1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀስ 

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 2012

ጥሬ ገንዘብ አውጥቶ መክፈል አሁን በጂጂጋ ዘመን ያለፈበት መስሏል። በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ከቅርብ ወራት ወዲህ በሞባይል ስልክ ገንዘብን ማንቀሳቀስ እጅግ ተስፋፍቷል። ሆኖም በአብዛኛው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የኢንተርኔት ግንኙነትን ይፈልጋል። ይህ ደግሞ የግንኙነት ትስስሩ አሁንም አስተማማኝ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ተግዳሮት ነው።

https://p.dw.com/p/3hYYJ
Afrika | Mobile money
ምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba

ኢትዮጵያ ውስጥ በሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀስ በቅርቡ የተጀመረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ አገልግሎቱ መስፋፋቱ እየታየ ነው። ቀደም ሲል አጋጅነት በነበረው ሕግና የደንበኞች ጥሬ ገንዘብን የመለዋወጥ ልማድ ምክንያት አገልግሎቱ በጣም ወደኋላ ብሎ ነበር። ሆኖም በቅርቡ በሕጉ ላይ በተደረጉ ለውጦችና ኮቪድ 19 ካስከተለው የንጽሕና ጥንቃቄ ጋር በተገናኘ ነገሮች ቀስ በቀስ እየተለወጡ በመሄድ ላይ ናቸው። አሁንም ግን በተለይ ገጠራማው አካባቢ በቀላሉ የሚደረስበት አልሆነም። 

ጥሬ ገንዘብ አውጥቶ መክፈል አሁን ጂጂጋ ላይ ዘመን ያለፈበት መስሏል። በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ከቅርብ ወራት ወዲህ በሞባይል ስልክ ገንዘብን ማንቀሳቀስ እጅግ ተስፋፍቷል። በዚህ ቡና ቤት ውስጥ ከደንበኞች ገሚሱ በስልክ ነው የሚከፍሉት። አብዱላዚዝ ሳላህ ከተገልጋዮች አንዱ ነው።
«ደህንነትህ የተጠበቀ ነው፣ በርካታ ገንዘብ በኪስህ ይዘህ መዘዋወር ስለማይኖርብህ ገንዘብህም ለአደጋ አይጋለጥም። ኮሮናን በተመለከተ ደግሞ ይህ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ በሌላ ሰው የተነካካ ገንዘብን ካንተ ያርቃል።»  
ጂጂጋ ላይ ሌላው ቀርቶ በስፋት የተለመደውንና የሚታወቀውን ጫት በሞባይል ገንዘብ ለመግዛት ይቻላል።  ከስድስት በፊት ሥራ የጀመረ አንድ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት አሁን 200 ሺህ ደንበኞች አፍርቷል። ሥራ አስኪያጁ አብዱላዚዝ ሀሰን እንደሚሉት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በስፋት ጥቅም ላይ ከዋለባት ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የሶማሌ ክልል በርካታ ጥቅሞች አሉት። 
«በዚህ ክልል ውስጥ በቀላሉ መግባት ይቻላል፤ በዚህ አካባቢ በሚገኙ ደንበኞች ምክንያትም አዲሱን ቴክኒዎሎጂ ለመላመድ በጣም ቀላል ነው። ቀለል ያሉ ና ይህን የመሳሰሉ ነገሮችን ይወዳሉ። እናም ክልሉ በሞባይል ገንዘብ ክፍያ አገልግሎት የተሠማሩ በርካታ ተፎካካሪዎችን እየሳበ ነው።»
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት መንግሥት እንዲህ ያለውን የገንዘብ አገልግሎት እንዲጠቀሙ ማበረታቻ እያደረገ ነው። በዚያም ላይ አንዳንድ አጋጅ የነበሩ ሕጎችንም በቅርብ ወራት ውስጥ ለውጧል። ሳምሶን ጌቱ ይህን አገልግሎት ከሚሰጡት አንዱ  የሆነው የአሞሌ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ናቸው። 
«የቀድሞዎቹ ደንቦች በዛም አነሰ የሚያተኩሩት የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ነበር። አዲሱ ደንብ እንደእኛ ያሉ የቴክኒዎሎጂ አገልግሎት ለሚያቀርቡ በኤክትሮኒክስ የመክፈል ፈቃድን ይሰጣል፤ ስለዚህ ደንበኞችን፤ ነጋዴዎችን፣ ወኪሎችን በማግኘት የገንዘብ ሽግግሩ በኩል ይበልጥ ፈታ ያለ አካሄድን ሰጥቶናል። ይህም በማደግና በመስፋፋቱ በኩል ሰፋ ያለ ዕድል ሰጥቶናል።» 
ሆኖም ግን በአብዛኛው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የኢንተርኔት ግንኙነትን ይፈልጋል። ይህ ደግሞ የግንኙነት ትስስሩ አሁንም አስተማማኝ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ተግዳሮት ነው። ቱክቱክ አሽከርካሪው ሀሰን አሊ ጊዜ ከማባከን በሚል አሁንም ደንበኞቹ በጥሬ ገንዘብ እንዲከፍሉት ነው የሚፈልገው። 
«አንዳንዴ ኔትወርክ ይቆማል ወይም በተከታታይ ለበርካታ ቀናት አይኖርም። ለእኔ በስልክ ገንዘብ ከፍለውኝ ያንን ለማግኘት ብዙ ከመጠበቅና ጊዜም ከማባከን በጥሬው ብቀበል ነው የሚሻለኝ።» 

China Peking Internet-Zensur
ምስል Getty Images/AFP/G. Baker
Äthiopien Polizei in Jijiga
ምስል picture-alliance/dpa/EPA

በመላ ሀገሪቱ ተመሳሳይ የተገልጋሎች ጸባይ በራሱ ዋና ፈተና ነው፤ በዋና ከተማዋ ሳይቀር። ይህ በእንዲህ እንዳለም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ወደገጠር ለመግባት ገና ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ውሱን የሆነው የባንክ አገልግሎት እንዲሁም የኢንተርኔት ግንኙነቱ ዝቅተኛነት ይህን አሠራር ወደዚያ ለማዳረስ አዳጋች ያደርገዋል። ሆኖም ዛሬም 80 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ከከተማ ውጭ የሚኖር በመሆኑ መሠረታዊው ነገር ቢስተካከል እጅግ ሰፊ ገበያ በዚህ ዘርፍ ይኖረዋል። 

ሸዋዬ ለገሠ/ማሪያ ጌርዝ ኒኩሊስኩ

እሸቴ ለገሰ