1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ አበባ፦በመኪና አደጋ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል

ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2012

ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገለጠ። በትናንትናው አደጋ 45 ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ እና መካከለኛ ጉዳት፤ እንዲሁም 17ቱ ላይ እጅግ ጽኑ የመቁስል አደጋ መድረሱ ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/3Q0LB
Äthiopien Busunfall in Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

ዓርብ መስከረም 9 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ከሽሮ ሜዳ ወደ ካዛንችስ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ፦ A 68377 የኾነ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ከሌላ ኮድ 3 የግል ጠቆር ያለ ተሽከርከርካሪ ጋር ከተጋጨ በኋላ ድልድይ ስር ተወርውሮ በመገልበጡ የ2 ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ 31 ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ አደጋ ደርሶባቸዋል። ተጎጂዎቹ ዘውዲቱ መታሰቢያ እና ዳግማዊ ምኒልክ እንዲሁም አቤት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲኾን፤ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ ለዶቼ ቬለ (DW)ተናግረዋል።

Äthiopien Busunfall in Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

ከኢዮቤልዮ ቤተመንግሥት ዝቅ ብሎ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ያለው ድልድይ ስር ተወርውሮ የገባው ይህ አውቶቡስ ዛሬ ማለዳ ሲነሳ፤ 7 ከባድ የእሳት አደጋ እና መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል። በአጠቃላይ አደጋው ሲከሰት 94 ተሳፋሪዎች የነበሩ ሲኾን፤ 45ቱ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ እና መካከለኛ ጉዳት፤ እንዲሁም 17ቱ ላይ እጅግ ጽኑ የመቁስል አደጋ መድረሱ ተዘግቧል። ትናንት ማታ አደጋ የደረሰባቸውን ተሳፋሪዎች ወደ ሆስፒታል ለማመላለስ 12 አምቡላንሶች ሲንቀሳቀሱ ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ