1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ኒቆዲሞስ ኤሊያስ

ዓርብ፣ የካቲት 24 2015

ኒቆዲሞስ ኤሊያስ ገና ሚኒስትሪ ፈተና እንኳን አልተፈተነም። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የፕሮግራሚንግ ባለሙያ ሊሆን ችሏል። የ 14 ዓመቱ አዳጊ ወጣት እንደ ኔትፊሊክስ እና አማዞን የመሳሰሉ የተለያዩ ድረ ገጾችን አስመስሎ ሊሰራ ችሏል።

https://p.dw.com/p/4OB2z
ኒቆዲሞስ ኤሊያስ
ኒቆዲሞስ ኤሊያስምስል Elias. G/DW

ኒቆዲሞስ ኤሊያስ

ዓለማችን በየጊዜው በቴክኖሎጂ እየተራቀቀች ስለሆነ በርካታ ወጣቶች ከኮምፒውተር ጋር የተያያዘ ትምህርት መከታተል ወደፊት ስራ ይገኝበታል የሚል እምነት አላቸው።  አዎ! የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በሰለጠነ የሰው ኃይል ደረጃቸውን ለማሟላት ወይም ለመጠበቅ ስለሚፈልጉ የኮዲንግ እና ፕሮግራሚንግ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ፍላጎታቸው አሁንም ከፍተኛ ነው።  ባለፈው ሳምንት ህንድን የጎበኙት የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ  የ«ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሀገር» ብለው ከገለጿት ህንድ  የ IT ባለሙያዎችን ወደ ጀርመን አምጥተው ማሰራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ለዚህም ባለሙያዎችን ለመሳብ የቪዛ አሰጣጡ ላይ ጀርመን ማሻሻያ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

Intelligente Technologie, künstliche Intelligenz und Datensicherheit
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በሰለጠነ የ IT ባለሙያዎችን የሰው ኃይል ደረጃቸውን ለማሟላት ወይም ለመጠበቅ ይፈልጋሉምስል rook/YAY Images/IMAGO

የዛሬው እንግዳችንም ለቴክኖሎጂ በጣም ቅርብ ነው። ኒቆዲሞስ  ኤሊያስ ይባላል። ሌሎች ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን ድረ ገፆች እና መተግበሪያዎች የመስራት አቅም አለው። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዳበረው እውቀት ነው። የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ኒቆዲሞስ  ወይም ኒቆ ፕሮግራሚንግ መማር የጀመረው ባለፈው ዓመት የ13 ዓመት ልጅ ሳለ ነው። ከዛም የሰራሁት ይላል « የግሌ ድረ ገፅ እና ለስራዬ ማሳመሪያ እንዲሆን ደግሞ የኔትፊሊክስ እና የአማዞን ክሎኖች ነው።»  ፕሮግራሚንግ የመማር ሀሳቡ የኒቆዲሞስ ሳይሆን የአባቱ ነበር። በመጨረሻ ግን ኒቆዲሞስ ተግባሩን ወደደው። በደንብ ፕሮግራሚንግ የተማረው ኢቫንጋዲ ቴክ (Evangadi Tech) የተባለው እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው የኦንላይን አካዳሚ በሰጠው ነፃ የትምርት እድል አማካኝነት ነው። ይህንንም ትምህርት የተከታተለው ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ነው። « ከትምህርት ቤት ስመለስ ከ10 ሰዓት ጀምሬ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ይህንን አጠና ነበር» ይላል።

ኒቆዲሞስ በመደበኛው ትምህርቱ በተወሰነ ደረጃ የኮምፒውተር ትምህርት ይወስዳል። ይሁንና «ከቃል ትምህርት ባለፈ በተግባር የምንሰራው ነገር የለም። ለመስራት ብንፈልግ እንኳን በቂ እቃዎች አይቀርቡልንም» ይላል።   ይህንንም ክፍተት እና ፍላጎቱን ወላጆቹ ሊያሟሉለት ችለዋል። አባቱ፤ አቶ  ኤሊያስ ገብረ እግዜያብሔር  ልጃቸው ፕሮግራሚንግ እንዲማር ያበረታቱበት ሌላም ምክንያት አለ ፤ ከአሁኑ ተጨማሪ እውቀት ማዳበር አለበት ብለን እንደ ወላጅ ስለምናምን እንደዚህ አይነት ነገሮችን እንሞክርለት ነበር» ይላሉ አቶ ኤሊያስ። እሳቸውም የልጃቸውን ብቃት የተረዱት ኒቆዲሞስ ስክራች ኮዲንግ የተባለ አጭር ስልጠና በወሰደበት ወቅት ነው። ከዛም ይህንን ማዳበር የሚችልበትን መንገድ አፈላለጉ።

ኒቆዲሞስ ኤሊያስ
ኒቆዲሞስ ኤሊያስ በቀን ለአራት ሰዓት ያህል ያጠና ነበርምስል Elias. G/DW

አዱኛ በቀለ ኒቆዲሞስ የተማረበት የኢቫንጋዲ ቴክ አካዳሚ መስራች ነው።  አካዳሚው « በአሁኑ ሰዓት ከ 15 በላይ አሰልጣኞች ያሉት ሲሆን እስካሁን ለ11ኛ ጊዜ  ነፃ የትምህርት እድል ሰጥቷል » ይላል አዱኛ። በየዙሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 30 ተማሪዎች ይህንን ነፃ የትምህርት እድል ያገኛሉ።  በባለፈው ዙር 30ዎቹ ተማሪዎች የተመረጡት ለትምሕርቱ ካመለከቱ ከ 1100  ሰዎች  መካከል ነው « እነሱን ለመምረጥ ያስቀመጥናቸውን መስፈርቶች አሉ።  ከዛም የፃፉትን እናያለን።» ይህም በነጥብ ይያዝና አሳማኝ ምላሽ የሰጡትን አካዳሚው ይመርጣል።  « ኒቆም ያገኘው ውጤት ሲደመር ከሁሉም በለጠ» ይላል አዱኛ ኒቆዲሞስ እንዴት ነፃውን የትምህርት እድል እንዳገኘ ሲያብራራ።  በብዛት ትምህርቱን የሚከታተሉት ከ 20 እስከ 40 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ እንደ ኒቆዲሞስ ገና አዳጊ የሆኑ ወጣቶች አልፎ አልፎም ጡረታ የወጡ ሰዎች እንደሚገኙበት አዱኛ ለዶይቸ ቬለ ገልጿል።

ኒቆዲሞስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፕሮግራሚንግ ተምሮ ብዙ ነገሮች መስራት ቢችልም  እድሜው ለስራ ስላልደረሰ ተቀጥሮ መስራት አይችልም። ወላጆቹም አሁን ይበልጥ መደበኛ ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር እያበረታቱት ነው« ስምንተኛ ክፍል ስለሆነ የሚኒስትሪ ተፈታኝ ነው የሚሆነው። ግን ያገኘው እውቀትም ሙሉ በሙሉ የሚተው ከሆነ የሚጠፋ ነገር ነውና እሱንም እንዳይረሳው  ጎን ለጎን ጊዜ አመቻችቶ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ይሰራል።» ይላሉ አባቱ አቶ ኤሊያስ።

የኒቆዲሞስን ችሎታ የሚያደንቀው የኢቫንጋዲ ቴክ መስራች እና የፕሮግራሚንግ አሰልጣኝ፣ አዱኛ በዚህ ሙያ ስራ ለማግኘት ያለው ፉክክር በኒቆዲሞስ ደረጃ እውቀት ላዳበረም ሰው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ሳይገልፅ አላለፈም። « ከሌላ ቴክኖሎጂ ፊልድ እድሉ የተሻለ ነው። ግን ፉክክር እየበዛበት ነው። » አዱኛ እንደነገረን ስልጠናው በዋናነት በትርፍ ጊዜው የሚማር ተማሪን ከግንዛቤ አስገብቶ የሚሰጥ ስለሆነ  «የሰዓት ልዩነት ብዙም ሚና እንዳይጫወት አድርገን ነው ያሰናዳነው» ይላል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ