ኢሬቻ በአዲስ አበባ ሲከበር የታሰሩ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ተቃዋሚዎች ጠየቁ
ቅዳሜ፣ መስከረም 22 2014በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ በሚገኘው ደሎሎ ቡዴና የሆራ ስፍራ ኢሬቻ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ሲከበር አባገዳዎች እና ሃዳ ሲንቄዎች ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ታድሟል።
በባህላዊ ልብሶች ያሸበረቁ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች እና በገዳስርዓት ውስጥ ትልቁ ስፍራ የሚሰጣቸው አባገዳ፣ አባመልካ እና አባሙዳ እንዲሁም ሴት እናቶች ( ሃዳሲንቂዎች) ሆ..ያ ማሬዎ… እያሉ የኢሬቻውን ስርዓት አከናውነዋል፡፡
የቱለማ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዋና ጸኃፊ አባገዳ ጎበና ሆላ፣ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ እና የጉጂ አባገዳ ጂሎ መንኦ እንዲሁም ከየአከባቢው ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ አባገዳዎች ሆራ (ወንዙን) ባርከው የምርቃት እና የመልካም ምኞች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘመናዊነት በተላበሱ ሳቢ ባህላዊ ልብሶች ያሸበረቁ የበዓሉ ታዳሚያንም በየፊናቸው የባህሉን ትውፊት በጠበቀ መልኩ እየጨፈሩ ወደ ሆራው ስፍራ በማቅናት በደስታ እና በአንድነት ስርዓቱን ሲከውኑ ተስተውለዋል፡፡
ከማለዳው 12 ሰዓት ገደማ አባገዳዎች እና ሃዳ-ሲንቂዎች ከመስቀል አደባባይ የኢሬቻ ስርዓት ወደ ሚከበርበት ደሎሎ ቡዴና በሚያመሩበት ወቅት በመግቢያ በሩ አከባቢ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች እና በጸጥታ አካላቱ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት መጠነኛ መረጋገጥ ተስተውሏል፡፡
አባገዳዎቹ በዚው የኢሬቻ ስፍራ ስርዓቱን አከናውነው ከወጡም በኋላ በጭፈራቸው እና በተቃውሞ ድምጽ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎች እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ወጣቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙም ተደምጠዋል። ወጣቶች "ፍትህ ለሃጫሉ" የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።
ስዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ