1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃዊ አንድነት በሥዕል ሲገለፅ

ዓርብ፣ ግንቦት 18 2015

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ትናንት ሀሙስ 60ኛ ዓመቱን አክብሯል። ይህ ቀን በአፍሪቃ ህብረት አዳራሽ ብቻ ሳይሆን ሰሞኑን «አፍሪቃዊ ማንነት የሥዕል ትርዒት » በሚል መሪ ቃል አዲስ አበባ ውስጥ ለአራት ቀናት በቆየ የሥዕክ አውደ ርዕይ ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/4RqDv
Äthiopien | Panafrikanismus
ምስል W. Kebede

አፍሪቃዊ አንድነት በሥዕል ሲገለፅ

የፓን አፍሪካኒዝም አላማ የአፍሪካ ሀገራትን ከቅኝ ግዛት ማላቀቅ እና ኋላም ቅኝ ግዛት ካበቃ በኋላ በድንበር የተበታተነውን ህዝብ መልሶ አንድ ማድረግ ነበር።  የአፍሪቃውያን አንድ መሆን የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት  የአሁኑ አፍሪቃ ህብረት እንዲመሰረት ትልቅ ሚና ተጫውቷል። 60ኛውን ዓመት የአፍሪቃን አንድነት ለማስታወስ ሰሞኑን 60 ሰዓሊያን የተካፈሉበት አውደ ርዕይ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። «አፍሪቃዊ ማንነት የሥዕል ትርዒት » በሚል መሪ ቃል በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ካስተባበሩት ሰዎች መካከል ሰዓሊ እና የታሪክ ተመራማሪው ወንደሰን ከበደ አንዱ ነው። በዚህ ዝግጅት ሰዓሊዎቹን ማስተባበር እና የግል ታሪካቸውን መፃፍ ከስራ ድርሻው ዋንኛዎቹ እንደነበሩ ገልጾልናል። አራት ተቋማት ያዘጋጁት አውደ ርዕይ ካለፈው ሰኞ እስከ ትናንት ሀሙስ ድረስ ዘልቆ ነበር። አፍሪቃውያንን አንድ ያደረጋቸው «የጋራ የደህንነት አደጋ ውስጥ መግባታቸው ነው» የሚለው ወንደሰን አፍሪቃዊ ማንነት እንዲበለፅግ ኪነ ጥበብ እና ስነ ፁሁፍ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ይናገራል። በቀድሞው ትውልድ ሚና የነበራቸውን ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ የሚናገረው ወንደሰን ያም ሆኖ በአሁኑ ትውልድ በበቂ ሁኔታ በዚህ ላይ እየተሰራ ስላልሆነ ይህንን አውደ ርዕይ እንደጀመሩ ለዶይቸ ቬለ ገልጿል። « አዲስ አበባ የአለም ሶስተኛው የዲፕሎማት ከተማ ሆኗ ለምንድን ነው በስነ ጥበቡ መምራት የማትጀምረው? በየዓመቱ የአፍሪቃ መሪዎች አዲስ አበባ መጥተው እንደሚሰበሰቡ ሁሉ ለምንድን ነው የአፍሪቃ ሰዓሊያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የስዕል ስራቸውን የማያሳዩት እና የማያወሩት ብለን ነው መድረኩን የጀመርነው» ይላል የኢትዮጵያ ሰዓሊያን እና ቀራፂያን ማህበር ዋና ፀሀፊም የሆነው ወንደሰን። 
ረዥም ዓመታት በሥዕል ሙያ ላይ የቆየችው ሰዓሊ አይናለም ገብረማርያም አራቱ የአውደ ርዕይ ቀናት «ከጠበቅነው በላይ ሰው የጎበኘው እና የአደነቀው ነበር ትላለች።» በአይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የሥዕል አውደ ርዕይ ስትገልፅ። « 60 ዓመቱን በ60 ሰዓሊያን ነው ያከበርነው። ሁሉም ከኢትዮጵያ ነበሩ። ከውጭ ለማምጣት አሁን አልተመቸንም። ዝግጅቱን ቋሚ ስለምናደርገው በሚቀጥለው ዓመት ከመላው አፍሪቃ ቢያንስ አንዳንድ ሰዓሊ ለመወከል እንሞክራለን። 

Äthiopien | Panafrikanismus
ምስል W. Kebede

ሰዓሊያኑ በስዕላቸው የአፍሪቃን አንድነት እንዴት ገለፁ?

« ኢትዮጵያን መስራች መሆኗን የሚገልፅ፣ በማን ዘመን ነው የሆነው?  የሚለውን የሚገልፁ ስዕሎች ነው ያቀረብነው» ትላለች ሰዓሊ አይናለም። አሁን ኢትዮጵያ ላይ ህዝቡ በብሔር ተከፋፍሎ እንደ ኢትዮጵያዊ እንኳን አንድ መሆን ሲያዳግተው በሚስተዋልበት ሰዓት እንዴት አፍሪቃዊ ህብረትን ማጠንከር ይቻላል? ሰዓሊ አይናለም፤ ለዚህ ሰዓሊያን የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነ እና ለመሳካቱ ጥርጥር እንደሌላት ነው የገለፀችልን። « ህዝቡ የተዋለደ ነው። በደም ተሳስሯል። ወደድንም ጠላንም አንድ ነን። አፍሪቃውያንም ቢሆኑ ድንበር ተሰርቶ፣ የባንዲራ ልዩነት ነው እንጂ ወጥ ናቸው። ህዝቡ አንድ ነው የሚለውን ነው እኛ ሰዓሊያን ለህዝቡ ማስተማር የምንፈልገው » ትላለች።
ሰዓሊ እና የታሪክ ምሁር የሆነው ወንደሰንስ 60 ዓመታቱን መለስ ብሎ ሲቃኝ የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍ ምን ያህል ተሳክቷል ይላል? « የመጀመሪያዎቹ ፓን አፍሪቃውያን ያስቡት የነበረው ሆኗል ወይ ብንል አልሆነም። ግን እዚህም እዚያም አንዳንድ ጅምሮች አሉ። ለምሳሌ አረንጌዴ ፓስፖርት ብለው የጀመሩት። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ አፍሪቃውያን ወይም የአፍሪቃ ህብረት ከምዕራባውያን ነፃ አይደሉም። በአውሮፓውያኑ የገንዘብ ድጓማ ነው ያሉት። ራሳቸውን ከዚህ ነፃ ሳያደርጉ ይኼ ብሔራዊ ድንበር የሚለውን ለማፍረስ ትንሽ ይከብዳቸዋል።» ስለሆነም ይላል ወንደሰን።  መላው አፍሪቃውያንም ይሁኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወጣት ስለ የፓን አፍሪካኒዝም የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ በደንብ እንዲካተት እና ትውልዱ እንዲያውቅ ይመክራል። 

ሰዓሊ እና የታሪክ ምሁር ወንደሰን ከበደ
ሰዓሊ እና የታሪክ ምሁር ወንደሰን ከበደምስል W. Kebede

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ