1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከ19 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለሚፈጅ መልሶ ግንባታ የሚሆን ፋታ አላት?

ሰኞ፣ ሰኔ 12 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት የ19.7 ቢሊዮን ዶላር መልሶ ግንባታ ይፋ ሲያደርግ አቶ አሕመድ ሽዴ የአገሪቱን ሰላም "ማዝለቅ እጅግ ወሳኝ" እንደሆነ ገልጸዋል። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚታየው ግጭት በዕቅዱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚስማሙት ዶ/ር ብዙነህ ጌታቸው እና ዶ/ር ቀልቤሳ መገርሳ "ትክክለኛው ጊዜ እስኪመጣ" መጠበቅ አትችልም ሲሉ ይሞግታሉ

https://p.dw.com/p/4SmIn
Äthiopien Mekelle Binnenvertriebene aus Tigray
ምስል Million Hailessilasse/DW

ኢትዮጵያ ከ19 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለሚፈጅ መልሶ ግንባታ የሚሆን ፋታ አላት?

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ መንግሥታቸው ይፋ ያደረገው ከ19.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚጠይቅ የመልሶ ግንባታ መርሐ-ግብር "እጅግ ሰፊ" እንደሆነ አላጡትም። ከመርሐ-ግብሩ ግዝፈት ባሻገር ግን ስኬት እና ውድቀቱን የሚበይኑ ሌሎች በርካታ መሠረታዊ ነገሮች ይኖራሉ።

አቶ አሕመድ ባለፈው ሰኔ 1 ቀን2015 የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፣ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና ዲፕሎማቶች በተገኙበት መርሐ-ግብሩ ይፋ ከተደረገ በኋላ "ሰላማችንን ማዝለቅ እጅግ ወሳኝ ነው። አገራዊ አንድነቱን የበለጠ ማጠናከር እጅግ በጣም ወሳኝ ነው" ሲሉ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ፊቱን ወደ መልሶ ግንባታ በይፋ ያዞረው ደም አፋሳሹን ጦርነት ያቆመ ሥምምነት በደቡብ አፍሪቃ በተፈረመ በሰባተኛ ወሩ ገደማ ነው። የመልሶ ግንባታ መርሐ-ግብሩም በዋንኛነት በፕሪቶሪያ የተፈረመው ሥምምነት ትሩፋቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ይመስላል።

በእርግጥ ጊዜው ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ መልሶ ግንባታ የምታዞርበት ነው?

ዶክተር ብዙነህ ጌታቸው ኢትዮጵያ ለመልሶ ግንባታ "ትክክለኛው ጊዜ እስኪመጣ" መጠበቅ አትችልም የሚል አቋም አላቸው። በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የበርሚንግሐም ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ብዙነህ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ለመልሶ ግንባታ ፋታ የምታገኝበትን ጊዜ ልጠብቅ ብትል ላይመጣ ይችላል።

"የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ሥምምነት ከተቋጨ በኋላ በአንጻራዊነት አገሪቷ ሰላም አግኝታለች። ሰላም አግኝታለች ስንል ጦርነት ወይም ግጭቶች ቆመዋል ሳይሆን ቢያንስ በትግራይ የነበረው ትልቁ ምንአልባትም በዚያ ወቅት ዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ጦርነቶች ትልቅ የነበረ ጦርነት መቆሙ ለአገሪቷ ትልቅ እፎይታ ነው" የሚሉት ዶክተር ብዙነህ "መንግሥት ወደ ልማት የመመለስ፤ ሌሎች በሌሎች ክልሎች ያሉ ትናንሽ ወይም መካከለኛ ግጭቶችን፣ ጦርነቶችን የማረጋጋት፣ በድርድር የመፍታት ሥርዓት የማስያዝ ተነሳሽነት መውሰዱ ግዴታ ነው" ሲሉ ይሞግታሉ።

"የኢትዮጵያን ታሪክ ስናይ ከግጭት ነጻ የሆነች አገር አልነበረችም። በኢሕአዴግ ጊዜ እንኳ በአንጻራዊነት የተረጋጋ ሥርዓት የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ክልሎች ትናንሽ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች ነበሩ" የሚሉት ዶክተር ብዙነህ  "ስለዚህ 'ትክክለኛው ጊዜ እስኪመጣ እንጠብቅ' ቢባል ጭርሱን ላይመጣም ይችላል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የመልሶ ግንባታው ዕቅድ "እንዲያውም ዘግይቷል" የሚሉት ዶክተር ብዙነህ "በነበረው ጦርነት የተጎዱ ተቋማትን፤ የመገንባት፤ የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው የመመለስ የማደራጀት ሥራዎች መተግበር አለባቸው" ሲሉ አስረድተዋል።

Äthiopien | PK Friedensgespräche | Redwan Hussien und Getachew Reda
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ፊቱን ወደ መልሶ ግንባታ በይፋ ያዞረው ደም አፋሳሹን ጦርነት ያቆመ ሥምምነት በደቡብ አፍሪቃ በተፈረመ በሰባተኛ ወሩ ገደማ ነው።ምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመቱ ጦርነት ፋታ ብታገኝም በቆዳ ስፋት እና በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆኑት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ግን በቅጡ አልተረጋጉም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ራሱን "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ጋር የሰላም ንግግር ቢጀምርም በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚካሔደው ግጭት የማገርሸት አዝማሚያ አሳይቷል።

የዐቢይ መንግሥት በክልሎች ይታዘዝ የነበረውን የልዩ ኃይል ሲያፈርስ በአማራ ክልል ከገጠመው ተቃውሞ በኋላ ያበጠው አለመረጋጋት ሙሉ በሙሉ መፍትሔ አልተበጀለትም። በሁለቱ ክልሎች የመንግሥት እና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ይገደላሉ። ሰዎች ይታገታሉ። መንገዶች ይዘጋሉ። እንዲህ አይነቶቹ ኩነቶች እንኳን ለግዙፍ የመልሶ ግንባታ መርሐ ግብር ቀርቶ ለለት ተለት የንግድ እንቅስቃሴ እንኳ እንከን እየፈጠሩ ነው።

በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ እንደሚሉት "አሁንም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ትክክለኛ መልሶ ግንባታ የማይታሰብ ነው።" ዶክተር ቀልቤሳ "ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ጤናማ የሆነ የፖለቲካ ግንኙነት [ማበጀት] እጅግ ረዥም ጊዜ ይፈጃል" የሚል እምነት አላቸው። በዚህም ምክንያት "አገሪቱ የፖለቲካ ችግሩ ሙሉ በሙሉ እስኪፈታ" መጠበቅ አትችልም። 

Äthiopien Konflikte
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመቱ ጦርነት ፋታ ብታገኝም በቆዳ ስፋት እና በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆኑት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ግን በቅጡ አልተረጋጉም። ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

"በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ትምህርት ቤቶቻቸው ፈርሰውባቸዋል፤ በጣም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የጤና ኬላዎች ወድመዋል። ብዙ ድልድዮች፤ ብዙ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ-ልማቶች ፈራርሰዋል። የአገሪቱ ዋና ዋና ፈርጥ የነበሩ የኢኮኖሚ፣ የኢንዱስትሪ ማዕከላት" ወድመዋል እያሉ የግጭቱን ዳፋ የሚዘረዝሩት ዶክተር ቀልቤሳ እነዚህን መልሶ ለመገባት "ሁሉ ነገር መልሶ እስኪስተካከል መጠበቅ አትችልም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።  

በሁለቱ ክልሎች የሚታዩት ግጭቶች ብርታት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያነሰ ቢሆንም እንኳ ዳፋቸው ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመላው አገሪቱ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ይኖረዋል። "በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ያለው ግጭት በእርግጥም በእንደዚህ አይነት መርሐ-ግብሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ነገር ግን ጦርነቶቹ እስኪቆሙ ምንም አይነት ዕቅድ፣ የዕርቅ ሒደት ወይም የሰላም ግንባታ ውስጥ አንግባ የሚባል ከሆነ ጦርነቶቹ ረዥም ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ " የሚል ሥጋት ያላቸው ዶክተር ብዙነህ "ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግጭቶችን ቆም አድርጎ መነጋገር አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ ግጭቶችን መፍታት አይቻልም" ሲሉ ተናግረዋል።  

የመልሶ ግንባታው መርሐ ግብር እንዴት ያለ ነው?

የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ያደረገው የመልሶ ግንባታ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ኃይለኛ ውድመት ካደረሰባቸው ሦስቱ ክልሎች በተጨማሪ ግጭት በነበረባቸው የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል የሚገኘው የኮንሶ ዞን ጭምር ተግባራዊ ይሆናል።

Tigray-Krise in Äthiopien
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ብርቱ ውድመት እና ኪሳራ አድርሷል። መንግሥት ይፋ ባደረገው ሰነድ ውድመት እና ኪሳራው 28.7 ቢሊዮን ዶላር ተገምቷል። ምስል UGC/AP/picture alliance

በገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ በተደረገው ሰነድ እንደሰፈረው ይኸ ዕቅድ በተለይ በሦስት ዋና ዋና ግቦች ላይ ያነጣጠረ ነው። በጦርነት እና ግጭት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ዘላቂ መተዳደሪያ የሚመልስ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ መፍትሔ የሚያበጅ ፤ ሴቶች፣ ድሆች እና ሌሎች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ለሁሉም ማኅበራዊ ፍትኅ የሚያሻሽል ሰዎችን ያማከለ መልሶ ግንባታ ማካሔድ ቀዳሚው ነው።

ለሁሉም እኩል እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለማቅረብ መሠረተ-ልማቶችን እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ጨምሮ ቁልፍ ጥሪቶችን መልሶ መገንባት በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ግብ ነው። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በዘላቂነት እንዲያገግም ኤኮኖሚውን የሚያረጋጉ እና የመዋዕለ-ንዋይ ከባቢውን የሚያጠናክሩ እርምጃዎች መውሰድ በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጧል።

የገንዘብ ሚኒስሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ዕቅዱን በይፋ ሲያስተዋውቁ "ጥሩ እቅድ ብቻውን በቂ አይደለም። በዚህ ምክንያት የመልሶ ግንባታ ሒደቱ እንዴት ይካሔዳል ለሚለው ጉዳይ የተለየ ትኩረት ተሰጥቷል" ሲሉ ተናግረዋል።  "መልሶ ግንባታ ስኬታማ፤ የሕዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ እንዲሆን እና መተማመን እንዲያጠናክር መልካም አስተዳደር፣ ቁጥጥር እና ክትትል፣ ተጠያቂነት እንዲሁም ጊዜውን የጠበቀ የመረጃ ልውውጥ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው" ሲሉ አስረድተዋል።

Infografik Karte Äthiopien EN
የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ያደረገው የመልሶ ግንባታ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ኃይለኛ ውድመት ካደረሰባቸው ሦስቱ ክልሎች በተጨማሪ ግጭት በነበረባቸው የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል የሚገኘው የኮንሶ ዞን ጭምር ተግባራዊ ይሆናል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመቋጨቱ ቀደም ብሎ የመልሶ ግንባታ መርሐ ግብር የጀመረው መንግሥት ለሥራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ በዓመታዊው በጀት ውስጥ አካቷል። አቶ አሕመድ ሽዴ እንዳሉት ግን መንግሥታቸው መልሶ ግንባታውን ለማካሔድ የለጋሾችን እጅ ይጠብቃል። የታቀደው የመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን  "በጣም የትዬለሌ ነው" የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ ከኢትዮጵያ አቅም በላይ መሆኑን ገልጸዋል። ዕቅዱ ሲዘጋጅ በዋናነት የልማት አጋሮችን ታሳቢ ማድረጉ ገንዘቡን ለማግኘት ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ለዚህም ምዕራባውያኑ የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግም ሆነ የተቋረጠውን የበጀት ድጎማ ለመጀመር ያሳዩትን ቸልተኝነት ዶክተር ቀልቤሳ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

በአምስት ዓመታት የሚከወነው የመልሶ ግንባታ ሦስት ምዕራፎች የየራሳቸው ግቦች አሏቸው። ማኅበራዊ ትስስር እና ደሕንነትን ለማጠናከር የተወጠነው የመጀመሪያ ግብ ብቻውን በአምስት ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን 3.45 ቢሊዮን ዶላር ይፈልጋል። ቁልፍ መሠረተ-ልማቶች እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ 6.67 ቢሊዮን ዶላር፤ የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት እንዲያገግም የሚከናወኑ ሥራዎች በአንጻሩ 9.48 ቢሊዮን ዶላር ይሻሉ። በአጠቃላይ አገሪቱ ለመልሶ ግንባታ 19.7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ትፈልጋለች። 

የክልል እና የፌድራል መንግሥት በጀት፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚጠበቅ ብድር እና ዕርዳታ ዋንኛ የገንዘቡ ምንጮች ናቸው። ዩክሬንን ጨምሮ ከኢትዮጵያ በበለጠ የለጋሾች እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ትኩረት የሚሰጣቸው በርካታ ችግሮች በዓለም ዙሪያ መኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ቀልቤሳ "የልማት አጋሮች የሚሰጡት ድጋፍ የተገደበ" እንደሚሆን ይገምታሉ። አገሪቱ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ በወደቀችበት በዚህ ወቅት ከግሉ ዘርፍ መበደር እንደሚቸግራት የሚናገሩት ዶክተር ቀልቤሳ "ኤኮኖሚውም ቢሆን የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይበታል። የታክስ ገቢ በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ ከሚባሉ መካከል ነው። የውጭ ንግዱም ችግር ውስጥ ገብቷል" ሲሉ ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"ሁኔታዎች በጣም የሚሻሻሉ ከሆነ፤ ዕዳ ስረዛ የሚኖር ከሆነ፤ ሰላም እየተሻሻለ የሚሔድ ከሆነ እነዚህ ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ" የሚሉት የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው "ከተቀመጠው በጀት ምንም አይገኝም እያልኩ አይደለም። ነገር ግን አብዛኛው መጠን ይገኛል የሚል መተማመን የለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።

ይኸ የመልሶ ግንባታ ወጪ የተሰላው መንግሥት በግጭት የደረሰውን ውድመት እና ኪሳራ ይፋ ያደረገበትን ሰነድ በመመርኮዝ ነው። በመንግሥት ስሌት መሠረት በግጭት የደረሰው ውድመት እና ኪሳራ 28.7 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይሁንና የመንግሥት የዳሰሳ ጥናት ከጥቅምት 2013 እስከ ሕዳር 2015 ገደማ ባለው ጊዜ ግጭት ያደረሰውን ውድመት እና ኪሳራ ብቻ የተመለከተ ነው።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ