥቅምት ወር በየዓመቱ ስለጡት ካንሰር ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች በመላው ዓለም ይከናወናሉ። በየዓመቱ በጥር ወር ስለዚህ በሽታ የአደባባይ የግንዛቤ ማስጨበጪያ እንቅስቃሴዎች ይደረጉ ነበር። ዘንድሮ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንቅፋት ሆኗል። ያ ማለት ግን ምንም አልተሠራም ማለት አይደለም ይላሉ በካንሰር ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው መንግሥታዊ ያልሆነው የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበረሰብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ በቀለ። እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ቁጥር አንድ የካንሰር ህመም የጡት ካንሰር ነው። የችግሩን ስፋት በመረዳትም በተለይ ለጡት ህክምና የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን የሚያመላክት ለሀኪሞች መገልገያ የሚሆን መመሪያ በባለሙያዎች እየተዘጋጀ ነው። መመሪያውም ለህክምናው ከምርመራው አንስቶ የሚኖሩ ቅደም ተከተሎች እንዲሁም ለታማሚ ምን መድኃኒት ሊሰጥ እንደሚገባና እንዴት መደረግ አለበት የሚለውን ያካትታል። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ለካንሰር ህክምና የሚሰጠው በውስን ሃኪም ቤቶች ነው። በዚህም ምክንያት ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበረሰብ ከተለያዩ ክልሎች የመጡና አቅም የሌላቸውን ታማሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ህክምና የሚያገኙበትን መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል። በአንድ ጊዜም ከ20 በላይ ሰዎችን የሚያስተናግደበት ማደሪያና መመገቢያ ስፍራም አለው። ሆኖም ከቅርብ ወራት ወዲህ የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ እና በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ይዞታው አስተማማኝ ባለመሆኑ ህክምናውን ሽተው የሚመጡት ሰዎች ቁጥር በጣም መቀነሱን ነው አቶ ወንዱ የገለፁልን።

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ
ምስል picture alliance/dpa/lsw

ወደ ድርጅቱ እንዲህ ላለው ድጋፍ የሚመጡ ወገኖች  ማደሪያ በመስጠት የምግብና መጓጓዣ ወጪ እንዲሁም የህክምናውን ወጪ ይሸፈንላቸዋል። የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበረሰብ ዋና ሥራ አስኪያጅ  በአብዛኛው ሰዎች በአሁኑ ወቅት ስለጡት ካንሰር በቂ የሚባል ግንዛቤ አግኝተዋል ብለው ያምናሉ። ለዚህ ማሳያውም ብዙዎች ችግራቸውን እያወቁ ለምርመራ መምጣታቸው መሆኑንም ይናገራሉ። የማታክመውን በሽታ ምንነቱን ባትመረምረው ይሻላል የሚል አባባል የተጠቀሙት አቶ ወንዱ ለካንሰር ህክምና የሚሆኑ የተደራጀ አቅም ሳይገነባ ሰዎችን ተመርመሩ ብሎ መገፋፋቱ ብቻውን የሚያስገኘው አዎንታዊ ውጤት ይኖራል ማለት አይቻልም ነው የሚሉት።

እዚህ ላይ ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለዚህ የጤና ችግር አስቀድመው የተረዱ ወይዘሮን ገመጠኝ እናጋራችሁ። ወይዘሮ ሜሮን ከበደ ይባላሉ። ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ስላላቸው በየጊዜው የጤና ይዞታቸውን በምርመራ ሲከታተሉ ይቆዩና ድንገት የጡት ካንሰር እንዳላቸው በሀኪም ይነገራቸዋል። እኚህ ወይዘሮ ቀደም ብለው በመመርመር ክትትል ቢያደርጉም ሀኪም የጤና ችግራቸውን አስቀድሞ እንዳላየላቸው ነው የሚናገሩት። በዚህ ምክንያትም የካንሰሩ ደረጃ ከዞሮ ከፍ ብሏል። ህመማቸው ከተገኘላቸው እና ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ከተነገራቸው በኋላ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ወዲያው ተገቢውን ህክምና ማግኘት የሚቻል አልነበረም። ወረፋው ለወራት መጠበቅን ግድ የሚል ነበር። ይዞታቸውን ያስተዋሉት ሀኪምም አቅሙ ካላቸው ወደውጪ በመሄድ ቶሎ እንዲታከሙም መከሯቸው።

Äthiopien | Pink Lotus Ethiopia | Logo

ወይዘሮ ሜሮን በራሳቸው የግል ተነሳሽነት በተከታታይ ያደረጉት ምርመራ የጡት ካንሰር እሳቸው እንዳሉት ጥቂት ዘግይቶም ቢሆን ተደርሶበት ታክመው ከዳኑ ወራት ተቆጠሩ። እኔ ታክሜ ድኛለሁ ብለው ግን ቤታቸው ገብተው አልተቀመጡም። እሳቸው ያጋጠማቸው አይነት አንዳንዴ በሀኪሞች ዘንድ ሊያጋጥም የሚችል መዘናጋት እንበለው የችግሩ ቀድሞ አለመታወቅ ብዙዎችን ለከፋ የጤና እክል ከዚያም ሲያልፍም ለሞት እያበቃ መሆኑን አስተውለዋልና ሌሎችን ለመደገፍ ተነሱ። ብዙዎች ህመማቸውንም ሆነ መፍትሄውን ለራሳቸው የመያዝ ዝንባሌ ባለበት ሀገር ወይዘሮ ሜሮን ፒንክ ሎተስ ኢትዮጵያ  የጡት  ካንሰር  መረዳጃን  ከጥቂት  ተባባሪዎቻቸው  ጋር  በመሆን  አቋቋሙ።

ብዙውን ጊዜም ሰዎች ወደ ህክምናው የሚሄዱት በሽታው ስር ከሰደደ በኋላ በመሆኑ ለሞት የመዳረግ አጋጣሚው የሰፋ መሆኑን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች በዚሁ ዝግጅታችን የገለጹበት አጋጣሚ አለ።  የፒንክ ሎተስ ኢትዮጵያ  የጡት  ካንሰር  መረዳጃ መስራች ወይዘሮ ሜሮን ከበደም ከልምዳቸው ተነስተው ያጠናከሩት ይህንኑ  ነው። በዘገየ ቁጥር የሚያስወጣው የህክምና ወጪ ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም ሊያስከፍል ይችላል ሲሉም ይመክራሉ።

ወይዘሮ ሜሮን ዛሬም ምክራቸው ሰዎች ካንሰርን የሕይወት መጨረሻ አድርገው ሊያስቡት አይገባም የሚል ነው። ምንም እንኳን በኮቪድ 19 ምክንያት ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችሉም በስልክ ሌሎችን ማማከር  ቀጥለዋል። የእሳቸው ተሞክሮ ለሎች ትምህርት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። የኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና ዘርፍ ግን ትኩረት ይፈልጋልና በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። በካንሰር ላይ የበኩላቸውን ለማድረግ የሚንቀሳቀሱትን ሁለቱንም እንግዶቻችንን በማመስገን እንሰናበት።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ